አንጋፋው የአሜሪካ የምክር ቤት አባል በግብፅ ወኪልነት አዲስ ክስ ቀረበባቸው

ሴናተር ሮበርት ሜንዴዝ

የፎቶው ባለመብት, GETTY IMAGES

የአሜሪካ ሕግ መወሰኛ ምክር ቤት የውጭ ግንኙነት ቋሚ ኮሚቴ ሊቀ መንበር የነበሩት ቦብ ሜኔንዴዝ በግብፅ ወኪልነት አዲስ ክስ ቀረበባቸው።

አንጋፋው የምክር ቤት አባል ቦብ ሜኔንዴዝ ከዚህ ቀደም የግብፅ መንግሥትን ለመደገፍ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ዶላር ጉቦ ተቀብለዋል በሚል የሙስና ክስ ተከፍቶባቸዋል።

ሜኔንዴዝ እና ባለቤታቸው ናዲን የግብፅ መንግሥትን የረዱ “የአሜሪካ መንግሥት ምሥጢራራዊ መረጃ” አሳልፎ በመስጠት ነው ክስ የተመሠረተባቸው።

ጥንዶቹ ከሳምንታት በፊት በአሜሪካ የፍትሕ መንግሥት መሥሪያ ቤት የቀረበባቸውን የሙስና ክስ ጥፋተኛ አይደለንም ብለዋል።

ሴናተሩ ክሱን “ሐሰት” በማለት አስተባብለዋል።

የሴናተሩን ተጽዕኖ በመጠቀም አሜሪካ ለግብፅ የምትሰጠውን እርዳታ እና ወታደራዊ ድጋፍ ለመጨመር በተያዘው ዕቅድ መሠረት የገንዘብ፣ የወርቅ፣ የቤት ብድር ድጋፍ፣ የቅንጦት መኪና ከሦስት የኒው ጀርሲ ነጋዴዎች በመቀበል ወንጀል ዐቃቤ ሕግ ሜኔንዴዝ እና ባለቤታቸው ናዲን ላይ ክስ መሥርቷል።

ባለፈው ዓመት በኒው ጀርሲ የሚገኘው የሴናተሩ መኖሪያ ቤት ላይ በተደረገው ፍተሻ መርማሪዎች 480,000 ዶላር እና 155,000 ዶላር የሚገመት ጠፍጣፋ ወርቅ ተደብቆ አግኝተዋል።

ሐሙስ ዕለት በኒው ዮርክ የፌደራል ዐቃብያነ ሕጎች የቀረበው አዲስ ክስ ሜኔንዴዝ “ተጽእኗቸው እና ሥልጣናቸውን በመጠቀም የግብፅን መንግሥት በሚጠቅም መልኩ ኃላፊነታቸውን አላግባብ ተጠቅመዋል” ብሏል።

አሁን ከኃላፊነት ከተነሱበት የሴኔቱ የውጭ ግንኙነት ኮሚቴ ለግብፅ እንዳይሰጥ ተይዞ ነበረ 300 ሚሊዮን ዶላር ዕርዳታ እንዲለቀቅ ሴናተሮችን አበረታተዋልም ተብሏል።

የአሜሪካ መንግሥትን ምሥጢራዊ መረጃንም አሳልፈው ሰጥተዋል ሲል ዐቃቤ ሕግ ገልጿል።

በተጨማሪም ሜኔንዴዝ እና ባለቤታቸው ናዲን ከግብፅ ባለሥልጣናት ጋር በዋሽንግተን ዲሲ ውስጥ ’ስቴክ’ ሲመገቡ የተነሱትን አዳዲስ ፎቶዎች አካቷል።

ሚስታቸው ናዲንም “የእኔ ፍቅር [ሜኔንዴዝ] ሌላ ምን ሊያግዛችሁ ይችላል?” ማለታቸውንም ዐቃቤ ሕግ አክሏል።

ጥንዶቹ ባለፈው ወር ሦስት ክሶች የተመሠረቱባቸው ሲሆን እነዚህም ጉቦ ለመፈጸም በማሴር፣ አገልግሎት ለማጭበርበር በማሴር እና ሥልጣናቸውን አላግባብ በመጠቀም ገንዘብ ለማግኘት የሚሉ ናቸው።

ከአውሮፓውያኑ 2006 ጀምሮ በአሜሪካ የምክር ቤት አባልነት ያገለገሉት የ69 ዓመቱ ሜኔንዴዝ ባወጡት መግለጫ ከአዲሱ ክስ ራሳቸውን ተከላክለዋል።

“በክስ ላይ አዲስ ክስ መደራረብ ክሱን እውነት አያደርገውም። በሕይወቴ በሙሉ ታማኝነቴ ለአንድ አገር፣ እሱም ለአሜሪካ ብቻ ነው” ሲሉ አክለዋል።

ውዝግብ ውስጥ የገቡት ሜኔንዴዝ የኒው ጀርሲ ሴናተር ኮሪ ቡከርን ጨምሮ ከ30 በላይ የዲሞክራት ፓርቲ የምክር ቤት አባላት ከአባልነታቸው እንዲለቁ ጠይቀዋቸዋል።

የፔንሲልቬንያው የምክር ቤት አባል ጆን ፌተርማን አዳዲሶቹን ክሶች ተከትሎ ሜኔንዴዝ ከሕግ መወሰኛው ምክር ቤት እንዲባሩ ውሳኔ እንዲሰጥ ጠይቀዋል።

ፌተርማን በሰጡት መግለጫ “በአሜሪካ ሕግ መወሰኛ ምክር ቤት ውስጥ ተጠርጣሪ የውጭ ወኪል ሊኖረን አይገባም” ብለዋል።