የኢራኑ ፕሬዝዳንት በእስራኤል ጥቃት ጉዳት ደርሶባቸው እንደነበር ተዘገበ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የኢራን ፕሬዚዳንት ማሱድ ፔዜሽኪያን ባለፈው ወር እስራኤል በቴህራን ላይ በፈፀመችው ጥቃት ቀላል ጉዳት እንደደረሰባቸው ተዘገበ።
ለአብዮታዊ ዘብ ቅርብ የሆነው የኢራን የመንግሥት ፋርስ የዜና ወኪል እንደዘገበው ሰኔ 9/2017 ዓ.ም. ፔዜሽኪያን ጉዳት የደረሰባቸው በቴህራን በሚገኝ ምስጢራዊ የመሬት ስር ተቋም ውስጥ በከፍተኛ የብሔራዊ ደህንነት ምክር ቤት አስቸኳይ ስብሰባ ላይ በተገኙበት ወቅት ነው።
በዕለቱ እስራኤል ምስጢራዊውን የመሬት ውስጥ ተቋም መግቢያ እና ወደ ተቋሙ የሚያመሩ መስመሮች ላይ ስድስት ቦምቦች እንደጣለች የዜና ወኪሉ ዘግቧል።
ፕሬዚዳንቱ ከሌሎች ሰዎች ጋር በአደጋ ጊዜ መውጫ በኩል ሲያመልጡ በእግራቸው ላይ ጉዳት ደርሶባቸዋል ተብሏል። በአሁኑ ሰዓት ኢራን የእስራኤል ሰላዮች ሰርገው መግባታቸውን የሚያመለክቱ ፍንጮችን እየመረመረች እንደሆነ ተዘግቧል።
የፋርስ የዜና ወኪል ዘገባ በገለልተኝነት አልተረጋገጠም። እስራኤልም እስካሁን ዘገባውን በተመለከተ በይፋ አስተያየት አልሰጠችም።
በ12 ቀናቱ ጦርነት ወቅት ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የተለጠፉ ቪድዮዎች በሰሜን ምዕራብ ቴህራን በሚገኝ ተራራ ላይ የተፈጸሙ ተደጋጋሚ ጥቃቶችን አሳይተዋል።
አሁን የተገኙ መረጃዎች እንደሚያስገነዝቡት በአራተኛው የጦርነት ቀን የተሰነዘሩት ጥቃቶች የኢራን ከፍተኛ መሪዎች ተሰብስበውበት የነበረውን በቴህራን የሚገኝ ሚስጥራዊ የመሬት ስር ተቋም ዒላማ ያደረጉ ነበሩ።
የፋርስ የዜና ወኪል ዘገባ እንደሚያመለክተው በዕለቱ እስራኤል የፈጸመችው ጥቃት ተቋሙ ያሉትን ስድስት የመግቢያ እና መውጫ ነጥቦች እንዲሁም የአየር ማስገቢያ እና ማስወጫ ስርዓት እንዲዘጉ አድርጓል።
ለተቋሙ የተዘረጋው የኤሌክትሪክ ኃይልም ተቋርጦ የነበረ ቢሆንም ፔዜሽኪያን ግን ደህንነታቸው ተጠብቆ ወጥተዋል ተብሏል።
ከፍተኛው የብሔራዊ ደህንነት ምክር ቤት ከጠቅላይ መሪው ከአያቶላህ አሊ ኻሜኒ ቀጥሎ የኢራን ከፍተኛ ውሳኔ ሰጪ አካል ነው።
ባለፈው ሳምንት ፔዜሽኪያን እስራኤል የግድያ ሙከራ እንዳደረገችባቸው በመግለጽ ከስሰዋል።
የእስራኤል የመከላከያ ሚኒስትር በእስራኤል ካትዝ ግን የጦርነቱ ግብ በኢራን "የስርዓት ለውጥ" ማምጣት እንዳልሆነ በመግለጽ ክሱን ውድቅ አድርገዋል።
እስራኤል በጦርነቱ የመጀመሪያ ቀናት በፈጸመቻቸው ጥቃቶች በርካታ ከፍተኛ የኢራን አብዮታዊ ዘብ እና የጦር አዛዦች ገድላለች።
የኢራን መሪዎች የእስራኤል ጥቃት በድንገት እንደተፈጸመባቸው እና ቢያንስ በመጀመሪያዎቹ 24 ሰዓታት ውስጥ ውሳኔ ለመስጠት የሚያስችል አቋም ላይ እንዳልነበሩ አምነዋል።
የእስራኤል ባለስልጣናትም በተመሳሳይ አያቶላህ ኻሜኒ ዒላማ እንደነበሩ አምነዋል። ነገር ግን ጠቅላይ መሪው ከውጭው ዓለም ወደ ተቆራረጠ እና ደህንነቱ ወደ ተጠበቀ ምስጢራዊ ቦታ ሲዛወሩ ሊከታተሏቸው እንዳልቻሉ ገልጸዋል።
ይሁንና እስራኤል ሚስጥራዊ ተቋማት የሚገኙበትን ስፍራ ቀርቶ የኢራን ከፍተኛ ባለስልጣናት እና አዛዦች የት እንዳሉ ለማወቅ ያስቻላትን ወሳኝ መረጃዎች እንዴት ሰበሰበች የሚለው አሁንም ድረስ ጥያቄ ነው።
ሰኔ 6 ቀን እስራኤል፤ ኢራን የኒውክሌር መሳሪያ እንዳትሠራ ለመከላከል ነው በሚል በቴህራን የኒውክሌር እና ወታደራዊ ጣቢያዎች ላይ ድንገተኛ ጥቃት ፈጽማለች።
እስራኤል በአየር ላይ ጥቃት በመሰንዘር የበቀል እርምጃ የወሰደችው ኢራን በበኩሏ፤ የኒውክሌር መሳሪያ ለማምረት ጥረት አለማድረጓን በመግለጽ ክሱን አስተባብላለች። ኢራን የዩራኒየም ማበልጸጊያዋ የምትጠቀመው ለሰላማዊ ዓላማዎች መሆኑንም ትናገራለች።
ሰኔ 15 ቀን የአሜሪካ የአየር እና የባህር ኃይሎች በሦስት የኢራን የኒውክሌር ተቋማት ላይ የአየር እና የሚሳኤል ጥቃቶችን ፈጽመዋል።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጥቃቱ ተቋማቱን "ደምስሷል" ብለዋል። አንዳንድ የአሜሪካ የደህንነት ኤጀንሲዎች ግን ጥቃቱ ያደረሰውን ጉዳት መጠን በተመለከተ ያላቸው ምልከታ በጥንቃቄ የተሞላ ነው።















