በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ጠቅላይ ሚኒስትር ቸርችል ናዚን የተዋጉባት ተጽእኖ ፈጣሪዋ ሴት

የንባብ ጊዜ: 5 ደቂቃ

ለቀድሞው የዩናይትድ ኪንግደም መሪ ዊንስተን ቸርችል የልጃቸው ሚስት ምራታቸው ብቻ አልነበረችም፤ ታማኝ ወዳጅም ጭምር እንጂ። ይህቺ ሴት ግን "ታላቋ የዘመኑ ዘማዊት" የሚል ቅጽልም ነበራት።

ሕይወቷ ካለፈ 30 ዓመት ገደማ ቢሆንም አሁንም ድረስ የሥልጣን ጨዋታ የገባት ብልህ ሴት ነች? ወይስ "እፍረትአልባ" እና "አጸያፊ"? የሚለው አከራካሪ ነው።

ከብሪታኒያ ባላባት ቤተሰብ የተገኘችው ፓሜላ ሃሪማን፤ ከብሪታኒያ ተነስታ አሜሪካ ውስጥ ተጽእኖ መፍጠር የቻለች፤ ኋላም በፈረንሳይ የአሜሪካ አምባሳደር በመሆን ያበቃች ሴት ነች። ሕይወቷም በ20ኛው ክፍለ ዘመን የነበሩ በርካታ የፖለቲካ እና የባህል ዘርፍ ታዋቂ ሰዎችን ነክቷል።

ዊንሰተን ችርችል "እምቢ የማትል እና ቁርጠኛ ምሥጢራዊ መሣሪያቸው" አድርገው ያጯት ገና የ20 ዓመት ወጣት እያለች ነበር።

በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ከወሳኝ አሜሪካውያን ጋር እራት በልታ እና ወይን ተጎንጭታ ሲያሻትም አማልላ ናዚን እየተዋጋች ካለችው ብሪታኒያ ጎን እንዲቆሙ አድርጋለች።

በኋላም ተጽእኖዋ እየሰፋ ሄዶ እንደ ኬኔዲዎች፣ ቢል ክሊንተን፣ ኔልሰን ማንዴላ እና ትሩማን ከመሳሰሉ ስመጥር ሰዎች ጋር ግንኙነት ፈጥራ ነበር።

ፓሜላ ሃሪማን በፓሪስ ሪትዝ ሆቴል መዋኛ ገንዳ ሳለች በድንገት ባጋጠማት የደም መፍሰስን ያስከተለ በሽታ የተነሳ ከሞተች 30 ዓመት እየተጠጋ ነው።

በአውሮፓውያኑ 2024 "Kingmaker: Pamela Harriman's Astonishing Life of Power, Seduction, and Intrigue" የተሰኘው በእርሷ ሕይወት ላይ የሚያጠነጥን መጽሐፍ ሲወጣም አከራካሪነቷ አልቀነሰም።

በሶኒያ ፑርኔል የተጻፈው ይህ ግለ ታሪክ በወጣበት ወቅት መጽሐፉ በድፍረት፣ በብልሃት እና ከፍ ባለ ህልም ለተመራው የዚህች ሴት ሕይወት የተበረከተ ሙገሳ አድርገው የቆጠሩት ሰዎች ነበሩ።

ወደ እርካቡ ለመውጣት ወሲብን የተጠቀመች እና የፖለቲካ ተጽእኖዋ የተጋነነ ሴት በማለት የሚገልጿት ሌሎች ደግሞ መጽሐፉ ያልተገባ ውዳሴ እንዳቀረበ በማንሳት ተችተዋል።

እጅ ከሚያጥረው የዝቅተኛ መደብ ባላባት ቤተሰብ በአውሮፓውያኑ 1920 የተወለደችው ፓሜላ፤ "መልካም ትዳር" እንድታገኝ ተደርጋ ነበር ያደገችው። የመጀመሪያ ባለቤቷ የጠቅላይ ሚኒስትር ዊንስተን ቸርችል ብቸኛ ልጅ የሆነው ራንዶልፍ ቸርችል ነበር።

