በወሲብ ፓርቲ የምትታወቀው የፈረንሳይዋ ከተማ ከንቲባ እና የጠንቋይዋ ቅሌት

የፈረንሳይዋ የባህር ዳርቻ ከተማ አግደ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

አግደ የተሰኘችው የፈረንሳይዋ የባህር ዳርቻ ከተማ በውብ የባሕር ዳርቻ ነጭ አሸዋ እና በማይጠልቀው ፀሐይዋ ነው የምትታወቀው። ከዚህም በላይ ግን የከተማዋን ስም ያገነነው የምታዘጋጀው የወሲብ ፓርቲ ነው።

የጋራ ወሲብ ላይ መሳተፍ የሻቱ አውሮፓውያን ወደዚህች ከተማ በየዓመቱ ይጎርፋሉ። በሺህ የሚቆጠሩ ጥንዶች ወደ አግደ መጥተው ከሌሎች ጥንዶች ጋር በመቀያየር ወሲብ ይፈጽማሉ።

ነገር ግን ይህቺን በወሲብ ቱሪዝም ዝናዋ ከፍ ያለ ከተማ ከሰሞኑ መነጋገሪያ ያደረጋት የተለመደው ጉዳይ ሳይሆን ፈረንሳዊያንን አጀብ ያሰኘ ሌላ ዜና ነው።

በአካባቢው የምትገኝ አንዲት "ፍርቱና ተንባይ" [ጠንቋይ]፣ የከተማዋ ከንቲባ እንዲሁም የቀድሞ የደኅንነት ሠራተኛ እና የፖሊስ መኮንን የዜናው ማጠንጠኛ ሆነዋል።

ጠንቋይዋ እና ከንቲባ አሁን እሥር ቤት ናቸው። ምርመራ ተከፍቶባቸዋል። ፍርቱና ተንባይዋ ሶፊያ ማርቲኔዝ ከንቲባውን በማጭበርበር ተከሳለች። ከንቲባው ደግሞ የግብር ከፋዮችን ረብጣ ገንዘብ ጠንቋይዋ ላይ በማፍሰስ ሙስና ሰርቷል የሚል ክስ ቀርቦበታል።

ሶፊያ የሞቱ ሰዎችን ታናግራለች የሚል ዝና ተሰጥቷታል። ከንቲባው የሞቱ አባቱን እንድትናግርለት ሲጠይቃት ጥያቄውን ለማስተናገድ አላቅማማችም። "ስኬታማም ሆነች"። የጠንቁልና ሥራውን ስትጀምር ድምጿ የከንቲባውን አባት መስሎ ቁጭ ይላል።

ሶፊያ የተባለችው ሴት ከንቲባውን በአካል እና በስልክ እንዲህ ስታጨበርብር አራት ዓመታት አልፈዋል። ከንቲባው "ከሞቱ ሰዎች" በርካታ ስልኮች እንደሚደወሉለት አምኖ ቆይቷል። አንዳንድ ጊዜ መላዕክት ደውለው ጠንቋይዋን እንዲደጉማት ይነግሩታል።

ይሄኔ ነው ሙስናው የሚመጣው።

ከንቲባው የሕዝብ ገንዘብ ተጠቅሞ ሶፊያ እና ቤተሰቧን ሲያዝናና፤ አንድ ጊዜ ፖሊኔዥያ ሌላ ጊዜ ደግሞ ታይላንድ ሲልካት ነበር። "ድምፆቹ" የጠንቋይን ወዳጅ ዘመዶች እንዲቀጥር እንዲሁም ቤቷን እንዲያድሱላት ነግረውታል ይህንን አድርጓል ተብሎ ተወቅሷል።

የከተማዋ የቢዝነስ ሰዎች የጠንቋይዋን ቤት በነፃ ነው ያደሱላት። ይህን ያደረጉት ከንቲባው ከተቀየመን ወደፊት ሥራ አይሰጠንም በሚል ፍራቻ ነው።

