እስራኤል እና አሜሪካ በኢራን ላይ ስለከፈቱት ጥቃት እስካሁን የምናውቀው

የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

ስዊትዘርላንድ ጄኔቭ ላይ በአሜሪካ እና በኢራን መካከል የተካሄደው ሦስተኛ ዙር ድርድር ውጤት ባለማምጣቱ ደስተኛ አለመሆናቸውን ፕሬዝዳንት ትራምፕ ከተናገሩ ከሰዓታት በኋላ እስራኤል ቅዳሜ የካቲት 21/2018 ዓ.ም. ጠዋት በኢራን ላይ ጥቃት ከፍታለች።

ጠዋት ሁለት ሰዓት አካባቢ ከአየር እና ከባሕር ላይ በተወነጨፉ ሚሳዔሎች በዋና ከተማ ቴህራን ውስጥ የሚገኙ የተለያዩ ቦታዎች ላይ ከፍተኛ ፍንዳታዎች ተሰምተዋል።

ይህንንም ተከትሎ ከኢራን በኩል የአጸፋ ጥቃት ሊሰነዘር እንደሚችል በመስጋት በመላዋ እስራኤል የአደጋ ጊዜ ማስጠንቀቂያ ደውል የተሰማ ሲሆን፣ ዜጎቿ ከዕለት ተለት እንቅስቃሴ እንዲታቀቡ እስራኤል መክራለች።

ባለፉት ሳምንታት ወታደራዊ ኃይላቸውን በኢራን ዙሪያ እንዲጠናከር ያደረጉት ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አገራቸው በኢራን ላይ በተከፈተው ጥቃት ውስጥ መሳተፏን አረጋግጠዋል።

የኢራን መገናኛ ብዙኃን ጥቃቱ በዋና ከተማዋ ላይ ብቻ ያነጣጠረ ሳይሆን ሌሎች አምስት ከተሞችም ዒላማ መደረጋቸውን እና ከፍተኛ የፍንዳታ ድምጽ መሰማቱን ዘግበዋል።

ነገር ግን ከጥቃቱ በኋላ ባሉት ሰዓታት በኋላ በጥቃቱ ስለደረሰ ጉዳት እንዲሁም የኢራን መንግሥት ባለሥልጣናት ስለጥቃቱ ያሉት ነገር የለም። የአገሪቱ መንግሥት መገናኛ ብዙኃን ፕሬዝዳንቱ ማሱድ ፔዜሽኪያን "በደህና ሁኔታ" ላይ እንደሚገኙ ዘግበዋል።

እስራኤል እና ኢራን የአየር ክልላቸውን ለየትኛውም ዓይነት የአውሮፕላን በረራዎች መዝጋታቸውን አስታውቀዋል።

የእስራኤል መከላከያ ሚኒስቴር የኢራንን አቅም ለማዳከም 'ቀድሞ የማጥቃት' እርምጃ መውሰዱን በይፋ ቢያስታውቅም፣ አሜሪካ በጥቃቱ ውስጥ ተሳታፊ መሆኗን ኋላ ላይ አረገግጣለች።

ፕሬዝዳንት ትራምፕ በትሩዝ የማኅበራዊ ሚዲያ መድረካቸው ላይ ባሠራጩት ቪዲዮ አሜሪካ "ከፍተኛ የውጊያ ዘመቻ" በኢራን ላይ መከፈቱን ተናግረዋል።

ፕሬዝዳንቱ ጨምረውም ዘመቻው ለአሜሪካ እና ለወዳጆቸቻው ስጋት ያሉትን የኢራን መንግሥትን ዒላማ ያደረገ መሆኑን እና የኢራን አብዮታዊ ዘብ መሳሪያውን ካስቀመጠ ተጠያቂ እንደማይሆን ካልሆነ ግን "የማይቀረው ሞት ይጠብቃችኋል" ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

አሜሪካ በኢራን ላይ መዛት የጀመረችው እና ግዙፍ አውሮፕላን ተሸካሚ መርከቦቿን ወደ አካባቢው ማሰማራት የጀመረችው በታኅሣሥ ወር በተቀሰቀሰው ሕዝባዊ ተቃውሞ በሺዎች የሚቆጠሩ ተቃዋሚዎች ከተገደሉ በኋላ ነው።

አሜሪካ በኢራቅ ላይ ከ20 ዓመታት በፊት ከፈጸመችው ወረራ ወዲህ ከፍተኛ ነው የተባለውን ወታደራዊ አቅሟን ባለፉት ሳምንታት ወደ ፋርስ ባሕረ ሰላጤ አንቀሳቅሳ ለጥቃት ስትዘጋጅ እና ስትዝት ቆይታለች።