በወቅቱ ራንዶልፍ ገና በተጀመረው በሁለተኛው የዓለም ጦርነት እንደሚገደል እርግጠኛ ሆኖ ነበር። ከመሞቱ በፊትም ወንድ ልጅ የመውለድ ከፍተኛ ፍላጎት ነበረው። ከፓሜላ ጋር ለመጀመሪያ ጊዜ እራት ለመብላት በወጡበት ወቅትም ዙሪያ ጥምጥም መሄድ አልፈለገም።

የሕይወት ታሪኳን ያሳተመችው ፑርኔል፤ "አልወደዳትም ነበር...ግን ለእርሱ ልጅ ለመውለድ ያህል ጤነኛ ሆና ታይታው ነበር" ስትል ጽፋለች።

ከወላጆቿ ጋር የምታሳልፈው አሰልቺ ሕይወት ያንገሸገሻት ፓሜላም፤ ሀሳቡን ተቀብላ ልትወልድለት ትስማማች።

ምንም እንኳ ይህ የገባችበት ቁማር ኋላ ላይ ቢከፍላትም፤ ትዳሯ የሰመረ አልነበረም። ራንዶልፍ ሰካራም እና አስቸጋሪ ነበር። ልጅ ከመውለዷ በፊትም ሆነ በኋላ የሚመለከታት በንቀት ዐይን ነበር።

በአውሮፓውያኑ 1940 አማቷ ዊንስተን ቸርችል የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር ሲሆኑ ግን ሁኔታዎች ተቀየሩ።

የብሪታኒያ እና የዓለም ሁሉም ነገር የሚጠነሰስበት ክፍል ውስጥ ተቀላቀለች። "እንደ እኔ ፖለቲካን በቅርብ ለማየት ዕድል ያገኘ ማንም የለም" ስትል ኋላ ላይ ተናግራለች።

በወቅቱ ብሪታኒያ የናዚን የጦርነት ኃይል የተጋፈጠችው ብቻዋን ነበረ። በአስቸኳይ የአሜሪካን ድጋፍ የፈለጉት ቸርችልም የፈለጉት በቶሎ እንደማይደርስ ገብቷቸዋል።

ፓሜላ ብሪታኒያ ምን ዓይነት አጣብቂኝ ውስጥ እንደገባች ተረድታ ነበር። "አሜሪካ ከገባችበት ጦርነቱ አስተማማኝ ይሆናል። ጦርነቱ ውስጥ እስካልተሳተፉ ድረስ ግን ነገሩ አሳሳቢ ነው" የሚል አረዳድ እንደነበራት ተናግራለች።

ቸርችት ደስተኛ እና ውብ በሆነቸው የልጃቸው ሚስት ላይ ተስፋቸውን ጥለዋል፤ እሷም አላሳፈረቻቸውም።

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ሩዝቬልት ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ብሪታኒያ ለላኩት መልዕክተኛቸው ሃሪ ሆፕኪንስን በሙገሳ ላይ ሙገሳ ደርባለች።

በ1941 አቬሬል ሃሪማን ልዩ መልዕክተኛ ሆነው ወደ ዩናይትድ ኪንግደም ሲጓዙም ራሷን ማስተዋወቅ ችላለች። በወቅት 21 ዓመቷ የነበረችው ፓሜላ ከ49 ዓመቱ ባለትዳር ሃሪማን ጋር የፍቅር ግንኙነት ጀመረች።

የአሜሪካው ልዩ መልዕክተኛ ምን እንደሚናገር እና ምን እንደሚሠራ ማወቅ የሚሹት አማቷ ጠቅላይ ሚኒስትር ቸርችል መረጃ እንድታቀብላቸው ይጠይቋት ነበር።

ሮጀር ሉዊስ የተባለ ፀሐፊ 'ዘ ታይምስ ጋዜጣ' ላይ ባሳተመው አንድ ሂስ፤ ፓሜላ ለአማቷ ጠቃሚ መረጃዎችን ታቀብል ነበር የሚለውን ሃሳብ ውድቅ አድርጓል። "የወሲብ አባዜ ያለባት ቅጥረኛ" ሲሉም አብጠልጥሏታል።

