ዐቃቤ ሕግ በቀድሞው የሰላም ሚኒስቴር ዲኤታ አቶ ታዬ ደንደአ ላይ ሦስት ተደራራቢ ክሶችን መሠረተ

አቶ ታዬ ደንደአ

የፎቶው ባለመብት, MINISTRY OF PEACE

“መንግሥትን ለመጣል ሲያሴሩ ነበር” በሚል በቁጥጥር ስር የዋሉት የድሞው የሰላም ሚኒስቴር ዲኤታ አቶ ታዬ ደንደአ በዐቃቤ ሕግ ሦስት ተደራራቢ ክሶች እንደተመሠረተባቸው ጠበቃቸው ለቢቢሲ ተናገሩ።

ዐቃቤ ሕግ በአቶ ታዬ ላይ ክስ የመሠረተው የወንጀል ሕጉን ሁለት ድንጋጌዎች እና የጦር መሳሪያ አስተዳደር እና ቁጥጥር አዋጅን በመጥቀስ መሆኑን ከጠበቆቸው አንዱ አቶ ቱሊ ባይሳ ገልጸዋል።

የዐቃቤ ሕግ ክስ ሚያዝያ 14/ 2016 ዓ.ም. የተጻፈ መሆኑን የጠቀሱት ጠበቃ ቱሊ፤ አቶ ታዬ በማግስቱ ማክሰኞ ልደታ በሚገኘው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ችሎት መቀረባቸው አመልክተዋል።

“በመጀመሪያው ቀን ከጠበቆች ጋር አልተገናኙም ምንም የተነገራቸው ነገር የለም ከሰዓት በኋላ ወስደው ብቻቸውን ነው ፍርድ ቤት [ያቀረቧቸው]” ብለዋል ጠበቃ ቱሊ።

አቶ ታዬ ለመጀመሪያ ጊዜ ያለ ጠበቃ ፍርድ ቤት ከቀረቡ በኋላ ለሁለተኛ ጊዜ ትናንት ሐሙስ ሚያዝያ 17 ከአራት ጠበቆቻቸው ጋር በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ አንደኛ የሕገ መንግሥት እና ሕገ መንግሥት ሥርዓት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች ችሎት ቀርበዋል።

በሐሙሱ የችሎት ውሎ ለአቶ ታዬ እና ለጠበቆቻቸው ዐቃቤ ሕግ በዳኞች ተነቦላቸዋል።

የዐቃቤ ሕግ የመጀመሪያ ክስ በወንጀል ሕጉ “ከጠላት ጋር መተባባር”ን የሚመለከተውን ድንጋጌ መሠረት አድርጎ የቀረበ ነው።

ይህ የዐቃቤ ሕግ ክስ “መንግሥት ከኦነግ ሸኔ እና ከፋኖ ጋር በሚያደርገው ጦርነት ላይ የኦነግ ሸኔን አቋም የሚደግፍ እና የሚያበረታታ ጽሁፎች ሲጽፉ ነበር” የሚል ይዘት ያለው መሆኑን ጠበቃ ቱሊ ባይሳ ለቢቢሲ አብራርተዋል።

የወንጀል ሕጉ “ማንኛውም ኢትዮጵያዊ የሆነ ወይም የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም እንዲያስከብር በግልጽ አደራ የተጣለበት ሰው ኢትዮጵያ በጦርነት ላይ በምተገኝበት ጊዜ ወይም ግዛቷ በሙሉ ወይም በከፊል በጠላት በተወረረበት ጊዜ የጠላትን ዓላማ ለማሳካታ በማሰብ በምክርም ሆነ በተግባር ጠላትን የደገፈ እንደሆነ” ከሃያ ዓመት በማይበልጥ ጽኑ እስራት እንደሚቀጣ ያትታል።

የወንጀል ሕጉ አክሎም፤ “ነገሩ ከባድ በሆነ ጊዜ በዕድሜ ልክ ጽኑ እስራት ወይም በሞት ይቀጣል” ይላል።

“የጠላትን ወይም የወራሪን ጥቅም በሚያራምድ ፕሮፓጋንዳ፣ የፕሬስ ወይም ሌላ የመገናኛ ዘዴ ውስጥ” መሳተፍ በወንጀል ሕጉ ከተጠቀሱ ድርጊቶች መካከል ናቸው።

