አሜሪካዊው ተዋናይ በመኪና ዘራፊዎች በጥይት ተገደለ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
አሜሪካዊው ተዋናይ ጆኒ ዋክተር በመኪናው ላይ ዘረፋ ሊፈጽሙ በሞከሩ ግለሰቦች ተገደለ።
ተዋናዩ ሎስ አንጀለስ ውስጥ የመኪናውን አካል ለመስረቅ በሞከሩ ዘራፊዎች በተተኮሰበት ጥይት ነው ሕይወቱ ያለፈው።
የ37 ዓመቱ ተዋናይ አቁሞት የነበረውን መኪና አካል ሦስት ዘራፊዎች ለመስረቅ ሲሞክሩ ለመከላከል ጥረት አድርጎ ነበር።
በዚህ ወቅትም ዘራፊዎቹ ከፍተኛ ጉዳት አድርሰውበታል።
ተዋናዩ ባለፈው ቅዳሜ ምሽት ሕይወቱ እንዳለፈ ተገልጿል።
ወኪሉ ዴቪድ ሻውል “በጣም ድንቅ ሰው ነበር። የለበሰውን ካናቴራ ሳይቀር ለሰው ይሰጥ ነበር” ሲል እንደገለጸው ቫራይቲ ዘግቧል።
‘ጄኔራል ሆስፒታል’ በተባለው ፊልም ከሚታወቀው ተዋናዩ ጋር ለዓመታት አብረው እንደሠሩ ገልጾ “ሞቱ እስከወዲያኛው ድረስ ልባችንን ይሰብረዋል” ብሏል።
የተዋናዩ እናት የሆኑት ስካርሌት ለኤንቢሲ4 ቴሌቪዥን እንደገለጹት፣ ልጃቸው ከሥራ ሲመለስ ነበር መኪናው ላይ የዝርፊያ ሙከራ የተደረገው።
አንድ ግለሰብ መኪናው ጋር ሲያገኝ ተጠግቶ እንዳናገረውና ወዲያው ተኩስ እንደተከፈተበት እናቱ ተናግረዋል።
የልጃቸውን ግድያ “ትርጉም አልባ” ብለውታል።
ሊሰረቅ የነበረው የመኪናው አካል ካታሊቲክ ኮንቨርተው በዘራፊዎች ዒላማ የሚደረገው በውስጡ የከበረ ብረት ስላለው ነው።
እስካሁን ከግድያው ጋር በተያያዘ በቁጥጥር ሥር የዋለ ሰው እንደሌለ ተገልጿል።
የጄኔራል ሆስፒታል ፊልም አዘጋጆች “ድንቅ ሰው ነበር። ከእሱ ጋር መሥራት ታላቅ ዕድል ነበር” ብለዋል።
ጆኒ ዋክተር በ2013 ‘ሳይቤሪያ’ በተባለ ተከታታይ ፊልም እና ‘ዌስትወርልድ’ በተባለ ተከታታይ ፊልም ላይም ተውኗል።