የኮኔክቲከት ዩኒቨርሲቲ የታሪክ ፕሮፌሰር የሆኑት እና በሩዝቬልት ላይ መጽሐፍ ያሳተሙት ፍራንክ ኮስቲግሊዮላ በበኩላቸው፤ "በጦርነት ወቅት መረጃ ካለው አስፈላጊነት አንጻር ፓሜላ ለቸርችል ትልቅ ዕሴት ነበረች። በተቃራኒው ማሰብ ታሪክን አለማወቅ እንዲሁም የሴት ጠልነት ስሜት ነው" ብለዋል።

የፓሜላን ግለ ታሪክ የጻፈችው ፑርኔልም ብትሆን ወሲብን ትጠቀም ነበር የሚለው ጉዳይ ላይ አትከራከርም።

"ታላቋ የዘመኑ ዘማዊት" ተብላ ትጠራ እንደነበርም መጽሐፏ ላይ አስፍራለች። በርካታ የአሜሪካ የጦር አዛዦች፣ ጋዜጠኞች እና ሌሎችም ከእርሷ ጋር የፍቅር ግንኙነት ነበራቸው።

ፓሜላ እነዚህን ግንኙነቶቿን ተጠቅማ ምን ዓይነት መረጃዎችን ለጠቅላይ ሚኒስትር ቸርችል ትሰጥ ነበር? ጠቅላይ ሚኒስትሩስ ምን ዓይነት መረጃዎችን እንድታመጣ ይጠይቋት ነበር? የሚለው ግልጽ አይደለም።

ግለ ታሪኳን የያዘው መጽሐፍ ላይ ከፍቅረኞቿ ጋር "መኝታ ቤት ውስጥ የሚኖራት ወሬ በሁለቱም የአትላንቲክ ውቅያኖስ ጽንፍ ያሉ መሪዎች ጋር ይደርሱ ነበር፤ ከፍተኛ የፖሊሲ ውሳኔዎች ላይም ተጽእኖ ያሳድሩ ነበር" ተብሎ ተጽፏል።

ሉዊስ በዘ ታይምስ ጋዜጣ ባሳተመው ጽሑፍ ይህንን ጉዳይ "ግነት" ሲል ይጠቅሰዋል።

ሆኖም ባለቤቷ ራንዶልፍ፤ በአባቱ ጠንሳሽነት የሚካሄደውን የሚስቱን አመንዝራነት በተረዳ ጊዜ ወላጆቿ በተባባሪነት በመሳተፋቸው አስቆትቶት ነበር። ይህ ጉዳይ ምን አልባትም ተጽእኖ እንደነበራት አመላካች ሊሆን ይችላል።

ኑሮ እና ዝና በአሜሪካ

ፓሜላ ከጦርነቱ ማብቃት በኋላ ትዳሯን ፈትታ ወደ ፓሪስ አምርታለች። በዚያም እንደ ኤሊ ደ ሮዝቻይልድ እና ልዑል አሊ ካህን ካሉ ባለጸጎች ጋር የፍቅር ግንኙነት መሥርታለች።

ሀብታሞቹ ፍቅረኞቿ ቅንጡ ሕይወት እንድትመራ ቢያደርጓትም እንዳቸውም ጣቷ ላይ ቀለበት አላጠለቁም።

ዕድሜዋ ወደ 40 ሲጠጋ ደግሞ ታዋቂው የሆሊውድ አዘጋጅ ሌላንድ ሄይዋርድ ባለቤቱን ፈትቶ እንዲያገባት አድርጋለች።

ሄይዋርድ ከፓሜላ ጋር ከተጋባ በኋላ የሥራ ስኬቱ እና የጤና ሁኔታው በፍጥነት አሽቆልቁሏል። ይህም ቢሆን ጥላው አልሄደችም፤ በታማኝነት አብራው ቆይታለች።

"የቤተሰቡን ውድ ጌጣጌጦች ሰርቃለች" በማለት ፓሜላን የምትከስሳት ሄይዋርድ ልጅ እንኳ መልካም ሚስትነቷን መስክራላታለች። "ፓሜላ ታላቅ ተሰጥኦ ነበራት። የምትወዳቸውን ወንዶች ትረዳቸዋለች" ብላለች።

