በፍሎሪዳ ትራምፕን ለመግደል የሞከረው ግለሰብ የእድሜ ልክ እስራት ተፈረደበት

የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

ከአንድ ዓመት ተኩል በፊት ፕሬዚደንት ትራምፕ በአሜሪካዋ ግዛት ፍሎሪዳ የጎልፍ ሜዳ ላይ ሳሉ ተኩሶ ለመግደል ሙከራ ያደረገው ራያን ራውዝ የእድሜ ልክ እስራት ተፈረደበት።

የ59 ዓመቱ ራውዝ በወቅቱ ፕሬዚዳንታዊ እጩ የነበሩትን ትራምፕን በዌስት ፓልም ባሕር ዳርቻ ዓለም አቀፍ የጎልፍ መጫዎቻ ሜዳ ላይ ለመግደል በመሞከር ጥፋተኛ የተባለው ባለፈው ዓመት ነበር።

ራውዝ በአካባቢው በነበረ ጥሻ ተደብቆ ለመተኮስ ሲያነጣጥር የተመለከተው በስፍራው የነበረ የአሜሪካ የደኅንነት ወኪል ከተኮሰበት በኋላ ከቦታው ሸሽቶ የነበረ ሲሆን ብዙም ሳይቆይ በቁጥጥር ሥር ሊውል ችሏል።

ዳኛ ኤሊን ካኖን ውሳኔውን በያዘው መዝገብ ላይ የራውዝ ወንጀል " በማይካድ ሁኔታ የእድሜ ልክ እስራት እንዲወሰንበት የሚያስገድዱ ናቸው" ብለዋል።

"በወቅቱ ዋነኛ ፕሬዚዳንታዊ እጩ የነበሩትን ግለሰብ ለመግደል ለወራት እርምጃዎችን ሲወስድ ነበር። በመንገድ ላይ ያለ ማንኛውንም ሰው ለመግደልም ፍላጎት አሳይቷል። ከዚያም በኋላ ለተጎጂዎች ፀፀትም ሆነ ሀዘኑን አልገለፀም" ሲሉ ጽፈዋል።

የራውዝ ጠበቃ ማርቲን ሮስ በበኩላቸው በፍርዱ ላይ ይግባኝ እንደሚጠይቁ ገልጸዋል።

ባለፈው መስከርም ወር ላይ በተጀመረው የፍርድ ሒደቱ ራሱን ወክሎ ለመከራከር የመረጠው ራውዝ ጥፋተኛ እንዳልሆነ ገልጿል።

የሰሜን ካሮላይና ግዛት ተወላጅ የሆነው ራውዝ በቁጥጥር ሥር ከማዋሉ በፊት በሃዋይ ይኖር ነበር።

በነበሩት ችሎቶች ወቅት የተዘበራረቀ ሃሳብ ሲያነሳ የነበረ ሲሆን የትራምፕ የጎልፍ ጨዋታ ሲቃወም እና አዶሊፍ ሂትለርን እና የሩሲያውን ፕሬዚደንት ቭላድሚር ፑቲንን ሲጠቅስ ነበር።

ዳኞች ጥፋተኛ መሆኑን ካረጋገጡ በኋላም የአሜሪካ የጸጥታ ኃይሎች ከችሎቱ ይዘውት ከመውጣታቸው በፊት በእስክርቢቶ አንገቱ ለመውጋት ሞክሮ ነበር።

ምንም እንኳን ራውዝ ድርጊቱን በፈፀመበት ጊዜ ትራምፕን ለመግደል ግልጽ የሆነ ዕይታ ያልነበረው ቢሆንም የፌደራል ወኪሎች ራውዝ ተደብቆ ሊተኩስ ከነበረበት ሥፍራ ሆኖ ዒላማ የሚያደርግ በከፊል አውቶማቲክ የሆነ መሣሪያ ማግኘታቸውን ለዳኞች ተናግረዋል።

ከዚህም በተጨማሪ ዳኞች ትራምፕ ሊገኙባቸው ይችሉ የነበሩ ሥፍራዎች ዝርዝር እንዲሁም ለጓደኛው የተወውን ማስታወሻ እንዳገኙ እንደተነገራቸው እና ይህም "የግድያ ሙከራ" መሆኑን ጠቅሰዋል።

በችሎቱ ወቅት ባደረገው የመዝጊያ መግለጫ ላይ ራውዝ በሦስተኛ ሰው ንግግር ያደረገ ሲሆን የአሜሪካን ታሪክ፣ የሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት እና ጀልባ የመግዛት ፍላጎቱን ጨምሮ በርካታ የማይገናኙ ርዕሰ ጉዳዮች ዳሷል። ይህም ዳኛዋ በንግግሩ በተደጋጋሚ ጣልቃ እንዲገቡና ዳኞቹን እንዲበትኑ አድርጓቸዋል።

በጉዳዩ ላይ ዋና አቃቤ ሕግ የሆኑት ጆን ሺፕሊ "ይህንን ጉዳይ እንዲጠናቀቅ ያደረጉ "ብዙ ማስረጃዎች" ቀርበዋል ብለዋል።

ይህ በፍሎሪዳ የተከሰተው ክስተት በ2024 ትራምፕን ለመግደል የተደረገው ሁለተኛው ሙከራ ነው። በዚያው ዓመት ሐምሌ ወር ላይ አንድ ታጣቂ በፔንስልቬንያ በትለር የምርጫ ቅስቀሳ ዘመቻ ላይ ሳሉ ተኩስ ከፍቶባቸው ነበር።

በዚህ ተኩስ አንድ ሰው ሲሞት ትራምፕን ጨምሮ በርካታ ሰዎች ቆስለዋል።

ተኩሱን የከፈተው እና በኋላ ላይ የ20 ዓመቱ ቶማስ ክሩክስ እንደሆነ የተለየው ግለሰብ በቦታው በነበሩ ፖሊሶች ተገድሏል።