አላማጣ እና ኮረም ከተሞች እንዴት እየሰነበቱ ነው?

የፎቶው ባለመብት, alamata comm.
የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነትን ተከትሎ በአማራ ክልል ስር ሲተዳደሩ የቆዩት የራያ አካባቢዎች ያለ አስተዳዳሪ ወደ ሁለተኛ ሳምንታቸው እየተሻገሩ ነው።
ከየካቲት ጀምሮ አልፎ አልፎ ሲከሰት የነበረው “በህወሓት ታጣቂዎች” እና “በአካባቢው ሚሊሺያዎች” መካከል ሲደረግ የነበረው የተኩስ ልውውጥ ከሚያዝያ 5/2016 ዓ.ም. ጀምሮ ከፍ ባለ ሁኔታ ተካሂዶ ከሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ወዲህ የነበረውን መዋቅር ቀይሮታል።
ላለፉት ሦስት ዓመት ገደማ አካባቢዎቹን ሲመሩ የነበሩት ከአማራ ክልል በኩል የተሾሙ አስተዳዳሪዎች፤ ከሚመሯቸው የራያ ወረዳ እና ከተሞች ሸሽተው ቆቦ ከተማ እና ሌሎች አጎራባች አካባቢዎች ውስጥ ተጠልለዋል።
በቆቦ ከተማ የሚገኙት ከራያ አካባቢዎች የሸሹት የመንግሥት ሹመኞች ብቻ አይደሉም።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ እርዳታ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት (ኦቻ) በዚህ ሳምንት መጀመሪያ በወጣው ሪፖርት 50 ሺህ ሰዎች ከራያ ወረዳ እና ከተማ አስተዳደሮች እንደተፈናቀሉ አስታውቋል። ከተፈናቃዎቹ ውስጥ 42 ሺህ ያህሉ የሚገኙት በሰሜን ወሎ ዞን ስር በምትገኘው ቆቦ ከተማ እንደሆነ ጽህፈት ቤቱ ገልጿል።
ሌሎች የራያ አካባቢዎች ነዋሪዎች ግን አሁንም ባሉበት ኑሯቸውን ቀጥለዋል።
አስተዳዳሪ የሌላቸው ከተሞች
የአማራ እና ትግራይ ክልሎች የየራሳቸው አስተዳዳሪዎች የተሾሙላቸው የአላማጣ እና የኮረም ከተሞች ያለምንም አስተዳዳሪ ከቀሩ ሁለት ሳምንታት ተቃርበዋል። ከሁለቱም ክልሎች የተሾሙ አመራሮች የሚገኙት በየክልላቸው ውስጥ በሚገኙ አጎራቦች አካባቢዎች ውስጥ ነው።
በአላማጣ እና ኮረም ከተማዎች ውስጥ የፌደራል እና የመከላከያ ሠራዊት አባላት እንደሚገኙ ቢቢሲ ያነጋገራቸው የሁለቱ ከተማዎች አምስት ነዋሪዎች ተናግረዋል። በከተሞቹ ውስጥ የሚገኙት የፌደራል መንግሥት እንዲሁም የአካባቢ አስተዳደሮችን ተቋማት እና ቢሮዎች እየጠበቁ ያሉት በሁለቱ የፀጥታ አካላት መሆኑን ነዋሪዎች ገልጸዋል።
ቢቢሲ ያነጋገራቸው የአላማጣ ከተማ ነዋሪዎች በአሁኑ ሰዓት ከተማዋ ውስጥ አንጻራዊ ሰላም እንዳለ ጠቅሰዋል። ባንኮች፣ የኢትዮ ቴሌኮም ቢሮዎች እንዲሁም የተወሰኑ መደብሮች መከፈታቸውን ሦስት ነዋሪዎች ተናግረዋል።