በአውሮፓውያኑ 1971 ባለቤቷ ሄይዋርድ ከሞተ በኋላ ሌላ ትዳር ለመመሥረት ብዙም ጊዜ አልፈጀባትም።

በ20ዎቹ መጀመሪያ ላይ ሳለች የአሜሪካ ፕሬዝዳንት መልዕክተኛ ሆኖ ወደ ብሪታኒያ በመጣበት ጊዜ የፍቅር ግንኙነት ጀምረው ከነበረው አቬሬል ሃሪማን ጋር አንድ ድግስ ላይ ተገናኘች።

ሃሪማንም ከአንድ ዓመት በፊት ሚስቱን በሞት አጥቶ ነበር። በስርቆት ተጀመረውን ፍቅራቸውን እንደገና አስጀምረው በወራት ጊዜ ውስጥ ተጋብተዋል።

ፓሜላ የሕይወቷን የመጨረሻዎቹን ሁለት አስርት ዓመታት ያሳለፈችው አሜሪካ ውስጥ ተጽእኖ ፈጣሪ ሆና ነበር።

በ1980 ሮናልድ ሬገን ካሸነፉ በኋላ፤ በሚሊዮኖች ዶላር በሚቆጠረው የባለቤቷ ሀብት ታግዛ ለዴሞክራቲክ ፓርቲ ዕጩዎችን የገንዘብ ድጋፍ ማድረግ ጀመረች።

የመሪነት ሥልጣን ላይ ከመውጣታቸው በፊት ድጋፍ ካደረገችላቸው ፕሬዝዳንቶች መካከል በወቅቱ የዴላዌር ግዛት ሴናተር የነበሩት ጆ ባይደን እና በሰዓቱ የአርካንሳስ ግዛት ገዢ የነበሩት ቢል ክሊንተን ይገኙበታል።

ይህ የተጽእኖ ፈጣሪነት ጉዞዋ የተቋጨው በክሊንተን የሥልጣን ዘመን በፈረንሳይ የአሜሪካ አምባሳደር ተደርጋ ስትሾም ነው።

ዕድሜው እየገፋ ለነበረው ባለቤቷ ሃሪማን ታማኝ እና መልካም ሚስት የነበረች ቢሆንም፤ ፖለቲካን "በጭኖቿ መካከል ያደረገች" የሚል ቅጽል ከማግኘት አላመለጠችም።

የፓሜላ ታሪክ ላይ በተጻፈው መጽሐፍ ላይ ሂሱን ያሳተመው የታሪካዊ ልብ ወለድ ደራሲው ቶማስ ማሎን፤ ግለ ታሪኩ እጅግ ወሳኝ በምትመስለው ይህቺ ሴት ሕይወት ውስጥ ያለውን የባዶነት ስሜት በሚገባ ያልዳሰሰ ሲል ተችቷል።

ፓርሜላንም "ጸጸት የማይሰማት፣ ሜካኒካል ባህሪ ያላት፤ ከማስደነቅ ይልቅ የምታጸይፍ" ሲል ጠርቷታል።

የመጽሐፉ ደራሲ ፑርኔል በበኩሏ በኮንግረስ ቤተ መጻሕፍት የሚገኙትን የፓሜላን ጽሁፎች እና ደብዳቤዎች ካነበበች በኋላ እንደወደደቻት ትናገራለች።

ምናልባት የፓሜላ ሕይወት እያንዳንዱ ሰው በራሱ መነጽር የተለያየ ትርጉም የሚሰጠው ጉዞን የያዘ ነው።

ምናልባትም የሚነሳባት ቁጣ መግነኑ ማኅበረሰብ የሥነ ምግባር ጉዳይ ሲነሳ ሴቶች ላይ እንደሚበረታ የሚያመለክትም ይሆናል።

ፀሐፊው ሎውረንስ ሊመር እንደሚናገረው "ሴት ሆነሽ ከብዙ ሰዎች ጋር የምትተኚ ከሆነ 'አመንዝራ' ነሽ፤ ወንድ ከሆንክ ግን 'አማላይ' ነህ።"