ባለፈው ሳምንት የተካሄደው ድርድር ከውጤት አለመድረሱን ተከትሎ አሜሪካ ኢራንን ለማስገደድ ውስን ጥቃት ለመፈጸም እንደተዘጋጀች ሲነገር የነበረ ሲሆን፣ የአሁኑ የእስራኤል እና የአሜሪካ ጥቃት የዚህ አካል ይሁን አይሁን አልታወቀም።

እስከ እስራኤል ድረስ ዘልቆ የሚመታ ሚሳዔል የታጠቀችው ኢራን ከተከፈተባት ከጥቂት ሰዓታት በኋላ ወደ እስራኤል ሚሳዔሎችን ማስወንጨፏ ተዘግቧል።

የእስራኤል መከላከያ ኃይል እንዳለው ዛሬ በኢራን ላይ የተከፈተው ጥቃት ለወራት ከተደረገ ዝግጅት እና ዕቅድ በኋላ ቀኑ የተቆረጠው ከሳምንታት በፊት ነው።

አሜሪካ ሲካሄድ በነበረው ድርድር ላይ ለዓመታት ሲያወዛግብ ከነበረው ከኢራን የኒውክሌር ፕሮግራም በተጨማሪ ረጅም ርቀት ተወንጫፊ ሚሳዔሎቿ ላይም እርምጃ እንዲወሰድ ስትጠይቅ ነበር። ኢራን ግን የሚሳዔሎቿ ጉዳይ "ቀይ መስመር" መሆኑን በመግለጽ ተቃውማለች።

ከጥቃቱ መጀመር በኋላ ፕሬዝዳንት ትራምፕ እና ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታኒያሁ በተናጠል እንደተናገሩት ኢራናውያን መንግሥታቸውን እንዲያስወግዱ ጥሪ አቅርበዋል። ይህ በኢራን ውስጥ የአገዛዝ ለውጥ የማምጣት ፍላጎት በሁለቱ አገራት በይፋ ሲነገር የቀየ ዕቅድ ነው።

ከጥቃቱ መፈጸም ከሰዓታት በኋላ የሚወጡ ዘገባዎች እንደሚያመለክቱት የአገሪቱ ፕሬዝዳንት ጽህፈት የተመታ ሲሆን፣ ፕሬዝዳንቱ ላይ ጉዳት አለመድረሱን ሜህር የተባለው የዜና ምንጭ ገልጿል።

በኢራን ውስጥ ዋነኛው ውሳኔ ሰጪ የሆኑት ጠቅላይ መሪው አያቶላህ አሊ ኻሜኒ ጥቃቱ ሲፈጸም በዋና ከተማዋ ውስጥ እንዳልነበሩ እና ወደ አስተማማኝ ቦታ መዘዋወራቸውን አንድ ባለሥልጣን ለሮይተርስ ዜና ወኪል ተናግረዋል።

ባለፉት ሳምንታት በኢራን ላይ ጥቃት የሚፈጸም ከሆነ ከወታደራዊ ዒላማዎች በተጨማሪ ጠቅላይ መሪው እና ልጃቸው ላይ እንደሚያተኩር ተገልጾ ነበር።

በከተሞች አካባቢ ዛሬ የተፈጸሙት ጥቃቶችም ምናልባት የኢራን ፖለቲካዊ እና ወታደራዊ መሪዎችን ዒላማ ሳያደርጉ እንዳልቀሩ እየተነገረ ነው።

እስካሁን በጥቃቶቹ በሰው ላይ ስለደረሰ ጉዳት እና የትኞቹ ተቋማት እንደተመቱ የተባለ ነገር የለም።

አሜሪካ ከእስራኤል ጋር በመሆን ወሳኝ ዘመቻ በኢራን ላይ መክፈቷን የተናገሩት ፕሬዝዳንት ትራምፕ በሂደቱ መስዋዕትነት ሊኖር እንደሚችል አስጠንቅቀዋል።

ጥቃቱ ዓላማ ያደረገው የኢራንን ሚሳዔሎች ማውደም እና ባሕር ኃይሏን መደምሰስ መሆኑን የጠቀሱት ትራምፕ፣ በዚህ ሂደትም ሞት እና ጉዳት በአሜሪካውያን ላይ ሊደርስ እንደሚችል ይህም መጪውን ጊዜ ደኅንነቱ የተጠበቀ ለማድረግ ነው ብለዋል።

የእስራኤል ጦር ዛሬ ኢራን ላይ ከፈጸመው ጥቃት ጎን ለጎን በሊባኖስ ውስጥ የኢራን አጋር በሆነው ሄዝቦላህ ይዞታዎች ላይ እርምጃ ወስዷል። ከጥቃቱ ጋር ተያይዞ ሠራዊቱን በሊባኖስ ድንበር ላይ ለማጠናከር የተጠባባቂ ኃይል አባላትን በሙሉ ጠርቷል።