ይህ ዜና ፈረንሳይን ናኝቷል። ብዙዎች ጆሯቸውን ማመን ከብዷቸዋል። የከንቲባው ጠበቃ የሆኑት ዣን ማርክ ዳሪጌድ ዝነኛ ሆነዋል።

"በጣም የሚገርም ዜና ነው" ይላሉ ጠበቃው። "በአንድ በኩል አንድ ፖለቲከኛ አለ። የከተማዋ ከንቲባ እና የቀድሞ የፓርላማ አባል ነው። ደግሞ በጣም ብሩህ አእምሮ ያለው ሰው ነው። እንደዚህ ያለ ሰው በአንዲት ጠንቋይ እንዲህ ሰጭበረበር ማየት አስገራሚ ነው።"

"ይህቺ ሴት ወደ ሰውዬው ሕይወት መጥታ የሞቱ አባትህን ላናግርልህ ትላለች። ደካማ ጎኑን አገኘችው። ይህን ተጠቅማ የግል ፍላጎቷን ስታሟላ ከርማለች። መጨበርበሩን ለማመን ብዙ ጊዜ ወስዶበታል" ይላሉ ጠበቃው።

የጠንቋይዋ ጠበቃ ሉክ አብራትክዊዝ ግን በዚህ አይስማሙም።

"እርግጥ ነው የከንቲባው እምነት በልታለች፤ ይህንንም አምናለች። ነገር ግን የማጭበርበር ስልት አይደለም። ያደረገችውን ነገር አምናለች፤ ሆኖም ዶክተሮች እና የኪነ-ሕንፃ ባለሙያዎች ሳይቀሩ ለመግለፅ ከባድ የሆነ ኃይል እንዳላት ያምናሉ" ይላሉ።

"ከዚህ በፊት በሕይወታቸው የተከሰተ፤ ነገር ግን ማንም የማያውቀውን ምስጢር እሷ ታውቃለች።"

ምንም እንኳ ጠበቃዎቹ ባይስማሙም የከተማዋ ነዋሪዎች ግን የዚህ ሁሉ ምንጩ ነው ይላሉ።

የከተማዋ ከንቲባ ጄን

የፎቶው ባለመብት, Check

የምስሉ መግለጫ, የከተማዋ ከንቲባ ጄን

ደረቷን ለፀሐይ ገልጣ መንገድ ዳር ከተሰደረች አንዲት ካፌ ቡና እየጠጣ የነበረው ዣን-ማክስ "ከንቲባው ይመቸኛል። ከንቲባው ለኔ ጥሩ ነው። ነገር ግን ተጭበርብሯል። ምናልባት ከሷ ፍቅር ይዞት ሊሆን ይችላል" ይላል።

ሌላኛው የከተማዋ ነዋሪ ደግሞ "እኔ የዚህ ሁሉ ጣጣ መነሻው ወሲብ ነው ባይ ነኝ። ገንዘብ የነካው ነገር ወሲብም ሳይነካው አይቀርም" ሲል አስተያየቱን ይሰጣል።

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ቀኝ-ዘመም ፓርቲዎች በዚህ አካባቢው ከፍተኛ ድጋፍ እያገኙ መጥተዋል። የከንቲባው ከፍተኛ ነቃፊ የሆኑት ፋቢዬን ቬርሳኖ የአክራሪዋና ቀኝ-ዘመሟ ማሪን ለ-ፔን ፓርቲ አባል ናቸው። ከንቲባው ሥራቸውን በገዛ ፈቃዳቸው ሊለቁ ይገባል ይላሉ።

"ሩህሩህ ሊሆን ይችላል። ከለተያዩ ሴቶች ጋር በፍቅር መውደቅም መብቱ ነው። እሱ ግላዊ ሕይወቱ ነው። ነገር ግን የግብር ከፋዮችን ገንዘብ መጠቀም ሌላ ነገር ነው" ይላሉ ፋቢዬን።

"ከተማዋን መሳለቂያ አድርጓታል።"

የከተማዋ ዳኛ፤ ከንቲባው እና ፍርቱና ተነብያለሁ የምትለውን ግለሰብ በፖሊስ ቁጥጥር ሥር እንዲቆዩ ብለዋል። ይህን ያደረጉት ምስክሮችን እንዳያገኙ በማሰብ ነው።

ማርቲኔዝ የሴቶች ማረሚያ ቤት ሳለች ሌሎች ታራሚዎች ጥንቆላ ትሰራለች በሚል ስለደበደቧት አሁን ብቻውን እንድትቆይ ተደርጋለች።