በከተማዋ ውስጥ የሚገኙ አንዳንድ መደብሮች ያልተከፈቱት አካባቢዎቹን ላይ አስተዳዳሪ አለመኖሩ በፈጠረባቸው ስጋት ምክንያት መሆኑን የሚናገሩ አንድ የአላማጣ ነዋሪ፤ በከተማዋ ውስጥ የሚገኙት የፌደራል ፖሊስ እና የመከላከያ ሠራዊት አባላት እየተንቀሳቀሱ ያሉት በዋና የአስፓልት መንገዶች ላይ እንደሆነ አስረድተዋል።
ከትግራይ ክልል በኩል የተሾሙት የአላማጣ ከተማ ከንቲባ አቶ ዝናቡ ደስታም በተመሳሳይ በከተማዋ ሁለቱ የፌደራል መንግሥት ኃይሎች ቢኖሩም የፀጥታ ሁኔታው በበቂ ሁኔታ እየተሸፈነ አለመሆኑን ለቢቢሲ ተናግረዋል።
በአማራ ክልል በኩል የተሾሙት የአላማጣ ከንቲባ አቶ ኃይሉ አበራ በበኩላቸው የመከላከያ ሠራዊት እና ፌደራል ፖሊስ አባላት ከተማዋ ውስጥ መኖራቸውን አንስተው በአሁኑ ሰዓት ስላለው ሁኔታ ግን “ዝርዝር መረጃ” እንደሌላቸው ጠቅሰዋል።
ነዋሪዎች ያሉበት ሁኔታ
ባለፈው ሳምንት መጀመሪያ የመንግሥት ኃላፊዎች ከአላማጣ መውጣታቸውን ተከትሎ በመንግሥት ተቋማት ደረጃ የሚሰጡ አገልግሎቶች እስካሁን ድረስ እንደቆሙ መሆኑን ሦስት ነዋሪዎች ገልጸዋል። የከተማዋ አስተዳደር መሥሪያ ቤቶች፣ ትምህርት ቤቶች እና የጤና ተቋማት አገልግሎት እየሰጡ እንዳልሆነም ጠቅሰዋል።
አንድ የከተማዋ ነዋሪ*፤ “[የጤና አገልግሎት] የለም ማለት ይቻላል። አሁን በቅርብ አንዲት ወላድ ነበረች፤ ደም [ያስፈልጋል] ተብላ ወደ ወልዲያ ሄዳለች። ምንም ዓይነት አገልግሎት የለም። በጣም ተቸግራ እዚህ ያሉ ዶክተሮች በግል ተባበሯት፤ …ወደ ቆቦ በትራንስፖርት ሄዳ፣ ከቆቦ ወደ ወልዲያ ወሰዷት” ሲል በከተማዋ ላለው ሁኔታ ማሳያ ጠቅሷል።
በኮረም ከተማም በተመሳሳይ የመንግሥት አገልግሎት ሰጪ መሥሪያ ቤቶች ዝግ መሆናቸውን ሦስት የከተማዋ ነዋሪዎች ለቢቢሲ ተናግረዋል። የቀድሞ አስተዳዳሪዎች ለቀው በወጡባት ኮረም ከተማም የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች እና ተቋማት እየተጠበቁ ያሉት በፌደራል ፖሊስ እና በመከላከያ ሠራዊት አባላት መሆኑን ተናግረዋል።
ይሁንና ከአላማጣ ከተማ በተለየ መልኩ የትግራይ ክልል ታጣቂዎች በከተማዋ ውስጥ እንደሚንቀሳቀሱ ሦስት ነዋሪዎች ገልጸዋል። ቢቢሲ ያነጋገራቸው ነዋሪዎች ታጣቂዎቹ በከተማዋ ነዋሪዎች ላይ “ዝርፊያ ፈጽመዋል” ሲሉ ከሰዋል።
ታጣቂዎቹ የሰፈሩት በከማው ውስጥ በሚገኙት ስድስት ትምህርት ቤቶች ውስጥ መሆናቸውን የሚናገሩ አንድ ነዋሪ፤ “የትምህር ቤት መጽሐፍት ‘የአማራ ክልል ናቸው’ በሚል ተቀድደዋል” ሲሉ በትግራይ ታጣቂዎች ተፈጽሟል ያሉትን ድርጊት ጠቅሰዋል።
ሌላ ነዋሪ በበኩላቸው፤ በከተማዋ ውስጥ በታጣቃዎቹ በሚፈጸሙት ድርጊቶች ሳቢያ ነዋሪዎች አሁንም ወደ ቆቦ ከተማ እየሸሹ መሆኑን ተናግረዋል። በቆቦ ከተማ የሚገኙት በአማራ ክልል የተሾሙት የአላማጣ ከተማ ከንቲባ አቶ ኃይሉም የኮረም ከተማ ነዋሪዎች አሁንም ወደ ቆቦ ከተማ እየገቡ መሆኑን ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።
