የቻይና ገንዘብ ዋጋ ከዶላር አንጻር በከፍተኛ ሁኔታ ማሽቆልቆሉ ተገለጸ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የአገራት የገንዘብ ዋጋ እያሽቆቆለ መሆኑ በስፋት እየተነገረ ባለበት በአሁኑ ወቅት፣ የቻይና ገንዘብ ዩዋን ከአሜሪካ ዶላር አንጻር በከፍተኛ ደረጃ ዋጋው ማሽቆልቆሉ ተገለጸ።
ዩዋን በዓለም አቀፍ ግብይት ውስጥ ያለው ዋጋን በተመለከተ መረጃ ይፋ መሆን ከጀመረበት ከአውሮፓውያኑ 2011 ወዲህ ዩዋን ዝቅተኛ ተባለው ደረጃ ላይ ደርሷል።
ከአስራ አራት ዓመታት በፊት በዓለም ላይ ካጋጠመው የገንዘብ ቀውስ ወዲህ የቻይና የአገር ውስጥ ገንዘብ ዋጋ አሁን በጣም ደካማ ከተባለበት ደረጃ ላይ መድረሱ ተነግሯል።
ይህ ሁኔታ የተከሰተው የአሜሪካ ማዕከላዊ ባንክ የወለድ ምጣኔን በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ ከፍ ማድረጉን ተከትሎ፣ ከዋናዎቹ ገንዘቦች አንጻር የዶላር ዋጋ ከፍ ብሏል።
የቻይና መገበያያ ገንዘብ ዩዋን ማሽቆልቆልን ለመግታት የአገሪቱ ማዕከላዊ ባንክ እርምጃዎችን እየወሰደ መሆኑ ተገልገጿል።
የቻይና ሕዝባዊ ባንክ በመባል የሚታወቀው የአገሪቱ ብሔራዊ ባንክ፣ ባንኮች በሚይዙት የውጭ ገንዘብ መጠን ላይ ቅናሽ አድርጓል።
የምጣኔ ሃብት መቃወስ በሚያጋጥምበት አስቸጋሪ ጊዜ በርካታ ባለሃብቶች ገንዘባቸውን ወደ ዶላር በመቀየር ማስቀመጥ አስተማማኙ ዘዴ እንደሆነ ያምናሉ።
ይህም የዶላርን ዋጋ ከፍ በማድረግ ያጠናከረው ሲሆን፣ የብሪታኒያ ፓወንድን የመሳሰሉ ሌሎች ገንዘቦች ደግሞ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ዋጋቸው እንዲያሽቆለቁል አድርጓል።
በአሁኑ ወቅት በዓለም ላይ ለግብይት ከሚመረጡ ጠንካራ ገንዘቦች አንጻር የአሜሪካ ዶላር ባለፉት 20 ዓመታት ውስጥ ካስመዘገበው ከፍተኛው ዋጋ ላይ ደርሷል።
በዚህም ሳቢያ ይህ የቻይናው ገንዘብ ዩዋን ዋጋ ከዶላር አንጻር ማሽቆልቆልም አንድ ማሳያ ነው ተብሏል።
በተጨማሪም ይህ ቻይና እና አሜሪካ በአገራቸው ውስጥ የሚያጋጥሟቸውን የምጣኔ ሃብት ጉዳዮች ለመፍታት የሚከተሉትን የተለያየ መንገድን ያሳያል ተብሏል።
የቻይና ማዕከላዊ ባንክ በኮቪድ ምክንያት የተጎሳቆለውን የአገሪቱን ምጣኔ ሃብት ለማነቃቃት የወለድ መጠንን ሲቀንስ፣ የአሜሪካ የፌደራል ግምጃ ቤት ግን የዋጋ ግሽበትን ለመቆጣጠር ተቃራኒ እርምጃ ነው የወሰደው።
ይህ አገራቱ የተለያየ መፍትሔዎችን መምረጣቸው ሙሉ ለሙሉ ችግር አይደለም የሚሉት የአውስትራሊያ ኮመንዌልዝ ባንክ ከፍተኛ ባለሙያ የሆኑት ጆሴፍ ካፑርሶ ናቸው።
ባለሙያው ጨምረውም የቻይና ገንዘብ ዋጋ መውረድ በአገሪቱ ውስጥ ያሉ ላኪዎች ለውጭ አገራት የሚያቀርቡትን ምርቶች ርካሽ በማድረግ ከፍተኛ ፍላጎት እንዲፈጠር በማድረግ ተጠቃሚ ያደረጋቸዋል ብለዋል።
ከዚህ በተቃራኒው ደግሞ የገንዘብ አቅም መዳከም ባለሃብቶች ገንዘባቸውን ከአገር በማስወጣት በፋይናንስ ግብይቱ ላይ አለመተማመንን ይፈጥራሉ።
የቻይና ገንዘብ ዩዋን ዋጋ መዳከም በአውስትራሊያና በሴንጋፖር ዶላር እንዲሁም በደቡብ ኮሪያ ዎንን ጨምሮ በአካባቢው ባሉ በሌሎች ባደጉ አገራት ምጣኔ ሃብት ላይ መዳካምን አስከትሏል።
ጃፓን ገንዘቧ የን ከዶላር አንጻር በመዳከሙ ከበርካታ ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ባለፈው ሳምንት ገንዘቧን ለመደገፍ መንግሥት ጣልቃ ገብቷል።
ይህ የዩዋን ዋጋ መቀነስ ከቻይና ባሻገር ለቻይና ኩባንያዎች ጥሬ እቃዎችን የሚያቀርቡትንና በቻይና ገንዘብ ላይ ጥገኛ የሆኑትን የእስያ ታዳጊ አገራት ገበያዎችም በዩዋን መዳከም ምክንያት ጉዳት ያጋጥማቸዋል።
ከዚህ ቀደም ቻይና ሆን ብላ የገንዘቧን ዋጋ በማውረድ ወደ ውጭ የምትልከው ምርት ርካሽ እንዲሆን ከአሜሪካ የምታስገባቸው ደግሞ ውድ እንዲሆኑ እያደረገች ነው ስትል ዋሽንግተን ስትከሳት ነበር።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በእስያ ውስጥ ያሉ ዋነኛ የአክሲዮን ገበያዎች ዋጋ በከፍተኛ ደረጃ ማሽቆልቆሉ ተነግሯል። በዚህም የጃፓን፣ የሆንግ ኮንግ እና የደቡብ ኮሪያ የአክሲዮን ግብይት ዋጋ ከሁለት በመቶ በላይ በሆነ መጠን ቀንሷል።












