ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ለሰባት ዓመታት በአምባሳደሯ ቤት ተቀምጦ አሜሪካን የሰለላት የሶቪየቶች የጥበብ ሥራ
የጥበብ ሥራ (ቅርጽ) እንዴት ሊሰልል ይችላል?
ነገሩ እንዲህ ነው።
ወቅቱ በአውሮፓውያኑ 1945 ነበር።
የዓለማችን ኃያላን ሶቭየት ኅብረት እና አሜሪካ ፉክክር ላይ የነበሩበት።
የካፒታሊስቱ የምዕራቡ ዓለም እና የኮሚኒስቱ ምሥራቅ የርዕዮተ ዓለማቸውን የበላይነት ለማስፈን የተንቀሳቀሱበት፤ በተለምዶ ቀዝቃዛው ጦርነት ተብሎ የሚጠራው ጊዜ።
በዚህም ወቅት ከሶቭየት ኅብረት የተበረከተው እና የማዳመጫ መሳሪያ የተደበቀበት የጥበብ ሥራ (በእጅ የተሠራ ቅርጽ) በአሜሪካ የደኅንነት እና የስለላ ተቋማት ሳይታወቅ ለሰባት ዓመታት ቆይቷል።
ከ80 ዓመታት በፊት፤ ሁለተኛው የዓለም ጦርነት እየተገባደደ የነበረበት ጊዜ ነበር።
የሩሲያ ስካውት ቡድን አባላት በሞስኮ ተቀማጭነታቸውን ላደረጉ የአሜሪካ አምባሳደር ስጦታ አበረከቱ።
ስጦታው በእጅ የተቀረጸ የአሜሪካ መንግሥት ዓርማ ነበር።
የስካውት ቡድኑ አባላት ስጦታቸውን ስፓዞ ሐውስ ወደተሰኘው የአምባሳደሩ መኖሪያ ቤት ሄደው ነበር ያበረከቱት።
ስጦታው በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት አሜሪካ እና ሶቪየት የነበራቸውን ትብብር የሚያመለክት ነበር። የወቅቱ የአሜሪካ አምባሳደር ደብልዩ አቭሬል ሃሪማንም ይህንን ስጦታ እስከ አውሮፓውያኑ 1952 ድረስ በቤታቸው ውስጥ በኩራት ሰቅለውት ነበር።
ነገር ግን አምባሳደሩም ሆነ የፀጥታ ቡድናቸው ሳያውቁ ዓርማው ድብቅ የማዳመጫ መሳሪያ ተገጥሞበት ነበር።
መሳሪያው ዲፕሎማሲያዊ ውይይቶችን ሳይቀር ማንም ሳያወቅ ለሰባት ዓመታት ወደ ሶቪየቶች ሲያስተላልፍ ቆይቷል።
ሶቪየት ኅብረት የጠላትን መረጃ ለማወቅ የጥበብ ሥራን ሰርጎ የመግቢያ መሳሪያ በማድረግ ስትራቴጂካዊ ጥቅም ለማግኘት ችላለች።
የእንጨት ፈረስ ገንብተው በውስጡ ተደብቀው ጠላታቸውን ማሸነፍ ከቻሉት የግሪከ አፈ ታሪከ የትሮጃን ፈረስ በኋላ ድንቅ የሚባል ብልጠት ነበር ሶቭየት ኅብረት ያሳየችው።
ምንም እንኳን የስለላ ልብወለድ ቢመስልም ይህ እውነተኛ ታሪክ ነው።
የአሜሪካ የደኅንነት ሰዎች 'ዘ ቲንግ' የሚል ስያሜ የሰጡት ይህ መሳሪያ እንዴት ሊሠራ ቻለ?