የታጣቂዎች እንቅስቃሴ
በትግራይ ክልል በኩል የራያ አካባቢ ወረዳ እና ከተማዎችን በስሩ የያዘው የደቡባዊ ትግራይ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሀፍቱ ኪሮስ፤ በኮረም ከተማ የትግራይ ክልል ታጣቂዎች ገብተዋል ስለመባሉ እና ታጣቂዎቹ ፈጽመዋቸዋል ስለተባሉ ድርጊቶች ከቢቢሲ ጥያቄ ቀርቦላቸዋል።
በአሁኑ ሰዓት በኮረም “በጣም የተረጋጋ ሰላም እና ደኅንነት” መፈጠሩን የሚናገሩት ዋና አስተዳዳሪው፤ “ኮረም እና አላማጣም ላይ በአሁኑ ሰዓት የፌደራል ኃይሎች የፀጥታ እና ሰላሙን የመጠበቅ ሥራ በከፍተኛ ሁኔታ እየፈጸሙ ነው” ብለዋል።
አቶ ሀፍቱ፤ የትግራይ ክልል ታጣቂዎች በከተማዋ ስለመግባታቸው እና በትምህርት ቤቶች ውስጥ ስለ መስረፈራቸው ማረጋገጫ ከመስጠትም ሆነ ከማስተባበል ተቆጥበዋል።
እንደ ራያ ባሉ አካባቢዎች ላይ ከዚህ ቀደም በፌደራል መንግሥት እና በትግራይ ክልል ጊዜያዊ መስተዳደር መካከል የነበረው “ከመከላከያ ሠራዊት ውጪ ሌላ ታጣቂ ኃይል አይኑር” የሚለው “ንግግር” በአሁኑ ሰዓት “መቀየሩን” ዋና አስተዳዳሪ ገልጸዋል።
የፕሪቶሪያ ስምምነትን የተፈራረሙት የፌደራል መንግሥቱ እና ህወሓት ከስምምነቱ በታች ያሉ ጉዳዮችን በፖለቲካዊ ንግግር እየፈቱ እና “እያሻሻሉ” እየሄዱ መሆኑን የሚናገሩት አቶ ሀፍቱ፤ “ለምሳሌ አሁን ማሻሻያዎች አሉ። በዚያ አካባቢ ከመከላከያ ሠራዊት እና ከፌደራል ፖሊስ ውጪ ማንኛውም ታጣቂ መኖር የለበትም የሚል የውይይት ሀሳብ እንደነበር ይታወቃል። አሁን እሱ ተቀይሯል። ሌላ እድገት አለው” ብለዋል።
ዋና አስተዳዳሪው “ተቀይሯል” ያሉት የታጣቂዎች ጉዳይ የሚወያዩት አካላት ይፋ እንደሚያደርጉት በመጥቀስ ዝርዝሩን ከመናገር ተቆጥባዋል።
ሁለቱ ክልሎች በሚወዛገቡባቸው አካባቢዎች ባለፉት ሳምንታት የተፈጠረውን ሁኔታ የአፍሪካ ኅብረት እና በኢትዮጵያ የሚገኙ የተለያዩ አገራት ተወካዮች እንዳሰሰባቸው እና ሁሉም ወገኖች ከግጭት እንዲቆጠቡ አሳስበዋል።
የአማራ እና የትግራይ ክልሎች በይገባኛል በሚወዛገቡባቸው አካባቢዎች ላይ የህወሓት ታጣቂዎች ወረራ ፈጽመዋል ብሎ ባለፈው ሳምንት የአማራ ክልል መንግሥት መክሰሱ ይታወሳል።
ለወሰን እና ለማንነት ጉዳዮች መፍትሄ ለመስጠት እየሠራ መሆኑን የገለጸው የፌደራል መንግሥቱ የህወሓት ኃይሎች ትጥቅ መፍታት አለባቸው ሲል ከቀናት በፊት ባወጣው መግለጫ አመልክቷል።
*ለዚህ ዘገባ ቢቢሲ ያነጋገራቸው ነዋሪዎች ለደኅንነታቸው ስጋት ስላላቸው ስማቸው እንዲጠቀስ አልፈቀዱም












