ከአላማጣ እና የራያ ወረዳዎች የተፈናቀሉ ሰዎች ቁጥር 50 ሺህ መድረሱን ተመድ አስታወቀ

የአላማጣ ከተማ

የፎቶው ባለመብት, ALAMATA COMM

ግጭት ከተነሳባቸው የአላማጣ ከተማ፣ ዛታ እና ኦፍላ የራያ ወረዳዎች የተፈናቀሉ ሰዎች ቁጥር 50 ሺህ መድረሱን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ እርዳታ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

ተፈናቃዮቹ የተጠለሉባቸውን የዞን ባለሥልጣናት ዋቢ አድርጎ ጽህፈት ቤቱ ሰኞ ሚያዝያ 14/2016 ዓ.ም. ባወጣው ሪፖርት መሠረት ከተፈናቃዮቹ መካከል 42 ሺህ የሚሆኑ በሰሜን ወሎ በምትገኘው ቆቦ ከተማ እንዲሁም 8300 የሚሆኑት ደግሞ በሰቆጣ እና ዋግ ኽምራ ዞኖች ተጠልለዋል ብሏል።

በአብዛኛው ሴቶች፣ ህጻናት፣ ታዳጊዎች እና አረጋውያንን ያሉበት ተፈናቃዮች በማኅበረሰቡ ባሉ ቤቶች ለመጠለል እየሞከሩ እንደሆነ ገልጾ፣ ሌሎች ደግሞ ከቆቦ ከተማ ሦስት ኪሎ ሜትር ርቀት በሚገኝ ጋራ ሌንጫ በተሰኘው የኢንዱስትሪ መንደር ክፍት ቦታ ላይ ተጠልለው ይገኛሉ ተብሏል።

በዚህ ስፍራ የተጠለሉ ተፈናቃዮች በአስቸጋሪ ሁኔታ ለበልግ ዝናብ መጋለጣቸውን የጠቀሰው የመንግሥታቱ ድርጅት መግለጫ የተወሰኑትን ተፈናቃዮች ወደ ሌላ ስፍራ ለማዘዋወር እየተሞከረ እንደሆነ መሬት ላይ ያሉ አጋሮቹን ዋቢ አድርጓል ጠቅሷል።

የፌደራል ኃይሎች ጣልቃ መግባታቸውን ተከትሎ በአላማጣ፣ ወልዲያ እና ቆቦ ከተሞች አካባቢ ከትናንትና ሚያዝያ 14/ 2016 ዓ.ም ጀምሮ የፀጥታው ሁኔታ የተረጋጋ መሆኑም ተገልጿል።

ከአላማጣ ወደ ቆቦ የሚወስደው እንዲሁም ከአላማጣ ወደ ማይጨው የሚወስዱ መንገዶች ለትራንስፖርት ክፍት መሆናቸውን እንዲሁም ባንክን የመሳሰሉ ሕዝባዊ አገልግሎቶች እንደገና ሥራ መጀመራቸው ተጠቁሟል።

በትግራይ ክልል የተቀሰቀሰውን ጦርነት ተከትሎ ወደ አማራ ክልል እንዲጠቃለሉ በተደረጉ የአላማጣ ከተማ እና ራያ ወረዳዎች እንደ አዲስ የተቀሰቀውን ግጭት ተከትሎ በአዲስ አበባ መቀመጫቸውን ያደረጉ የካናዳ፣ ፈረንሳይ፣ ጀርመን፣ ጣሊያን፣ ጃፓን፣ ዩናይትድ ኪንግደም፣ አሜሪካ ኤምባሲዎች ውጥረት እንዲረግብ ጥሪ አቅርበዋል።

ኤምባሲዎቹ ሁሉም አካላት ትጥቅ በመፍታት እና መልሶ ከማኅበረሰቡ ጋር ለማዋሃድ እንዲሁም የተፈናቀሉ ዜጎችን ወደ መኖሪያ ቀያቸው ለመመለስ የሚደረጉ ጥረቶች ላይ አጽንኦት ተሰጥቶ እንዲሰራ አሳስበዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ኤምባሲዎቹ ውጥረቱ እንዲረግብ እና ለሰላማዊ ዜጎችን ጥበቃ ጥሪ ባደረጉበት በዚህ መግለጫ “በአካባቢው የሚስተዋሉ ውስብስብ የፖለቲካ እና የፀጥታ ችግሮችን ለመፍታት እና የኢትዮጵያን ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥ ባለድርሻ አካላትን ያካተተ ሁሉን አቀፍ ንግግር ብቸኛው መንገድ” ነው ብለዋል።

ባለፉት ሳምንታት የራያ አላማጣ አካባቢዎች እንደ አዲስ ግጭት መቀስቀሱን ተከትሎ የተለያዩ አወዛጋቢ ሪፖርቶች ወጥተዋል።

ጦርነቱን ተከትሎ በአማራ ከልል ስር የተጠቀለሉት የአካባቢው አስተዳደራዊ መዋቅሮች ሙሉ በሙሉ መፍረሳቸው የተነገረ ሲሆን፣ የአላማጣ ከተማ በመከላከያ ሠራዊት እና በፌደራል ፖሊስ ቁጥጥር ስር ከሚያዝያ 7/2016 ዓ.ም. ጀምሮ መሆኑን የከተማዋ ከንቲባ ተናግረው ነበር።

በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዲሞክራሲ ግንባታ ማስተባበሪያ እና የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አደም ፋራህ ግጭቱን ተከትሎ በሰጡት አስተያየት "የይገባኛል ጥያቄዎች" የሚነሳባቸውን አካባቢዎች በተመለከተ “በሕግ እና በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ከስምምነት ላይ የተደረሰበት በመሆኑ ለመርኅ ተገዢ መሆን ያስፈልጋል” ብለዋል።

“የይገባኛል ጥያቄ የሚነሳባቸው አካባቢዎች ችግር ሰላማዊ፣ ሕጋዊ እና የሕዝብ ወሳኝነትን ባረጋገጠ አኳኋን መፍትሄ የሚያገኝበትን ሁኔታ ለመፍጠር ውይይቶች ተደርገዋል፤ ስምምነት ላይ ተደርሷል። በዚያ መንገድም የፌደራል መንግሥት ለመፈጸም የተለያዩ ዝግጅቶች እና ሥራዎችን እየሠራ ነው” ሲሉ አቶ አደም በብልፅግና ማኅበራዊ ሚዲያ ገጽ ላይ በቀረበው መግለጫ ተናግረዋል።

ከዚህ ውጪ የሚደረጉ ግጭቶችም ሆነ ትንኮሳዎች ተቀባይነት የላቸውም ያሉት አቶ አደም፣ ሁሉም አካላት ለፕሪቶሪያው ስምምነት ተገዢ መሆን እንዳለባቸው ገልጸው በስምምነቱ መሠረትም “የሕዝብን የሥልጣን ባለቤትነንት ባረጋገጠ መልኩ” ተፈጻሚ ይሆናል ብለዋል።

የፕሪቶሪያን ስምምነት ተከትሎ ተግባራዊ ካልሆኑ ጉዳዮች አንዱ ተፈናቃዮችን ወደ ቀያቸው የመመለስ ጉዳይ እንደሆነ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ምክትል ርዕሰ መስተዳደር ጄኔራል ታደሠ ወረደ ከሰሞኑ ተናግረው ነበር። በቅርቡ በአፍሪካ ኅብረት አማካኝነት በተደረገው ውይይትም ከፌደራል መንግሥቱ ጋር መግባባት ላይ እንደተደረሰም ገልጸዋል።

መግባባት ላይ ተደርሶባቸዋል ካሏቸው ጉዳዮችም መካከል “ተፈናቃዮችን ለመመለስ በዋነኝነት በደቡብ እና ምዕራብ ትግራይ የተቋቋሙ ሕገወጥ አስተዳደሮችን ማፍረስ፤ የተደራጁ ታጣቂዎችን ቡድኖችን መበተን” ሌሎች ጉዳዮች ተፈጻሚ እንደሚሆኑም ጠቅሰዋል።

ከሰሞኑ በተነሳው ግጭትም የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ህወሓት የፕሪቶሪያውን ስምምነት ሙሉ በሙሉ በመጣስ አራተኛ ዙር ወረራ በሕዝብ በላይ ፈጽሟል ሲል ከሷል።

የክልሉ መንግሥት ግጭቱን ተከትሎ ባወጣው መግለጫው “ከትናንት ታሪካዊ ስህተቱ መማር የተሳነው ህወሓት የፕሪቶሪያውን ስምምነት ሙሉ በሙሉ በመጣስ ለአራተኛ ዙር ሕዝባችን ላይ ወረራ ፈፅሟል” ብሏል።

ክልሉ ይህንን ያለው ካለፈው ሳምንት ማብቂያ ጀምሮ በአላማጣ እና ራያ አካባቢዎች ለቀናት የዘለቀ የተኩስ ልውውጥ ከተካሄደ በኋላ በከተሞች አካባቢ የመከላከያ እና የፌደራል ፖሊስ በዙሪያቸው ደግሞ የህወሓት ታጣቂዎች ገብተዋል የሚሉ ሪፖርቶች መውጣታቸውን ተከትሎ ነው።

የክልሉ መንግሥት ሕወሓት ወረራ የፈፀመባቸው የራያ አላማጣ፣ ራያ ባላ፣ ኦፍላ፣ ኮረም እና ዛታ መሆናቸውን በመግለጽ የክልሉ ሕዝብ፣ የፌደራል መንግሥቱ እና ዓለም አቀፍ ኅብረተሰብ ድርጊቱን እንዲያስቆሙ ጥሪ አቅርቧል።

የአማራ እና የትግራይ ክልሎች የይገባኛል ጥያቄ በሚያነሱባቸው አካባቢዎች ያሉ አስተዳደሮች በፌደራል መንግሥቱ እንዲፈርሱ እንደሚደረግ የመከላከያ ሚኒስትሩ ዶ/ር አብርሃም ከዚህ ቀደም መግለጻቸው ይታወሳል።

ሚኒስትሩ ባለፈው ዓመት የአሸንዳ በዓልን ምክንያት በማድረግ በይፋዊ የፌስቡክ ገጻቸው ላይ በትግርኛ ባሰፈሩት ሰፋ ያለ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት “በአካባቢዎቹ ቀደም ሲል የተፈጠረውን ሁኔታ በመጠቀም የተቋቋሙ አስተዳደሮች እንዲፈርሱ” እንደሚደረግ እና በአካባቢዎቹ ከፌደራል የፀጥታ ኃይሎች ውጭ የታጠቀ ኃይል አንዳይኖር እንደሚደረግ አስፍረው ነበር።