የመስቀል ወፍ፡ አብራን ያለች እንግዳ ወይስ መስቀል ጠብቃ የምትመጣ ባዳ?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
*የመስቀል ወፍ ለወራት ጠፍታ ቆይታ አዲስ ዓመት ሲገባ በተለይ ደግሞ መስከረም ሲጋመስ እንደምትከሰት በብዙዎች ዘንድ ይታመናል።
በአባባልም አንድ ሰው ለረጅም ጊዜ ጠፍቶ ቆይቶ ድንገት ሲከሰት “ምነው የመስቀል ወፍ ሆንክ” ይባላል። ይህም ለረጅም ጊዜ ሳይታዩ ወይም ጠፍቶ ቆይቶ መታየትን ለማመልከት ማኅበረሰቡ የሚጠቀምበት አባባል ነው።
አእዋፋትን በቅርበት የሚያጠኑት አቶ ይልማ ደለለኝ ግን “እነዚህ የመስቀል ወፍ ተብለው የሚታወቁት አእዋፋት እንደሚባሉት ለረጅም ጊዜ ተሰውረው ቆይተው በመስቀል ሰሞን የሚከሰቱ ሳይሆኑ ዘወትር አብረውን የሚኖሩ ናቸው” ይላሉ።
እንደባለሙያው ከሆነ በኢትዮጵያ በመስቀል ወፍ ስም የምትታወቀው አንድ አይነት ዝርያ ያላት ወፍ ብቻ ሳይሆን ቁጥራቸው ከአራት በላይ የሆኑ የተለያዩ ዝርያ ያለቸው አእዋፋት ናቸው።
ለዚህም እንደምሳሌ የሚጠቅሱት ቁራ በሚል የሚጠሩ አእዋፋት ቢኖሩም በውስጣቸው የተለያዩ ዝርያዎች እንዳሉት ሁሉ የመስቀል ወፍ ውስጥም የተለያዩ የወፍ አይነቶች መኖራቸውን ነው።
ከእነዚህ የመስቀል ወፎች መካከልም አዘውትረን የምናያቸው እና በቅርብ የምናውቃቸው ትንንሽዬዎቹ ድንቢጥ ተብለው የሚታወቁት አእዋፋትም በመስቀል ወፍነት ከሚጠሩት ውስጥ ይካተታሉ።
እንደየቋንቋው እና እንደየአካባቢው እነዚህ ወፎች የየራሳቸው ስያሜ እና መጠሪያ ሊኖራቸው እንደሚችል የሚጠቅሱት አቶ ይልማ፣ የመስቀል ወፍ የሚባሉት ግን በርካታ አይነት ወፎች በውስጣቸው አካትተዋል ይላሉ።
በእንግሊዝኛው እነዚህ አዕዋፋት ኢንዲጎ በርድስ፣ ዋይዳ፣ ቢሾፕ ወይም ዊዶ በርድ ተብለው እንደሚታወቁ እና በእነዚህ ውስጥም የተለያዩ ዝርያዎች መኖራቸውን ባለሙያው ያስረዳሉ።
ወፎቹ የሚታዩበት ጊዜ
እነዚህ የመስቀል ወፍ ተብለው የሚጠሩት አእዋፋት በስፋት ታይተው በበርካቶች ዐይን ውስጥ የሚገቡት የክረምቱ ወራት አብቅቶ የበጋው ወቅት በሚጀምርበት መስከረም ወር ላይ ነው።
አእዋፋቱ በአብዛኛው ዘር በል በመሆናቸው በዚህ ወቅት ደግሞ የሚደርሱ ሰብሎች በስፋት የሚገኙበት እና ወፎቹም የሚራቡበት አመቺ ወቅት በመሆኑ በስፋት እንደሚስተዋሉ አቶ ይልማ ይናገራሉ።
እነዚህ አእዋፋት ባሕሪያቸው ከአንድ አካባቢ ወደሌላ አካባቢ ወቅቶችን እና የአየር ሁኔታዎችን እየተከተሉ የሚሰደዱ በመሆናቸው በሌሎች አገራት ውስጥም ይገኛሉ።
አቶ ይልማ እንደሚሉት የተለያዩ አእዋፋት በተለያዩ ወቅቶች በተለይ ከሰሜናዊ ንፍቀ ክበብ ወደ አፍሪካ የሚመጡ ሲሆን፣ በሌላ ጊዜ ደግሞ ወደዚያው ተመልሰው የሚሄዱም አሉ።
ወደ ኢትዮጵያ ወቅቶችን ጠብቀው የተለያዩ ወፎች ከመካከለኛው ምሥራቅ፣ ከስካንዴኔቪያን፣ ከምሥራቅ አውሮፓ አገራት እንዲሁም ከሩሲያ የሚመጡ እንዳሉ እና እነዚህም በስደተኛ ወፍነት በባለሙያዎች እንደሚታወቁ ይገልጻሉ።
የመስቀል ወፍ ተብለው የሚታወቁት አብዛኞቹ ግን በኢትዮጵያ ውስጥ እና በዙሪያዋ ባሉ አገራት ውስጥም የሚገኙ ናቸው። ስለዚህ አእዋፋቱ ከኢትዮጵያ ባሻገር በኬንያ፣ በኡጋንዳ እና በታንዛንያ ውስጥ እንደሚገኙ ይጠቅሳሉ።
‘አብረውን ያሉ እንግዶች’