ጆን ሊትል የተሰኙት የ79 ዓመቱ የስለላ እና የደኅንነት ባለሙያ በዚህ መሳሪያ ለረጅም ጊዜ ሲደነቁ ቆይተዋል።
የመሳሪያውንም ተመሳሳይ ቅጂ ሠርተዋል።
ይህንን ሥራ የሚያሳይ የሊትል ዘጋቢ ፊልም በቅርቡ የወጣ ሲሆን፣ በመጪው ወርም በባኪንግሃምሻየር በሚገኘው ብሔራዊ ሙዝየም ለዕይታ ይበቃል።
ባለሙያው 'ዘ ቲንግ' የተሰኘውን ድብቅ የማዳመጫ መሳሪያ የሚገልጹት በሙዚቃ መሳሪያዎች ነው።
ልክ እንደ ዋሽንት እስትንፋስ ወደ ሙዚቃ የሚቀየርበት፣ ወይም የከበሮ ቆዳ ሲመታ ንዝረት ወደ ጆሮ ገብቶ ድምጽ የሚቀየርበትን መንገድ በመግለጽ ነው።
መሳሪያዋ በጣም አነስተኛ እንደ ወስፌ መሳይ ወይም የሴቶች ባርኔጣ ላይ የምትሰካ ጌጥ መሳይ ናት።
መሳሪያዋ የትኛውንም ክትትል ማለፍ ከመቻሏም በተጨማሪ፣ የተገጠመላት "የኤሌክትሮኒክስ ባትሪ" የላትም፤ እንዲሁም አትግልም።
የመሳሪያዋ ምሕንድስና በጣም የሚያስደንቅ ነበር።
እያንዳንዷ እርዝማኔ ተለክታ በጥልቀት ነበር የተሠራችው።
የታሪክ ምሁሩ ኤች ኬ ኪት ሜልተን እንደሚሉት 'ዘ ቲንግ' "የድምጽ ክትትል ሳይንስን ከዚህ ቀደመ የማይቻል ነው ተብሎ ወደሚታሰብ ደረጃ ያላቀች ናት" ብለዋል።
በአምባሳደሩ መኖሪያ ቤት ነበር በስጦታ በተበረከተው ዓርማ ውስጥ የተቀመጠችው መሳሪያዋ፤ በአቅራቢያው ባለ ሕንጻ የርቀት ማስተላለፊያም እንዲበራ ተደርጎ ነው የተዘጋጀው።
ይህም ከፍተኛ ፍሪኩዌንሲ በመላክ ከመሳሪያዋ አንቴና ንዝረቶች እንዲወጣ ማድረግ ቻለ።
በዚህ የጥብብ ሥራ ላይ የድምጽ መሳሪያ መገጠሙ የታወቀው በአውሮፓውያኑ 1951 ነበር።
በሞስኮ መቀመጫውን ያደረገው የብሪታንያ ወታደራዊ ሬድዮ አፕሬተር 'ዘ ቲንግን' የሚጠቀምበትን ትክክለኛ ሞገድ (ዌቭ ሌንግዝ) በአጋጣሚ በማግኘቱ ነበር ማዳመጫው መኖሩ የታወቀው።
እናም ኦፐሬተሩ ከሩቅ ክፍል ንግግር መስማቱን ተከትሎ ክትትል ተደረገ።
በዓመቱ የአሜሪካ ቴክኒሻኖች የአምባሳደሩ መኖሪያ ላይ ፍተሻ ጀመሩ።
ከጥቂት ቀናት በኋላ ይህ በእጅ የተቀረጸው ታላቁ ዓርማ ያረፈበት የጥበብ ሥራ ከመጋረጃ ጀርባ የአምባሳደሩን ውይይቶች የሚያዳምጥ የማይታይ ጆሮ መሆኑን የተረዱ።
ጥብብን እንደ ስለላ
የ'ዘ ቲንግ'ን ስኬታማነትን አስመልክቶ ሩሲያዊው ቴክኒሻን እና መሳሪያዋን የሚቆጣጠራት ቫዲም ጎንቻሮቭ "ለረጅም ጊዜ፣ በቀዝቃዛው ጦርነት ወቅት፣ አገራችን በጣም ጠቃሚ የሆኑ እና ልዩ መረጃዎችን በማግኘት በተወሰነ መልኩ አደራጅቶን ነበር" ይላል።
እንደ 'ዘ ቲንግ' ያሉ የሶቭየት ኅብረት መሳሪያዎች ምዕራባውያኑን ለመሰለል ምን ያህል ጥቅም ላይ እንደዋሉ እስካሁን ድረስ ከሶቭየት ኅብረት የስለላ ተቋማት ውጪ ማንም አያውቅም።
የስለላ መሳሪያዋ ዋነኛዋ ስኬት ቴክኒካዊ ሁኔታዋ ነበር።
ውበት ላላቸው ነገሮች ያለውን አመለካከት ከግምት ውስጥ በማስገባት ነበር የተነደፈችው።
የሥነ ጥበብ ሥራዎችን ወይም ማስጌጫዎችን ከባህላዊ ፍላጎት ማሳያ ወይም የባህል መገለጫ ውጪ ሌሎች ዓላማዎች የላቸውም የሚለው እምነት አለ።
የሶቪየት የደኅንነት አካላትም ይህንን እሳቤ ከግምት ውስጥ በማስገባት በእንጨት የተቀረጸውን ዓርማ መጠቀሚያ አድርገውታል።
