የሩሲያ ጄነራል ሞስኮ ውስጥ መኪናቸው ላይ በተጠመደ ቦምብ ተገደሉ

ከአካባቢው የተገኙ ምስሎች የመኪናው በሮች በፍንዳታው ክፉኛ የተጎዳ ነጭ መኪና በሌሎች ተሽከርካሪዎች ተከቦ ያሳያሉ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, በፍንዳታው ክፉኛ የተጎዳ ነጭ መኪና በሌሎች ተሽከርካሪዎች ተከቦ ይታያል

በሩሲያ ዋና ከተማ ሞስኮ ውስጥ መኪና ላይ በተጠመደ ቦምብ አንድ የአገሪቱ ከፍተኛ የጦር መኮንን መገደላቸውን ባለሥልጣናት ተናገሩ።

ፍንዳታውን እየመረመረ የሚገኘው ኮሚቴ እንዳለው ሌተናል ጄነራል ፋኒል ሳርቫሮቭ ሰኞ ጠዋት በመኪናቸው ላይ የተጠመደ ቦምብ ፈንድቶ መሞታቸውን አስታውቋል።

የ56 ዓመቱ የጦር መኮንን ሳርቫሮቭ የጦር ኃይሎች የኦፕሬሽን ማሠልጠኛ ክፍል ኃላፊ ነበሩ ተብሏል።

ምርመራ የሚያደርገው ኮሚቴ ቦምቡን በማጥመድ ውስጥ የዩክሬን ደኅንነት መሥሪያ ቤት ተሳትፎ ይኖርበት እንደሆነ እየመረመረ መሆኑን አስታውቋል።

ዩክሬን ስለ ግድያው እስካሁን ድረስ ምንም አስተያየት አልሰጠችም።

ሳርቫሮቭ በደረሰባቸው ጉዳት ወደ ሆስፒታል ከተወሰዱ በኋላ መሞታቸውን ኮሚቴው ገልጾ፣ በግድያ እና ፈንጂዎችን በሕገወጥ መንገድ ማዘዋወር ላይ ምርመራ መጀመሩን ተናግሯል።

ፍንዳታው የደረሰው ከሩሲያ ዋና ከተማ በደቡብ አቅጣጫ በሚገኝ የመኖሪያ ሕንጻ አቅራቢያ በሚገኝ የመኪና ማቆሚያ ስፍራ ላይ ሲሆን፣ የደረሰውን ፍንዳታ የሚመረምሩ ባለሙያዎች ወደ ቦታው ተልከዋል።

ከአካባቢው የተገኙ ምሥሎች በሮቹ በፍንዳታው ክፉኛ የተጎዳ ነጭ መኪና በሌሎች ተሽከርካሪዎች ተከቦ ያሳያሉ።

እንደ ሩሲያ መገናኛ ብዙኃን ዘገባ ከሆነ፣ ሳርቫሮቭ ቀደም ሲል በኦሴቲያን-ኢንጉሽ ግጭት እና በአውሮፓውያኑ 1990ዎቹ እና በ2000ዎቹ መጀመሪያ ላይ በቺቺኒያ ጦርነቶች ወቅት በውጊያዎች ላይ ተሳትፈዋል።

ከዚህም በተጨማሪ ከአውሮፓውያኑ 2015 አስከ 2016 ባለው ጊዜ ውስጥ በሶሪያ ውስጥ ዘመቻዎችን መርተዋል።

መርማሪዎች አደጋው በደረሰበት ሥፍራ ላይ ማስረጃዎችን ሲያሰባስቡ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, መርማሪዎች አደጋው በደረሰበት ሥፍራ ላይ ማስረጃዎችን ሲያሰባስቡ

የክሬምሊን ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭ እንዳሉት ቭላድሚር ፑቲን የሳርቫሮቭን ሞት ወዲያውኑ ተነግሯቸዋል።

ሩሲያ በየካቲት 2022 ዩክሬንን ሙሉ በሙሉ ከወረረችበት ጊዜ ጀምሮ በርካታ ወታደራዊ ባለሥልጣናት እና ታዋቂ ግለሰቦች በሩሲያ ዋና ከተማ የጥቃት ዒላማ ሆነዋል።

የአንድ ታዋቂ ብሔርተኛ እና የፑቲን የቅርብ አጋር ልጅ የሆነችው የ29 ዓመት ወጣቷ ዳሪያ ዱጊና በ2022 በመኪና ቦምብ ፍንዳታ ተገድላለች።

ጄነራል ያሮስላቭ ሞስካሊክ ባለፈው ዓመት ሚያዝያ ወር ላይ መኪና ላይ የተጠመደ ቦምብ ፈንድቶ የተገደሉ ሲሆን፣ ጄነራል ኢጎር ኪሪሎቭ ደግሞ በታኅሣሥ 2024 በቀላል የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ (ስኩተር) ላይ የተጠመደ ፈንጂ በርቀት መቆጣጠሪያ እንዲፈነዳ ተደርጎ ሕይወታቸው አልፏል።

ምንም እንኳ ይህ በሩሲያ ወገን ባይረጋገጥም አንድ የዩክሬን ምንጭ ግን ኪሪሎቭ በዩክሬን የደኅንነት አገልግሎት መገደላቸውን ለቢቢሲ ተናግሯል።

ዩክሬን በሩሲያ ወታደራዊ ባለሥልጣናት ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን በይፋ አምና ወይም ኃላፊነቱን ወስዳ አታውቅም።