ታዋቂዋ ሙዚቀኛ ሻኪራ በ14 ሚሊዮን ዩሮ የታክስ ማጭበርበር ፍርድ ቤት ልትቀርብ ነው

ሻኪራ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, ሻኪራ

ኮሎምቢያዊቷ የሙዚቃ ኮከብ ሻኪራ ከ14 ሚሊዮን ዩሮ በላይ ታክስ በማጭበርበር ክስ ስፔን ውስጥ ፍርድ ቤት ልትቀርብ ነው።

ስፔን ባርሴሎና ውስጥ የሚገኝ ፍርድ ቤት ነው ድምጻዊቷ ከታክስ ጋር በሚያያዙ ስድስት ያህል ክሶች ምክንያት እንድትቀርብ ያዘዘ ሲሆን፣ ችሎቱ ግን ክሷ መቼ መታየት እንደሚጀምር አስካሁን አልገለጸም።

በሻኪራ ላይ የታክስ ማጭበርበር ክስ ያቀረበው የስፔን ዐቃቤ ሕግ ጥፋተኛ ሆና ከተገኘች አስከ ስምንት ዓመት የሚደርስ አስር እና 23.8 ሚሊዮን ዩሮ እንድትቀጣ ይፈልጋል።

የ45 ዓመቷ የሙዚቃ ኮከብ ሻኪራ ግን ምንም አይነት ወንጀል አለመፈጸሟን በመግለጽ የቀረበባትን ክስ ታስተባብላለች።

“የቀረበብኝን ክስ ውድቅ የሚያደርግ በቂ ማስረጃ ስላለኝ እኔን የሚደግፍ ፍትሕ እንደማገኝ እርግጠኛ ነኝ” በማለት በቅርቡ በስፔን ቋንቋ ከታተመው ‘ኤል’ መጽሔት ጋር በነበራት ቃለ ምልልስ ገልጻለች።

የሻኪራን ጉዳይ የያዙት የሕግ ባለሙያዎች ባወጡት መግለጫ ላይ “በተገቢው ጊዜ መከራከሪያቸውን በማቅብ” ኃላፊነታቸውን እንደሚወጡ ገልጸዋል።

የስፔን ዐቃቤ ሕግ ቀደም ሲል ከሻኪራ ጋር ክስ ከመመስረት ይልቅ ከስምምነት ለመድረስ ፍላጎት እንዳለው ቢገልጽላትም፣ እሷ ግን ጉዳዩ በፍርድ ቤት እንዲታይ መርጣለች።

ክስ ከቀረቡባት ጉዳዮች መካከል ከአውሮፓውያኑ 2013 አስከ 2014 ድረስ ሻኪራ ስፔን ውስጥ እየኖረች ነገር ግን መኖሪያዋን ሌላ ቦታ አስመዝግባለች የሚለው ዋነኛው ነው ተብሏል።

በስፔን ሕግ መሠረት ታክስ ለማስከፈል ሲባል አንድ ሰው በአገሪቷ ውስጥ ስደስት ወራት ከቆየ እንደ ስፔን ነዋሪ ይቆጠራል። ነገር ግን ሻኪራ በወቅቱ በአብዛኛው ስፔን ውስጥ አልነበርኩም ስትል ትከራከራለች።

የስፔን ዐቃቤ ሕግ ግን ሻኪራ ቤተሰቧቿ እና የቀድሞ አጋሯ የባርሴሎናው እግር ኳስ ቡድን ተጫዋች ዤራርድ ፒኬ የኖሩበትን ቤት ባርሴሎና ውስጥ በ2012 (እአአ) መግዛቷን የሚያመለክት ሰነድ በቅርቡ ይፋ አድርጓል።

ጠበቃዎቿ እንደሚሉት አስከ 2014 (እአአ) ድረስ አብዛኛው የሻኪራ ገቢ የተገኘው በዓለም ዙሪያ ባቀረበቻቸው የሙዚቃ ዝግጅቶች አማካይነት ሲሆን፣ በዚህም ሳቢያ አብዛኛውን ጊዜዋን ከስፔን ውጪ ነበር ያሳለፈችው ሲሉ ይከራከራሉ።

“ከስፔናዊ ጋር ወዳጅነት ጀምሬ ስለነበር የስፔን የታክስ ባለሥልጣናት ታክስ ሊያስከፍሉኝ ፈልገው ነበር። ነገሩ ግልጽ ነው፤ ምንም ይሁን ምን የፈለጉት ገንዘብ ነው” ስትል ለኤል መጽሔት ተናግራለች።

የታክስ ጉዳይዋን ለመከታተልና ለመክፈል ስትል ከ2015 በኋላ ሻኪራ ስፔን መኖሪያዋ መሆኗን ይፋ አድርጋለች። ከዚያ በኋላም ከ17 ሚሊዮን ዩሮ በላይ ታክስ እንደከፈለች እና ምንም አይነት እዳ እንደሌለባት ገልጻለች።

በሌላ በኩል ደግሞ የቀድሞ ፍቅረኛዋ እግር ኳስ ተጫዋቹ ፒኬ በ2019 ላይ በስፔን ብሔራዊ ፍርድ ቤት በቀረበበት የታክስ ስወራ ክስ ጥፋተኛ ተብሎ 2.1 ሚሊዮን ዩሮ ተቀጥቶ ነበር።

የሰባት እና የዘጠኝ ዓመት ልጆች ያሏቸው ሻኪራ እና ዤራርድ ፒኬ ለ11 ዓመታት ያህል የቆየው ትዳራቸው አብቅቶ መለያየታቸውን ባለፈው ዓመት ሰኔ ወር ላይ ይፋ ማድረጋቸው ይታወሳል።