ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ትራምፕ፤ ባራክ እና ሚሼል ኦባማን ዝንጀሮ አድርጎ የሚያሳይ ዘረኛ ቪድዮ በገጻቸው ከለጠፉ በኋላ አጠፉ
ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ፤ የቀድሞ ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ እና ቀዳማዊት እመቤት ሚሼል ኦባማን እንደ ዝንጀሮ አድርጎ የሚያሳይ ይዘት ያለውን ዘረኛ የማኅበራዊ ሚዲያ ቪድዮ ገጻቸው ላይ ከለጠፉ በኋላ አጠፉ።
አጠቃላይ ቪድዮው 62 ሰከንድ ርዝማኔ ያለው ሲሆን 'ዘ ላየን ስሊፕስ ቱ ናይት' በሚል ማጀቢያ ሙዚቃ አለው። በቪድዮው መጨረሻ ላይ ባራክ እና ሚሼል ኦባማን እንደ ዝንጀሮ አድርጎ የሚያሳይ ክፍል ይታያል።
እንደ አውሮፓውያኑ በ2020 የተካሄደው ምርጫ ተጭበርብሯል የሚል ይዘት ያለውን ቪድዮ ትራምፕ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው አጋርተዋል።
ትራምፕ ለጋዜጠኞች በሰጡት ማብራሪያ "ምንም ስህተት አልሠራሁም። የቪድዮውን መጀመሪያ ክፍል ብቻ ካየሁት በኋላ ነው የቢሮዬ ሠራተኞች የለጠፉት። ኦባማዎችን በዚያ መንገድ የሚያሳይ ክፍል እንዳለው አላወቅኩም" ብለዋል።
ጥቁር አሜሪካዊው ሪፐብሊካን ሴናተር ቲም ስኮት "በዋይት ሀውስ ያየሁት እጅግ ዘረኛ ነገር ነው" ሲሉ ተችተዋል።
ዋይት ሀውስ መጀመሪያ አካባቢ ተቺዎችን "ሐሰተኛ ቁጣ አታስተጋቡ" ብሎ ቢያጣጥልም፤ ውግዘቱ ሲበረታ ቪድዮው ከትራምፕ ትሩዝ ሶሻል ገጽ እንዲጠፋ ተወስኗል።
ዋይት ሀውስ ኋላ ላይ "በስህተት" ቪድዮው እንደተለጠፈ ገልጿል።
ኤክስ ላይ ይዘት የሚያጋራው ወግ አጥባቂ ዜርያስ የሠራው ቪድዮ፤ ጥቁር ሕዝብን ከዝንጀሮ ጋር የሚያመሳስል ዘረኛ ይዘት ነው።
የኒው ዮርክ ተወካይ አሌክሳንድያ ኦካዝዮ-ኮርቴዝ፣ የኒው ዮርክ ከንቲባ ዞህራን ማምዳኒ እና የቀድሞው የውጭ ጉዳይ ኃላፊት ሂላሪ ክሊንተን ከተለያዩ እንሰሳት ጋር እየተነጻጸሩ በቪድዮው ይታያሉ።
የቀድሞው ፕሬዝዳነት ጆ ባይደን እንደ ዝንጀሮ ሙዝ ሲበሉም ቪድዮው ያሳያል።
ባራክ እና ሚሼል ኦባማ እስካሁን አስተያየት አልሰጡም።
ትራምፕ በኤር ፎርስ አውሮፕላን ላይ ሆነው ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ "ብዙ ሺህ ነገሮች ነው የምመለከተው። ቪድዮውን ትንሽ ካየሁ በኋላ ሙሉውን እንዲመለከቱ ብዬ ለሚመለከታቸው ሰጥቻለሁ" ብለዋል።
ምርጫው መጭበርበሩን በተመለከተ ቪድዮው ያስተላለፈው መልዕክት ትክክለኛ እንደሆነም ተናግረዋል።
የትራምፕ ደጋፊዎችም ሳይቀር የቪድዮውን ዘረኛነት በመግለጽ ከገጻቸው እንዲወገድ አሳስበዋል።
ሪፐብሊካኑ የኒው ዮርክ ተወካይ ማይክ ላውር "በጣም የተሳሳተ እና አስቀያሚ ይዘት ነው። በአፋጣኝ ይቅርታ መጠየቅ አለበት" ብለዋል።
ቪድዮው ከትራምፕ ገጽ ከወረደ በኋላም ትችቱ ቀጥሏል።
የቢቢሲ የአሜሪካ አጋር ሲቢኤስ እንደዘገበው የትራምፕ ወዳጅ የሆኑት የፍሎሪዳ ተወካይ ብራየን ዶናልድስ ቪድዮው ከተለጠፈ በኋላ ወደ ዋይት ሀውስ ደውለው ቁጣቸውን ገልጸዋል።
"ፕሬዝዳንቱ የጣሉበትን ኃላፊነት ያልተወጣ አንድ ሠራተኛ" የሠራው ስህተት ነው የሚል ምላሽ እንደተሰጣቸውን ተዘግቧል።
በትራምፕ ገጽ ላይ የሚለጠፉ ይዘቶች ምን ዓይነት የማጣሪያ ሒደት እንደሚያልፉ ቢቢሲ ከዋይት ሀውስ ማብራሪያ ጠይቋል።
የዋይት ሀውስ ፕሬስ ሴክረተሪ ካሎላይን ሌቪት "ቪድዮው ፕሬዝዳንት ትራምፕን ንጉሥ አድርጎ የሚስል እና ዴሞክራቶችን 'ከላየን ኪንግ' ፊልም ገጸ ባህሪያት ጋር የሚያነጻጽር ነው። ሐሰተኛ ቁጣን መዘገብ አቁሙና ለአሜሪካ ሕዝብ ግድ የሚሰጥ ነገር ላይ አተኩሩ" የሚል ምላሽ ለቢቢሲ ሰጥተዋል።
የናሽናል አሶሴሸን ፎር ዘ አድቫንስመንት ኦፍ ከለርድ ፒፕል ፕሬዝዳንት ኃላፊ ዴሬክ ጆንሰን፤ ቪድዮው ከመሰረዙ በፊት "አስቀያሚ እና አስጸያፊ ነው" ሲሉ አውግዘዋል።
ትራምፕ ከጄፍሪ ኤፕስቲን ሰነዶች ትኩረት ለማስቀየር እየሞከሩ ነው በማለትም ተችተዋል።
የ2020 ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ተጭበርብሯል የሚለው ክስ ሐሰተኛ እንደሆነ በተደጋጋሚ ተገልጿል።
ትራምፕ ሚሼል እና ባራክ ኦባማን በመንቀፍ ይታወቃሉ።
ባራክ ኦባማ ኬንያ ነው የተወለዱት የሚል ሐሰተኛ ዜና አሰራጭተው እንደነበር ይታወሳል። ባራክ የተወለዱት ሀዋይ ሲሆን በዜግነታቸውም አሜሪካዊ ናቸው።