"የአማድ ዲያሎ ደርቢ" - ማንቸስተር ዩናይትድ በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ሲቲን አሸነፈ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ማንቸስተር ዩናይትድ በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ሁለት ጎል በማስቆጠር ድራማዊ በሆነ መንገድ ማንቸስተር ሲቲን በሜዳው ረትቶታል።
ብዙ የጎል ሙከራዎች ባልታዩበት ፍልሚያ ጃስኮ ግቫርዲዮል በመጀመሪያው አጋማሽ ባስቆጠራት ጎል ሲቲ እየመራ ቆይቶ ሶስት ነጥቡን ያገኛል ተብሎ ሲጠበቅ ነው ይህ የሆነው።
የጨዋታው ኮከብ የነበረው አማድ ዲያሎ 88ኛው ደቂቃ ላይ መጠለፉን ተከትሎ የተገኘውን የፍፁም ቅጣት ምት ብሩን ፈርናንዴዝ ወደ ጎል በመቀየር አቻ እንዲሆኑ አስቻለ።
ሲቲዎች እንደገና ተደራጅተው ለማጥቃት ቢሞክሩም አማድ ዲያሎ ጠባብ ከሚባል ቦታ አስደናቂ ጎል በማስቆጠር ዩናይትድ ባለድል እንዲሆን አስችሏል።
አሰልጣኝ ሩበን አሞሪም አሌሀንድሮ ጋርናቾ እና ማርከስ ራሽፈርድን ሳይዙ ነው ወደ ኢቲሀድ ያቀኑት።
ሜሰን ማውንት በ14ኛው ደቂቃ በጉዳት ምክንያት ከሜዳ ወጥቶ በኮቢ ሜይኑ ተተክቷል።
ብሩን ፈርናንዴዝ ጨዋታው ሊጠናቀቅ 17 ደቂቃዎች ሲቀሩት ያገኘውን ጥሩ ዕድል ባለመጠቀሙ ቆጭቶት እንደነበር ተናግሯል።
በሁለት ደቂቃዎች ውስጥ ሁኔታዎች ተገለባብጠው የሲቲ ደጋፊዎች በዝምታ ሲዋጡ የዩናይትድ ደጋፊዎች ደግሞ ደስታቸውን ሲገልፁ ታይተዋል።
ሁለቱም ቡድኖች በውጤት ቀውስ ውስጥ የሚገኙ እና ሶስት ነጥብ የሚያስፈልጋቸው ናቸው። ነገር ግን ጨዋታው ብዙም አስደናቂ የሚባል እና በሙከራዎች የታጀበ አልነበረም።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
አዲሱ አሰልጣኝ ሩበን አሞሪም በድሉ ምክንያት አዲስ መነቃቃት ያገኙ ይመስላል። የቢቢሲ ስፖርት ተንታኙ ዳኒ መርፊ የእሑድ ምሽቱን ጨዋታ "የአማድ ዲያሎ ደርቢ" ብሎታል።
ዩናይትድ ከሲቲ ይህ ነው የሚባል አደጋ ባይደገንባቸውም ቀያይ ሰይጣኖቹ የራቸውን ዕድል ለመፍጠር ተስኗቸው እንደነበር ታይቷል።
በ88ኛው ደቂቃ የሲቲው ማቲያስ ኑኔዝ ለግብ ጠባቂው የላከውን ኳስ የቀማው አማድ ዲያሎ በፍፁም ቅጣት ምት ክልል ውስጥ በኑኔዝ ተጠልፎ በመውደቁ ነው ዳኛው ለዩናይትድ ፍፁም ቅጣት ምት የሰጡት።
ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች በአርሰናል እና በኖቲንግሀም ፎረስት የተረታው የአሞሪም ቡድን በአስደናቂ ሁኔታ ድል መጎናፀፉ መነቃቃት እንደሚፈጥር ብዙዎች ይናገራሉ።
ሲቲ በሁሉም ውድድሮች ባለፉት 11 ጨዋታዎች 1 ጨዋታ ብቻ ነው ማሸነፍ የቻለው።
የሲቲው አሰልጣኝ ፔፕ ጉዋርዲዮላ "እኔ ብቁ አይደለሁም"ሲል ኃላፊነት እንደሚወስድ ተናግሯል። "እኔ አለቃ ነኝ፤ አሰልጣኝ ነኝ። መፍትሔ መፈለግ ሲገባኝ እሱን ማድረግ አልቻኩም" ብሏል።
የዩናይትዱ አሰልጣኝ ሩበን አሞሪም በበኩሉ "ትልቅ ሥራ ነው የሠራነው። በእምነት ነው የተጫወትነው" ሲል በተጫዋቾቹ ያለውን መተማመን ተናግሯል።
የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግን ሊቨርፑል አንድ ቀሪ ጨዋታ እያለው በ36 ነጥብ ሲመራ እሑድ ምሽት ብሬንትፈርድን የረታው ቼልሲ በ34 ይከተላል። አርሰናል በ30 ነጥብ ሶስተኛ ነው።
ካለፉት ስድስት ጨዋታዎች በአራቱ የተረታው ማንቸስተር ሲቲ በ27 ነጥብ አምስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። ማንቸስተር ዩናይትድ በ22 ነጥብ 13ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።












