በሰሜን ኢትዮጵያ ያለው ሁኔታ እንዳሳሰባቸው የአፍሪካ ኅብረት ሊቀመንበር ገለጹ

የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር ሙሳ ፋኪ ማሐማት

የፎቶው ባለመብት, @AUC_MoussaFaki

የምስሉ መግለጫ, የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር ሙሳ ፋኪ ማሐማት

በአማራ እና በትግራይ ክልሎች መካከል የይገባኛል ውዝግብ ባለባቸው አካባቢዎች ላይ እየታየ ያለው ሁኔታ በእጅጉ እንዳሳሰባቸው የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር ሙሳ ፋኪ ማሐማት ገለጹ።

ሊቀመንበሩ ባወጡት መግለጫ በሰሜን ኢትዮጵያ ራያ አላማጣ፣ ዛታ እና ኦፍላን ጨምሮ አወዛጋቢ በሆኑት አካባቢዎች ባሉ ማኅበረሰቦች መካከል “እየተባባሰ ያለውን ውጥረት” ስጋት ውስጥ ሆነው እየተከታተሉት መሆናቸውን አመልክተዋል።

የአማራ እና የትግራይ ክልሎች በይገባኛል በሚወዛገቡባቸው አካባቢዎች ካለፈው ሳምንት ጀምሮ የታጠቁ ኃይሎች እየገቡ መሆናቸውን በመግለጽ ነዋሪዎች እየሸሹ መሆናቸው መዘገቡ ይታወቃል።

ለሁለት ዓመት የቆየውን ደም አፋሳሽ ጦርነት ለማስቆም ያስቻለውን የፕሪቶሪያውን ስምምነት ተከትሎ ከአወዛጋቢዎቹ አካባቢዎች ከፌደራል መንግሥቱ ኃይሎች ውጪ ያሉ ታጣቂዎች ለቀው እንደሚወጡ የተገለጸ ሲሆን፣ ካለፈው ሳምንት ጀምሮ የተለያዩ መረጃዎች ከአካባቢዎቹ ነዋሪዎች እየወጡ ነው።

ቢቢሲ ያነጋገራቸው ነዋሪዎች እና የአካባቢዎቹ ባለሥልጣናት እንደሚሉት በከተሞች አካባቢ የፌደራል ፖሊስ እና የመከላከያ ሠራዊት አባላት መሠማራታቸውን፣ ከከተሞች ውጪ ባሉ ቦታዎች ላይ ደግሞ የህወሓት ታጣቂዎች እንደሚታዩ ገልጸዋል።

ይህንንም ተከትሎ በምሥራቅ በኩል በሚገኙት አወዛጋቢ ቦታዎቹ ይገኙ የነበሩ ነዋሪዎች በተፈጠረባቸው ስጋት ምክንያት መኖሪያቸውን ለቀው ወደ አጎራባች የአማራ ክልል አካባቢዎች መፈናቀላቸው ተነግሯል።

በዚህም ሳቢያ ከአላማጣ ከተማ፣ ዛታ እና ኦፍላ የራያ ወረዳዎች የተፈናቀሉ ሰዎች ቁጥር 50 ሺህ መድረሱን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ እርዳታ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ከቀናት በፊት አስታውቋል።

የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ህወሓት የፕሪቶሪያውን ስምምነት ሙሉ በሙሉ በመጣስ በራያ አላማጣ፣ ራያ ባላ፣ ኦፍላ፣ ኮረም እና ዛታ አካባቢዎች ላይ ወረራ ፈጽሟል ሲል ባለፈው ሳምንት ክስ ማቅረቡ ይታወሳል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር ሙሳ ፋኪ ማሐማት ባወጡት መግለጫ አዲስ እየታየ ያለውን የነዋሪዎች መፈናቀልን ለማስቆም ውጥረት ባለባቸው አካባቢዎች ያሉ ሁሉም ወገኖች “በአስቸኳይ ጠላትነትን እንዲያስወግዱ እና የሰላማዊ ሰዎችን ደኅንነት እንዲያረጋግጡ” ጥሪ አቅርበዋል።

ሊቀመንበሩ አክለውም በፌደራል መንግሥቱ እና በህወሓት መካከል ከሁለት ዓመት ገደማ በፊት ግጭትን በዘላቂነት ለማስወገድ ደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ ላይ የተደረሰው ስምምነት ተከብሮ ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ እንዲሆን ጠይቀዋል።

አክለውም በስምምነቱ ላይ እንደተመለከተው ይገባኛል የሚነሳባቸውን አካባቢዎች ጉዳይ በዘላቂነት ምላሽ ለመስጠት የሚያስችለውን ፖለቲካዊ ውይይት እንዲጀመር ጥሪ አቅርበዋል።

በተመሳሳይ በትግራይ ክልል የተቀሰቀሰውን ጦርነት ተከትሎ ወደ አማራ ክልል እንዲጠቃለሉ በተደረጉ የአላማጣ ከተማ እና ራያ ወረዳዎች እንደ አዲስ የተቀሰቀውን ግጭት ተከትሎ በአዲስ አበባ መቀመጫቸውን ያደረጉ የካናዳ፣ የፈረንሳይ፣ የጀርመን፣ የጣሊያን፣ የጃፓን፣ የዩናይትድ ኪንግደም እና የአሜሪካ ኤምባሲዎች ውጥረት እንዲረግብ ሰሞኑን ጠይቀዋል።

ኤምባሲዎቹ ሁሉም አካላት ትጥቅ በመፍታት እና መልሶ ከማኅበረሰቡ ጋር ለማዋሃድ እንዲሁም የተፈናቀሉ ዜጎችን ወደ መኖሪያ ቀያቸው ለመመለስ በሚደረጉ ጥረቶች ላይ አጽንኦት ተሰጥቶ እንዲሠራ አሳስበዋል።

በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዲሞክራሲ ግንባታ ማስተባበሪያ እና የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አደም ፋራህ ግጭቱን ተከትሎ በሰጡት አስተያየት ለአወዛጋቢ አካባቢዎቹ የፌደራል መንግሥቱ ዘላቂ መፍትሄ ለመስጠት እየሠራ መሆኑን ተናግረዋል።

የአገሪቱ የብሔራዊ የደኅንነት ምክር ቤት ከቀናት በፊት በወቅታዊ አገራዊ የደኅንነት እና የፀጥታ ጉዳዮች ዙሪያ ባወጣው መግለጫ በፕሪቶሪያው ስምምነት መሠረት የህወሓት ታጣቂዎች ትጥቅ መፍታት አለባቸው ብሏል።

እንዲሁም የማንነት እና የአስተዳደር ወሰን ጥያቄ የሚነሳባቸው አካባቢዎችን ጉዳይ “እልባት ለመስጠት እንዲቻል የተቀመጠው አቅጣጫ ተግባራዊ መደረግ አለበት” ብሏል።

ደም አፋሳሹ የሁለት ዓመት የእርስ በርስ ጦርነት ካበቃ በኋላ ትጥቅ ማስፈታት፣ የተፈናቀሉ ነዋሪዎች ወደ ቀያቸው መመለስን እና የይገባኛል ጥያቄ ላለባቸው አወዛጋቢ አካባቢዎች ዘላቂ መፍትሄ መስጠትን በተመለከተ የቀሩ ተግባራት እንዳሉ መንግሥት ገልጿል።