አቶ ታዬ ደንደአ እስካሁን ድረስ ፍርድ ቤት አለመቅረባቸውን ባለቤታቸው ተናገሩ

የፎቶው ባለመብት, SM
ከሰላም ሚኒስቴር ዴኤታነት ተነስተው መንግሥትን ለመጣል ሲያሴሩ ነበር በሚል ከሳምንት ገደማ በፊት በቁጥጥር ስር የዋሉት አቶ ታዬ ደንደአ እስካሁን ድረስ ፍርድ ቤት አለመቅረባቸውን ባለቤታቸው ወ/ሮ ስንታየሁ አለማየሁ ለቢቢሲ ተናገሩ።
ወ/ሮ ስንታየሁ ባለቤታቸው በሕግ ቁጥጥር ስር ከዋሉ አንድ ሳምንት እንደሆናቸው አስታውሰው እስካሁን ድረስ ፍርድ ቤት አለመቅረባቸውን እንዲሁም ጠበቆቻቸውም እንዲያናግሯቸው እንዳልተፈቀደ ተናግረዋል።
“እስካሁን ድረስ ፍርድ ቤት አልቀረበም። በቁጥጥር ስር ከዋለ ጀምሮ እርሱን ለማናገር የሚፈልጉ ጠበቆች ብዙ ቢሆኑም እንዲያናግሩት አልተፈቀደላቸውም።”
ወ/ሮ ስንታየሁ ባለቤታቸው አቶ ታዬ ደንደአን ለማናገር “በቀን ሦስት ደቂቃ ብቻ” እንደተፈቀደላቸው ጨምረው ይናገራሉ።
“ብዙ ማናገር አይፈቀድም። ከ3 ደቂቃ ላልበለጠ ጊዜ ብቻ እንደምነህ? ሰላም ነህ? ማለት ብቻ ነው የምችለው። እርሱንም በቅጡ ሳልናገር ፖሊሶቹ ዝም እንድል ይነግሩኛል። ገና እኔ ጋር ሳይመጣ ቶሎ ጨርሱ ይላሉ” ሲሉ ያለውን ሁኔታ ያስረዳሉ።
ወ/ሮ ስንታየሁ ከቤተሰብ መካከል ለመጠየቅ የተፈቀደላቸው ሁለት ሰዎች ብቻ መሆኑን ተናግረው፣ ከዚያ ውጪ ያሉ ግን መጠየቅ አንዳልተፈቀደላቸው ጨምረው አስረድተዋል።
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በበኩሉ አቶ ታዬ ደንደአ ብቻ ሳይሆኑ፣ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከታወጀ በኋላ የተያዙ ግለሰቦች በ24 ሰዓት ውስጥ ፍርድ ቤት እንዳልቀረቡ ይናገራል።
የኢሰመኮ መብቶች ክትትል እና ምርመራ ስራ ክፍል የሪጅን ዳይሬክተር ሠላማዊት ግርማይ “አቶ ታዬ ደንደአ ብቻ ሳይሆኑ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ስር ቁጥጥር የዋሉ ብዙ ሰዎች በተመሳሳይ ሁኔታ ውስጥ ናቸው። ስለዚህ እኛ በ24 ሰዓት ውስጥ ፍርድ ቤት መቅረባቸውን ሳይሆን ስለ አያያዛቸው እና ስለ ቤተሰባቸው ነው የምንከታተለው” ብለዋል።
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በአማራ ክልል የተቀሰቀሰውን አለመረጋጋት ተከትሎ የታወጀ ሲሆን እንደ አስፈላጊነቱ በሌሎች ስፍራዎች ላይም ተግባራዊ ሊሆን እንደሚችል በወቅቱ ተገልጾ ነበር።
የአቶ ታየ ደንደአ ባለቤት ይኖሩበት ከነበረበት የመንግሥት ቤት ‘ሙሉ ንብረታቸውን ሳያወጡ እንደታሸገባቸው’ ለቢቢሲ መናገራቸው ይታወሳል።
ኢሰመኮ በበኩሉ የአቶ ታዬ ቤተሰብ ከሚኖሩበት ቤት ወጥተው ለችግር መጋለጣቸውን በማሕበራዊ ሚዲያ ላይ ማየቱን ገልጾ ለማጣራት ክትትል እያደረገ መሆኑን ለቢቢሲ ገልጿል።
የገዢው ብልጽግና ፓርቲ ከፍተኛ አባል እና የኦሮሚያ ክልል ምክር ቤት እንደራሴ የሆኑት አቶ ታዬ ደንደአ ባለፉት ጥቂት ወራት በግል የማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው እና በመገናኛ ብዙኃን ላይ በሚያንጸባርቁት ከመንግሥት አቋም በሚቃረን አስተያየታቸው መነጋገሪያ ሆነው ነበር።
ከኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ጋር ስለተካሄደው ድርድር መክሸፍ፣ ስለሙስና፣ በኦሮሚያ ክልል ስላለው ግጭት እና አዲስ አበባ ውስጥ ሊካሄድ ታቅዶ በተከለከለው ሰላማዊ ሰልፍ ዙሪያ መንግሥትን የሚተች ጠንካራ አቋም ማንጸባረቃቸውን ተከትሎ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በተጻፈ ደብዳቤ ከኃላፊነታቸው መባረራቸው ይታወቃል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለአቶ ታዬ በጻፉት ደብዳቤ ከሚኒስትርነታቸው መሰናበታቸውን ይፋ ያደረጉትን አቶ ታዬን፣ በዚያኑ ዕለት ምሽት በርካታ የፖሊስ አባላት ወደ ቤታቸው መጥተው ፍተሻ በማካሄድ ይዘዋቸው እንደሄዱ ባለቤታቸው ወ/ሮ ስንታየሁ ለቢቢሲ ገልጸው ነበር።
የፀጥታ እና ደኅንነት የጋራ ግብረ ኃይል የአቶ ታዬን በቁጥጥር ስር መዋልን በተመለከተ ባወጣው መግለጫ፣ በሽብር ቡድንነት ከተፈረጀው ሸኔ እያለ ከሚጠራው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት አመራሮች ጋር ግንኙነት በመፍጠር “መንግሥትን በአመጽ፣ በሽብር እና በትጥቅ ለመጣል” ሲያሴሩ እንደተደረሰባቸው ጠቅሷል።
ለዓመታት በእስር ላይ የቆዩት አቶ ታዬ ደንደአ በአገሪቱ የተካሄደውን ሕዝባዊ ተቃውሞን ተከትሎ ከእስር የወጡ ሲሆን፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የመሪነት መንበሩን ከያዙ በኋላ ከቅርብ ደጋፊዎቻቸው መካከል በመሆን ወደ መንግሥት ሥልጣን መምጣታቸው ይታወቃል።
አቶ ታዬ ኢህአዴግን የተካው ብልጽግና ፓርቲ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል እና የኦሮሚያ ምክር ቤት አባል ከመሆናቸው በተጨማሪ በፓርቲው፣ በኦሮሚያ ክልል እና በፌደራል መንግሥቱ ውስጥ በከፍተኛ ኃላፊነት ቦታ ላይ ሠርተዋል።
በጠቅላይ ሚኒስትሩ ባለሦስት መስመር የምስጋና ደብዳቤ ምክንያቱ ባልተገለጸ ሁኔታ ከኃላፊነታቸው አስከተነሱበት ታኅሣሥ 1/2016 ዓ.ም. ድረስም ከሁለት ዓመት በላይ ለሚሆን ጊዜ የሰላም ሚኒስቴር ሚኒስትር ዲኤታ ሆነው ሲያገለግሉ ነበር።