'ዘ ቲንግ' ብቸኛው ቅርጽ ብቻ አይደለችም ለስለላ እና ለወታደራዊ ስልት መጠቀሚያ የተደረገች።
የሥነ ጥበብ ታሪክን በምንመረምርበት ወቅት ታዋቂው ሠዓሊ ሊዮናርዶ ዳቪንቺ ሞናሊዛን ከመሳል በተጨማሪ ታንኮች እና ምሽግ መስበሪያ የጦር መሳሪያዎችን ነድፏል።
ታዋቂው ሰዓሊ ፒተር ፓውል ሬበንስ በሰላሳ ዓመታት ጦርነት ወቅት ሰላይ ነበር።
በአንደኛው እና በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ከተለያዩ አገራት የተውጣጡ አርቲስቶች ጥበብን እንደ ሽፋን በመጠቀም ለዓላማቸው መጠቀሚያ አድርገዋል።
ስመ ጥሩ የብሪታንያ የጥበብ ታሪክ ተመራማሪው አንቶኒ ብለንት በሁለተኛው የዓለም ጦርነት እና በቀዝቃዛው ጦርነት ወቅት የሶቭየት ኅብረት ሰላይ ነበር።
ወደ 'ዘ ቲንግ' ስንመጣም የሙዚቃ ታሪክ የጉዳዩ ማዕከል ሆኖ እናገኘዋለን። የዚህች መሳሪያ ፈጣሪ ሌቭ ሰርጌይቪች ተርመን ወይም ሊዮን ቴርሚን እየተባለ የሚጠራው የሶቪየት ዜጋ የሆነ ጎበዝ መዚቀኛ እና የፈጠራ ሥራዎችን ያበረከተ ሰው ነው።
ይህ ሙዚቀኛ የዓለማችን የመጀመሪያ የኤሌክትሮኒክ መሳሪያ የፈለሰፈም እንደሆነ ይነገርለታል።
የሙዚቃ መሳሪያውም በስሙም ቴሬሚን በመባል ይታወቃል።
መሳሪያውን ሳይነኩ፣ በአየር ላይ እጅ በማንቀሳቀስ አንቴናዎቹ የሙዚቃዎቹን ኖት እንዲያዙ በማድረግ መጫወት የሚችሉት መሳሪያ ነው።
'ዘ ቲንግ' ከተገኘች በኋላ ጉዳዩ በአሜሪካ የስለላ ሰዎች ምሥጢር ሆኖ ቆይቶ ነበር።
ነገር ግን በአውሮፓውያኑ 1960 የኒውክሌር የጦር መሳሪያ እሽቅድድም ጣሪያ በነካበት ወቅት የአሜሪካ ዩቱ የተሰኘ የስለላ አውሮፕላን በሶቪየት ምድር ላይ ተመትቶ ወደቀ።
በዚህ የዲፕሎማሲ ቀውስ ወቅት የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባለሥልጣናት የቀዝቃዛው ጦርነት ስለላ የአንድ ወገን ብቻ አለመሆኑን ለማረጋገጥ ሩሲያ በጥበብ ሥራ ውስጥ የቀበረችውን የማዳመጫ መሳሪያ በተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት አጋለጡ።
የአምባሳደሩን መኖሪያ ቤት መደፈሩ አሳፋሪ የደኅንነት ጥሰት በመሆኑም ጆን ሊትል እንደሚናገሩት "ነገሩን በይፋ ለመናገር የስለላ አውሮፕላን ተመትቶ መጣል ነበረበት" ይላሉ።
ነገር ግን 'ዘ ቲንግን' የተደበቀበችበትን የላቀ መንገድ በወቅቱ ለሕዝብ አልተነገረም ነበር።
ሆኖም በድብቅ የብሪታኒያ የስለላ ባለሙያዎች መሳሪያዋን "SATYR" በሚል የኮድ ስም በጥልቅ ጥናት አካሂደውባታል።
ዝርዝሮቹ መንግሥታዊ ምሥጢር ተደርገው ቢቆዩም የቀድሞ የደኅንነት መኮንን ፒተር ራይት በአውሮፓውያኑ 1987፣ 'ስፓይካቸር' በሚለው ማስታወሻው ላይ ይፋ አድርጎታል።
'ዘ ቲንግ' በቴክኒክ መራቀቋ፣ የቀዝቃዛውን ጦርነት የስለላ ጨዋታን በመቀቀር በርካታ የታሪክ ምሁራንን ያስደመመች ናት።
የክላሲካል ሙዚቀኞች እንዲህ ዓይነት የስለላ መሳሪያ መፍጠራቸው፣ በእጅ የተቀረጸ የጥብበ ሥራ ወታደራዊ መረጃዎቸን ለመሰብሰብ መዋሉን የሚያስታውስም የድብቁ ታሪክ አካል ነው።