ሁለተኛው የዐቃቤ ሕግ ክስ ደግሞ “መገፋፋትና ግዙፍ ያልሆነ የማሰናዳት ተግባር” የሚመለከተውን የወንጀል ድርንጋጌ በመንተራስ የቀረበ ነው።

ይህ መገፋፋት “በሕገ መንግሥቱ እና በመንግሥት ላይ የሚደረጉ ወንጀሎች” እና “በመንግሥት የውጭ ደኅንነት እና በመከላከያ ኃይል ላይ የሚደረጉ ወንጀሎች”ጋር የተያያዘ ነው።

አንድ ግለሰብ የተጠቀሱት ወንጀሎች እንዲፈጸሙ ለማድረግ ወይም ለመደገፍ “ትክክለኛ ያልሆነ ጥላቻ የተሞላበት ወይም ያለውን አቋም የሚያፈርስ መረጃ በንግግር፣ በጽሁፍ ወይም በሥዕል የበተነ ወይም ያስታወቀ እንደሆነ” በቀላል እስራት ሊቀጣ ይችላል።

ነገር ግን “አድርጎቱ ሊያስከትል ይችል የነበረው አደጋ በተለይ በጣም ከፍ ያለ እንደሆነ ከአሥር ዓመት በማይበልጥ ጽኑ እስራት ይቀጣል” ሲል የወንጅል ሕጉ ያትታል።

ዐቃቤ ሕግ አቶ ታዬ ደንደአ “መንግሥት ከኦነግ ሸኔ ጋር ሲደረግ በነበረው ድርድር ቁርጠኛ አይደለም። ድርድሩም እንዳይሳካ ምክንያት የሆነው መንግሥት ነው በሚል የሚገፋፋ እና የማሰናዳት ወንጀል ፈጽሟል” የሚል ክስ ማቅረቡን አቶ ቶሊ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

አቶ ታዬ ደንደአ በቁጥጥር ስር ከማዋላቸው ጥቂት ቀናት በፊት ከቢቢሲ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ “የዳሬሰላሙ ድረድር እንዳይሳካ ያደረገው መንግሥት ነው ብዬ አምናለሁ” ብለው ነበር።

የፌደራሉ መንግሥት እና የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት በታንዛኒያ በሁለት ዙር ያደረጓቸው ድርድሮች ያለ ውጤት መጠናቀቃቸው ይታወሳል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ሦስተኛው በአቶ ታዬ ደንደአ ላይ የቀረበው ክስ “ቤታቸው ሲበረበር አንድ ፈቃድ የሌለው ክላሺንኮቭ ጠመንጃ ከቤታቸው ተገኝቷል” የሚል መሆኑን ጠበቃ ቱሊ ተናግረዋል።

በችሎት ውሎ የዐቃቤ ሕግ ክስ በንባብ ከቀረበ በኋላ አቶ ታዬ ደንደአ ከአያያዛቸው ጋር የተያያዘ አቤቱታ ማቅረባቸውን ጠበቃ ቱሉ ገልጸዋል።

አቶ ታዬ ያቀረቡት የመጀመሪያ አቤቱታ በሕገ መንግሥቱ የተሰጣቸው ያለመከሰስ መብት ሳይነሳ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን በመጥቀስ “መብቴ ተጥሶብኛል” የሚል ነው። ከዚህ በተጨማሪም አባል የሆኑበት የኦሮሚያ ክልል ምክር ቤት ያለመከሰስ መብታቸውን ያነሳበት “አኳዃን አግባብ አይደለም የሚል ቅሬታ አንስተዋል” ሲሉ ጠበቃቸው ገልጸዋል።

ለብቻቸው መታሰራቸው የጠቀሱት አቶ ታዬ እስካለፈው ረቡዕ ሚያዝያ 16/2016 ዓ.ም. ድረስ ከጠበቆችቻው፣ ከህክምና ባለሙያዎቻቸው እና ከቤተሰቦቻቸው ጋር አለመገናኘታቸውን ለፍርድ ቤቱ ተናግረዋል።

