ክሪስቲያኖ ሮናልዶ ሜዳ ላይ ባሳየው ድርጊት ምክንያት ተቀጣ

ክሪስቲያኖ ሮናልዶ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የአል-ናስር አጥቂው ክሪስቲያኖ ሮናልዶ ሜዳ ላይ ባሳየው ድርጊት ምክንያት የአንድ ጨዋታ ቅጣት ተላለፈበት።

በሳዑዲ ፕሮ ሊግ የሚጫወተው ሮናልዶ “ደጋፊዎችን በመቀስቀስ” በሚል ነው የተቀጣው።

ሮናልዶ ቡድኑ አል-ናስር ከአል-ሸባብ ጋር ሲጫወት የሸባብ ደጋፊዎችን ለማበሳጨት ባሳየው ምልክት ምክንያት አንድ ጨዋታ ያመልጠዋል።

የአል ሸባብ ደጋፊዎች “ሜሲ፤ ሜሲ” እያሉ የሮናልዶን የረዥም ጊዜ ተፎካካሪ ለማብሸቅ ሞክረዋል።

መዲናዋ ሪያድ የተደረገውን ጨዋታ አል-ናስር 3-2 አሸንፏል።

የ39 ዓመቱ የፖርቹጋል አጥቂ ክሪስቲያኖ ሮናልዶ እጁን ተጠቅሞ ለደጋፊዎች ባሳየው ምልክት አሳይቷል።

በተጨማሪ የሳዑዲ አረቢያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ተጫዋቹ 30 ሺህ የሳዑዲ ሪያል እንዲከፍል ፈርዶበታል።

ገንዘቡ ወደ ፓውንድ ሲመነዘር 6300 ገደማ ይሆናል።

የፌዴሬሽኑ የዲስፕሊን እና ሥነ-ምግብር ኮሚቲ እንዳለው ሮናልዶ የተወሰነበት ውሳኔ አሜን ብሎ ከመቀበል ባለፈ ይግባኝ መጠየቅ አይችልም።

በጨዋታው ሮናልዶ የመጀመሪያዋን ጎል በማስቆጠር ቢጀምር አል-ሸባብ ሁለት ጊዜ ከመመራት ተነስተው 2 አቻ ሆነዋል። ነገር ግብ በ87ኛው ደቂቃ ታሊስካ ባስቆጠራት ጎል አል-ናስር ባለድል ሆኗል።

ሮናልዶ፤ በነፃ ዝውውር ከማንቸስተር ዩናይትድ አል-ናስርን የተቀላቀለው በአውሮፓውያኑ ታኅሣሥ 2022 ነው።

ተጫዋቹ በዓለማችን እጅግ ከፍተኛውን ደሞዝ የሚያገኝ እግር ኳስ ተጫዋች እንደሆነ ይታመናል።

በያዝነው የውድድር ዘመን በ22 የሊግ ጨዋታዎች 20 ጎሎች ለቡድኑ ያስቆጠረ ሲሆን፤ አል-ናስር በሳዑዲ ፕሮ ሊግ ከአል-ሂላል ቀጥሎ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።

ሮናልዶ አል-ናስርን ከተቀላቀለ በኋላ በሁሉም ውድድሮች በ48 ጨዋታዎች 42 ጎሎች አስቆጥሯል።