የቀድሞው የሰላም ሚኒስትር ዲኤታ አቶ ታዬ ደንደአ ወደ ቃሊቲ ማረሚያ ቤት እንዲወርዱ በፍርድ ቤት ትዕዛዝ ተሰጠ

የቀድሞው የሰላም ሚኒስትር ዲኤታ አቶ ታዬ ደንደአ

የፎቶው ባለመብት, SM

በዐቃቤ ሕግ ሦስት ተደራራቢ ክሶች የቀረቡባቸው የቀድሞው የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ታዬ ደንደአ ያቀረቡት የዋስትና ጥያቄ ውድቅ ተደርጎ ወደ ቃሊቲ ማረሚያ ቤት እንዲወርዱ በፍርድ ቤት ብይን ተሰጠ።

ብይኑን የሰጠው ዛሬ ሐሙስ ግንቦት 1 ቀን 2016 ዓ. ም. የዋለው የፌራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ አንደኛ የሕገ መንግሥት እና ሕገ መንግሥት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች ችሎት ነው።

ችሎቱ ለዛሬ የተቀጠረው ለሁለት ዋና ዋና ጉዳዮች መሆኑን የአቶ ታዬ ጠበቃ ቱሊ ባይሳ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ፍርድ ቤቱ ለዛሬ የተቀጠረበት አንደኛው ጉዳይ በተከሳሽ በኩል ለቀረበው የመጀመሪያ ደረጃ የክስ መቃወሚያ የዐቃቤ ሕግን ምላሽ ለመጠባበቅ ነበር።

ዐቃቤ ሕግ ባለፈው ሳምንት ተከሳሽ በጽሑፍ ላቅረቡት የመጀመሪያ ደረጃ የክስ መቃወሚያ አምስት ገጽ ምላሽ ለፍርድ ቤት ማቅረቡን አቶ ቱሊ ገልጸዋል።

ሁለተኛው ችሎት የተመለከተው ጉዳይ፣ አቶ ታዬ ከዚህ በፊት ሚያዝያ 17 ቀን 2016 ዓ. ም. በነበረው ችሎት ያቀረቡት የዋስትና ጥያቄ ነው።

የአቶ ታዬ ጠበቆች በሚያዝያ 17ቱ የችሎት ውሎ፤ “ዋስትና ሕገ መንግሥታዊ መብት ነው” ያሉት ጠበቆች “ተፈጸመ የተባለው ድርጊት እጅግ በጣም ተራ” እና “ምንም ዓይነት የወንጀል ይዘት የሌለው ቀላል ነገር” መሆኑን በመጥቀስ የአቶ ታዬ የዋስትና መብት እንዲጠበቅ ጠይቀው ነበር።

ዐቃቤ ሕግ በበኩሉ “የቀረቡት ክሶች ተደራራቢ ናቸው፤ ዋስትናም ያስከለክላሉ” የሚል መከራከሪያ በማቅረብ ዋስትናውን ተቃውሞ ነበር።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የግራ ቀኙን ክርክር ያዳመጠው ፍርድ ቤት ዛሬ ረፋድ ላይ ተሰይሞ በዋስትናው ላይ ያስተላለፈውን ብይን በንባብ ማሰማቱን አቶ ቱሊ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ፍርድ ቤቱ “ተከሳሽ የተከሰሱበት ወንጀል ተደራራቢ እና ከፍ ያለ ቅጣት ሚያሰጥ በመሆኑ የዋስትና ጥያቄውን በጊዜያዊነት አልተቀበልንም” የሚል ብይን መስጠቱን ጠበቃው አክለው ገልጸዋል።

ይህን ብይን ተከትሎ ፍርድ ቤቱ፤ “የተሻለ ምግብ እና ውሃ የሚገኝበት እና ጥብቃ የሚደረግበት ቃሊቲ ማረሚያ ቤት እንዲሄዱ እና ከአቻ እስረኞች ጋር እንዲታሰሩ፣ አግባብነት ባለው በደኅና አያያዝ እንዲያዙ” ትዕዛዝ መስጠቱን ጠቁመዋል።

ዐቃቤ ሕግ በአቶ ታዬ ደንደአ ላይ የመሠረታቸው ሦስት ክሶች፤ የወንጀል ሕጉን ሁለት ድንጋጌዎች እና የጦር መሣሪያ አስተዳደር እና ቁጥጥር አዋጅን በመንተራስ የቀረቡ ናቸው።

የዐቃቤ ሕግ የመጀመሪያ ክስ በወንጀል ሕጉ “ከጠላት ጋር መተባባር”ን የሚመለከተውን ድንጋጌ መሠረት አድርጎ የቀረበ ነው።

ዐቃቤ ሕግ ሁለተኛውን ክስ ደግሞ ያቀረበው “መገፋፋትና ግዙፍ ያልሆነ የማሰናዳት ተግባር” የሚመለከተውን የወንጀል ድርንጋጌ በመጥቀስ ነው።

ሦስተኛው በአቶ ታዬ ደንደአ ላይ የቀረበው ክስ “ቤታቸው ሲበረበር አንድ ፈቃድ የሌለው ክላሺንኮቭ ጠመንጃ ከቤታቸው ተገኝቷል” የሚል መሆኑን ጠበቃ ቱሊ ተናግረዋል።

ፍርድ ቤቱ የዛሬውን የችሎት ውሎ ከማጠናቁ በፊት የዐቃቤ ሕግን ምላሽ መርምሮ ብይን ለመስጠት ለግንቦት 13 ቀን 2016 ዓ.ም. ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

አቶ ታዬ ደንደአ “መንግሥትን ለመጣል በማሴር” ተጠርጥረው በቁጥጥር ሥር የዋሉት ከአምስት ወራት ገደማ በፊት ታኅሣሥ 1 ቀን 2016 ዓ.ም. ነበር።

አቶ ታዬ በቁጥጥር ሥር ሲውሉ የፀጥታ እና የደኅንነት የጋራ ግብረ ኃይሉ “ከኦነግ ሸኔ አመራሮች እና በሽብር ወንጀል ከተጠረጠሩ ጽንፈኛ ኃይሎች ጋር ትስስር በመፍጠር መንግሥትን በአመጽ፣ በሽብር እና በትጥቅ ትግል ለመጣል ሲያሴር ተደርሶበታል” የሚል ውንጀላ እንደቀረበባቸው ይታወሳል።