ሪያል ማድሪድ ዌምብሌይ ላይ ዶርትሙንድን በማሸነፍ የሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫን አነሳ

ሪያል ማድሪድ የሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫን አነሳ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ሪያል ማድሪድ ቦሪስያ ዶርትሙንድን 2 ለምንም በማሸነፍ የአውሮፓ የሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫን አነሳ።

ዶርትሙንድ በተለይም በመጀመሪያው አጋማሽ ያባካናቸውን ዕድሎች ተጽዕኖ ያልፈፈጠሩበት ማድሪድ ለ15ኛ ጊዜ የአውሮፓ ትልቁን ዋንጫ ለማንሳት ችሏል።

አሰልጣኝ ካርሎ አንቸሎቲም አምስተኛ የሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫቸውን በማንሳት ታሪክ ለመጻፍ በቅተዋል።

የዶርትሞንዶቹ ካሪም አድዬሚ እና ኒክላስ ፉልከርግ ያገኟቸውን ዕድሎች ሳይጠቀሙባቸው ቀርተዋል።

ማድሪድ በሁለተኛው አጋማሽ ማብቂያ ላይ በዳኒ ካርቫሃል እና በቪንሺየስ ጁኒየር ጎሎች አማካይነት ለድል በቅቷል።

በዚህም ማድሪድ በአውሮፓ ትልቁ የክለቦች መደረክ የማይቀመስ መሆኑን አስመስክሯል።

በተለይም በጨዋታው የመጀመሪያ አጋማሽ ላይ የዶርትሙንድ ፈጣን አጨዋወት ከአቅሙ በላይ መስሎ ያመሸው ማድሪድ በአስፈላጊው ሰዓት ግን ውጤቱን ማሳካት ችሏል።

ለቡድናቸው የመጨረሻ ጨዋታውን ያደረገውን ቶኒ ክሩስን ጨምሮ ካርቫሃል፣ ናቾ እና ሉካ ሞድሪች ስድስተኛ የሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫቸውን አንስተዋል።

የማድሪድ ተጫዋቾች

የፎቶው ባለመብት, PA Media

ዶርትሙንዶች ከ11 ዓመት በፊት በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ለፍጻሜ ደርሰው በባየርን ሙኒክ ተሸንፈው ዋንጫውን ያጡበትን የዌምብሌይ ስታዲየም አሳዛኝ ምሽት በደስታ ለመቀየር ወደ ለንደን ከተማ ቢያቀኑም ስኬታማ አልሆኑም፡፡

ሪያል ማድሪድ ለፍፃሜው የደረሠው የጀርመኑን አር ቢ ሌብዚሽ፣ የእንግሊዙን ማንቸስተር ሲቲን እንዲሁም የጀርመኑን ባየርን ሙኒክን በጥሎ ማለፉ ሒደት በማሸነፍ ነው፡፡

ቢጫ ለባሾቹ በምድብ ማጣሪያው ኤሲ ሚላን፣ ኒውካስትል ዩናይትድ እና ፓሪስ ሳን ዠርሜን በመብለጥ የምድቡ መሪ ሆነው ወደጥሎ ማለፍ ዙር ተቀላቅለዋል።

በጥሎ ማለፉ ደግሞ የሆላንዱን ፒኤስ ቪ አይንድሆቨን፣ የስፔኑን አትሌቲኮ ማድሪድን እንዲሁም የፈረንሳዩን ፒ ኤስ ጂን ከውድድሩ በማስወጣት ለፍጻሜ ደርሰዋል፡፡