አቶ ታዬ ደንደአ በዋስ እንዲለቀቁ ተወሰነ

የፎቶው ባለመብት, SM
የቀድሞ የሰላም ምክትል ሚኒስትር እና የኦሮሚያ ክልል ምክር ቤት አባል አቶ ታዬ ደንደአ በዋስ እንዲለቀቁ መወሰኑን ባለቤታቸው ወ/ሮ ስንታየሁ አለማየሁ ለቢቢሲ ተናገሩ።
የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ውሳኔውን ያሳለፈው ሰኞ፣ ህዳር 23/ 2017 ዓ.ም በዋለው ችሎት ነው።
ሰበር ሰሚ ችሎት የአቶ ታዬ ደንደአን ዋስትና የፈቀደው የሥር ፍርድ ቤቶች የዋስ ጥያቄያቸውን ውድቅ ካደረጉ በኋላ ነው።
ፍርድ ቤቱ አቶ ታዬ ደንደአ በ20ሺህ ብር የዋስትና ገንዘብ በማስያዝ ወይም በዋስ እንዲፈቱ ብያኔ ማሳለፉን ባለቤታቸው ለቢቢሲ ገልጸዋል።
አቶ ታዬ ዛሬ ከሰዓት በኋላ አስፈላጊውን እንዲያሟሉ መጠየቃቸውን ጨምረው ባለቤታቸው ተናግረዋል።
ባለፈው ዓመት ከስልጣን ከተባረሩ በኋላ ለእስር የተዳረጉት አቶ ታዬ፣ ሁከትና ብጥብጥ በማነሳሳት፣ ፀረ-ሰላም ኃይሎችን በመደገፍ እንዲሁም የጦር መሳሪያ ህጉን በመተላለፍ ወንጀሎች ተከሰው ነበር።
የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ የህገ መንግሥትና ህገ መንግሥት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች ችሎት ከዚህ ቀደም ከሶስቱ ክሶች መካከል በሁለቱ፣ ሁከትና ብጥብት በማነሳሳት እና የጸረ- ሰላም ኃይሎችን ድጋፍ ማድረግ ክሶች በነጻ አሰናብቷቸው ነበር።
የጦር መሳሪያ ወንጀሎችን በተመለከተ የቀረበባቸውን ክስ እንዲከላከሉ ፍርድ ቤቱ በዚያኑ ችሎት ውሳኔ ያሳለፈ ሲሆን አቶ ታዬ ጉዳዩን እናውቃለን የሚሉ አምስት የመንግሥት ባለስልጣናትን ለምስክርነት ጠርተው ነበር።
በምስክርነት ካቀረቧቸው መካከል በቅርቡ ከኃላፊነታቸው የተነሱት የቀድሞው የሰላም ሚኒስትር አቶ ብናልፍ አንዷለም እና የፌደራል ፖሊስ ምክትል ኮሚሽነር መላኩ ፈንታ ምስክርነታቸውን መስጠታቸው ይታወሳል።
በቀሪዎቹ የመንግሥት ባለስልጣናት ምስክርነት ለመስማት ፍርድ ቤቱ ለታህሳስ 3/ 2017 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።
አቶ ታዬ በምስክርነት ቀርበው ያስረዱልኝ ካሏቸው መካከል የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ እና የአዲስ አበባ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ይገኙበታል።
ዐቃቤ ህግ በአቶ ታየ ደንደአ ላይ ሶስት ተደራራቢ ክሶችን የመሰረተው ባለፈው ዓመት ሚያዚያ 2016 ዓ.ም ነበር።
ዐቃቤ ሕግ በአቶ ታዬ ላይ ክስ የመሠረተው የወንጀል ሕጉን ሁለት ድንጋጌዎች እና የጦር መሳሪያ አስተዳደር እና ቁጥጥር አዋጅን በመጥቀስ ነው።
የዐቃቤ ሕግ የመጀመሪያ ክስ በወንጀል ሕጉ “ከጠላት ጋር መተባበር”ን የሚመለከተውን ድንጋጌ መሠረት አድርጎ የቀረበ ነው።
ይህ የዐቃቤ ሕግ ክስ “መንግሥት ከኦነግ ሸኔ [የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት] እና ከፋኖ ጋር በሚያደርገው ጦርነት ላይ የኦነግ ሸኔን[የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት] አቋም የሚደግፍ እና የሚያበረታታ ጽሁፎች ሲጽፉ ነበር” የሚል ይዘት ነበረው።
ሁለተኛው የዐቃቤ ሕግ ክስ ደግሞ “መገፋፋትና ግዙፍ ያልሆነ የማሰናዳት ተግባር” የሚመለከተውን የወንጀል ድንጋጌ በመንተራስ የቀረበ ነበር።
ይህ መገፋፋት “በሕገ መንግሥቱ እና በመንግሥት ላይ የሚደረጉ ወንጀሎች” እና “በመንግሥት የውጭ ደኅንነት እና በመከላከያ ኃይል ላይ የሚደረጉ ወንጀሎች”ጋር የተያያዘ ነው።
ሦስተኛው በአቶ ታዬ ደንደአ ላይ የቀረበው ክስ “ቤታቸው ሲበረበር አንድ ፈቃድ የሌለው ክላሺንኮቭ ጠመንጃ ከቤታቸው ተገኝቷል” የሚል ነበር።