አቶ ይልማ እንደሚሉት በልምድ እንደምንለው የመስቀል ወፍ ለረጅም ጊዜ ጠፍተው ቆይተው በመስቀል ወቅት የሚከሰቱ እንዳልሆኑ እና በዙሪያችን አብረውን የሚኖሩ ናቸው።
አእዋፋቱ አዲስ የሚሆኑብን አብረውን በዙሪያችን በሚቆዩበት ጊዜ የሚኖራቸው ገጽታ በመስከረም ወር ላይ በተፈጥሯዊ ሂደት ቀለማቸው ተለውጦ ዐይነ ግቡ ስለሚሆኑ የዚያ ወቅት አዲስ ክስተት እንደሆኑ ስለሚታሰብ ነው።
“ለዚህም የአዕዋፋቱን ተፈጥሮ መረዳት ያስፈልጋል” የሚሉት አቶ ይልማ እነዚህ ወፎች ላይ ይህ ተፈጥሯዊ ለውጥ የሚታየው በዋናነት በመስከረም ወር ላይ የሚራቡበት ጊዜ በመሆኑ ነው።
ይህ ደግሞ ከመስቀል በዓል ጋር ተቀራራቢ በመሆኑ የተለየ ገጽታን ተላብሰው እንዲታዩ ያደርጋቸዋል።
የተፈጥሮ ሂደት
በመስከረም ወር ላይ እንስት አእዋፋቱ እንቁላል ለመጣል የሚዘጋጁበት በመሆኑ ተባዕቱ ለእሱ እና ለተጣማሪው እንዲሁም ለሚፈለፈሉት አእዋፋት የሚያስፈልገውን ምግብ እና መጠለያን በሚያገኝበት ቦታ ላይ አንድ የተወሰነ አካባቢን ከልሎ ይይዛል።
የመራቢያ ጊዜ በመሆኑ ወንዱ ይህንን በሚያደርግበት ወቅት የላባው መጠን ይረዝማል ቀለሙም ይቀየራል። ቀለሙ ደማቅ እና ውብ ስለሚሆን የሰዎችን ዐይን በመሳብ እንደ አዲስ ወፍ ሊታይ ይችላል ይላሉ አቶ ይልማ።
ይህ ቀለምም ከሩቅ የሚታይ እንደሚሆን የሚናገሩት ባለሙያው፣ በተለይ ፀሐይ በሚያገኘው ጊዜ በማንጸባረቅ ትኩረት የመሳብ አቅም አለው።
በተጨማሪም ለውጡ የሚከሰተው በመራቢያ ጊዜ በመሆኑ እንስት ወፎችን ለመሳብ እና ለማማለል ከመጥቀሙ በተጨማሪ በአንጸባራቂ ውበቱ በቀላሉ ስለሚታይ፣ እንዲሁም በዚህ ላይ ዝማሬን ስለሚጨምር ሌሎች አእዋፋት የእርሱን አካባቢ እንዲርቁ ያደርጋቸዋል።
እንግዲህ ይህ የአእዋፋቱ ሥነ አካላዊ ለውጥ ነው በሌለው ጊዜ በአካባቢያችን ይኖሩ የነበሩትን እነዚህን ወፎች ለረጅም ጊዜ ጠፍተው በመስቀል ወቅት ብቅ ያሉ እንዲመስሉ ያደረጋቸው ይላሉ አእዋፋቱን በቅርበት የሚያጠኑት አቶ ይልማ ደለለኝ።
ባለሙያው እንደሚሉት “በአካባቢያችን ያሉትን አእዋፋት በቅርበት የመከታተል ልምድ ስለሌለን እና ክረምቱ አልፎ መስከረም አጋማሽ ላይ አእዋፋቱ ላባቸው በቀለማት አሸብርቆ በቀላሉ ዐይናችን ውስጥ ሲገቡ በዙሪያችን የነበሩት ወፎች ሳይሆኑ ጊዜ እየጠበቁ ብቅ የሚሉ ይመስሉናል።”
ቀለማቸው እና ዝማሬያቸው ከአዲስ ዓመት እና ከመስከረም የፀሐይ ወቅት ጋር ተዳምሮ ከሚፈጠረው መልካም ስሜት ጋር የሁሉንም ቀልብ ስለሚስቡ ሁሉም ይመለከታቸዋል፤ በዚህም ሳቢያ አዲስ ወፍ የመስቀል ወቅትን ጠብቆ እንደመጣ ይታመናል።
የመስቀል ወፍ ብለን የምንጠራቸው አእዋፋት ከሌሎች ለየት የሚሉት ተባዕቶቹ በጣም ደማቅ ቀለም ሲኖራቸው፣ ሴቷ ግን ቡኒ ወይም ወደ ግራጫ የሚያደላ ቀለም ነው ያላት፤ በመራቢያ ወቅት ወንዱ ከበርካታ እንስት አእዋፋት ጋር የመሆን ባሕሪ እንዳለውም አቶ ይልማ ይጠቅሳሉ።
ስለዚህ የአእዋፋት አጥኚ የሆኑት አቶ ይልማ ደለለኝ እንደሚሉት የመስቀል ወፎች ለረጅም ጊዜ ሳይታዩ ቆይተው መስከረም ወር ላይ የሚከሰቱ ዓመታዊ እንግዶች ሳይሆኑ አብረውን ቆይተው በተፈጥሮ ሂደት የላባቸው ቀለም የሚቀየር ቤተኛ አእዋፋት ናቸው ማለት ነው።
__________
* ይህ ጽሁፍ በድጋሚ የቀረበ ነው።