ጠበቃ ቱሊ “ይህንን እኛም በጽሁፍም ገና አጠናክረን የምናቀርብ ነው የሚሆነው እዚህ ላይ ምርመራ እንዲካሄድለን እንፈልጋለን። ይህን የፈጸሙ አካላት የሰብዓዊ መብት ጥሰት ፈጽመዋል ብለን ስለምናምን እሳቸውም በዚያው ልክ ስለሚያምኑ ይህንን የሚመረምር አንድ ቡድን እንዲዋቀርልን እንጠይቃለን” ሲሉ ለቢቢሲ አስረድተዋል።

የአቶ ታዬ ጠበቆች በችሎቱ ውሎ የዋስትና ጥያቄ ማቅረባቸውን ጠበቃው ተናግረዋል።

“ዋስትና ሕገ መንግሥታዊ መብት ነው” ያሉት ጠበቆች “ተፈጸመ የተባለው ድርጊት እጅግ በጣም ተራ” እና “ምንም አይነት የወንጀል ይዘት የሌለው ቀላል ነገር” መሆኑን በመጥቀስ አቶ ታዬ የዋስትና መብታቸው እንዲጠበቅ መጠየቃቸው ጠበቃ ቱሊ አስታውሰዋል።

ጠበቃው አክለውም “ዐቃቤ ሕግ የቀረቡት ክሶች ተደራራቢ ናቸው ዋስትናም ያስከለክላሉ የሚሉ መከራከሪያዎች አቅርቦ ዋስትናውን ተቃውሞታል” ብለዋል።

የግራ ቀኙን ክርክር ያደመጠው ችሎት ለሚያዝያ 24/2016 ዓ.ም. ተለዋጭ ቀጠሮ በመስጠት ችሎቱ ውሎውን አጠናቅቋል። ችሎቱ ተለዋጭ ቀጠሮ የሰጠው የተከሳሽ ጠበቆች የክስ መቃወሚያ ካላቸው ለመጠባበቅ እና የዋስትና ጥያቄው ላይ ብይን ለመስጠት ነው።

አቶ ታዬ ደንደአ “መንግሥትን ለመጣል በማሴር” ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር የዋሉት ከአምስት ወራት ገደማ በፊት ታኅሣሥ 1/2016 ዓ.ም. ነበር።

አቶ ታዬ በቁጥጥር ስር ሲውሉ የፀጥታ እና የደኅንነት የጋራ ግብረ ኃይሉ “ከኦነግ ሸኔ አመራሮች እና በሽብር ወንጀል ከተጠረጠሩ ጽንፈኛ ኃይሎች ጋር ትስስር በመፍጠር መንግሥትን በአመጽ፣ በሽብር እና በትጥቅ ትግል ለመጣል ሲያሴር ተደርሶበታል” ሲል ወንጅሏቸው ነበር።

በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ኩሉ ተወልደው ያደጉት አቶ ታዬ ደንደኣ ከዚህ በፊትም በሽብር ወንጀል ተጠርጥረው ከአንዴም ሁለቴ ለእስር ተዳርገዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ በኦሮሚያ ክልል እና በፌደራል መንግሥት የተለያዩ ኃላፊነቶች ላይ ሰርተዋል። የአቶ ታዬ የመጨረሻ መንግሥታዊ ኃላፊነት የሰላም ሚኒስትር ዴኤታነት ነበር።

አቶ ታዬ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ሦስት መስመር ደብዳቤ ከስሥጣን ከተነሱ በኋላ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው፤ “የተናገሩትን እና የፃፉትን የመደመር ዕሳቤ አምኜ ተከተልኩዎት። አሁን ግን በተናገሩት የማይኖሩ ብቻ ሳይሆን በሰው ደም የሚጫወቱ አረመኔ መሆንዎን ተረድቻለሁ” ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጠንከር ባሉ ቃላት መተቸታቸው ይታወሳል።