በሕንድ ምርጫ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ ለሦስተኛ ዙር እንደሚያሸንፉ ግምት ተሰጣቸው

ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ

የሕንዱ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ ድምጽ የመስጠት ሂደቱ በተጠናቀቀው ምርጫ ለሦስተኛ ዙር አሸናፊ እንደሚሆኑ ተመለከተ።

ከሕዝብ የተሰበሰበ አስተያየት የሞዲ ባጋራቲያ ጃናታ ፓርቲ (ቢጄፒ) በአጠቃላይ ምርጫው ቀዳሚው እንደሚሆን አሳይቷል።

ይሁን እንጂ ተንታኞች ከዚህ ቀደም በሕንድ የዜና ወኪሎች የተሰሩ የሕዝብ አስተያየቶች ትክክለኛ እና ገለልተኛ አልነበሩም ይላሉ።

ባለፉት ሰባት ምርጫዎች ቢጄፒ፤ ከተቃዋሚው ኮንግረስ ፓርቲ እና ከሌሎች የግዛት ፓርቲዎች ጠንካራ ፉክክር ሲገጥመው ቆይቷል።

በሕንድ አንድ ፓርቲ ወይም ጥምር ፓርቲ መንግሥት ለመመስረት በፓርላማው 272 ወንበሮችን ማሸነፍ ይኖርበታል።

የሕንድ የዜና ወኪሎች የሰሩት ጥናት በቢጄፒ የሚመራው፤ ብሔራዊ ዴሞክራሲያዊ ጥምረት (ኤንዲኤ) በፓርላማው 272 ወንበር የማግኘት ሰፊ ዕድል እንዳለው አሳይተዋል።

ከአንድ ወር በላይ የፈጀው የድምጽ መስጠት ሂደት መጠናቀቁን ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ ምርጫውን ማሸነፋቸውን አውጀዋል።

“የሕንድ ሕዝብ ክብረ ወሰን በሆነ ቁጥር የኤንዲኤ መንግሥትን ዳግም መምረጡን በመተማመን መናገር እችላለሁ” ሲሉ በኤክስ ገጻቸው ላይ ጽፈዋል።

የዜና ወኪሎች በዚህ ምርጫ የናሬንድራ ሞዲ ጥምር ፓርቲ ከ355 እስከ 380 ወንበር እንደሚያገኝ የገተመተ ሲሆን የተቃዋሚዎች ጥምረት ደግሞ ከ125 እስከ 165 ወንበር ሊያሸንፉ ይችላሉ ብለዋል።

1.4 ቢሊዮን ሕዝብ ባላት ሕንድ፤ የአሜሪካ፣ ሩሲያ፣ ጃፓን፣ ብሪታኒያ፣ ብራዚል እና ፈረንሳይ አጠቃላይ ሕዝብ ተደምረው ሊስተካከሉት የማይችሉት 969 ሚሊዮን ሕዝብ ድምጽ ለመስጠት ብቁ ነው።

ይህ ሁሉ ሕዝብ ድምጽ ሰጥቶ እስኪጨርስ የ6 ሳምንታት ጊዜም አስፈልጓል።

በሕንድ ከፍተኛ የሥራ አጥ ቁጥር እና ምግብ እና ነዳጅን ጨምሮ የመሠረታዊ ቁሶች ዋጋ መናር ዋነኛ የምርጫ አጀንዳዎች ነበሩ።