የትግራይ ክልል የ12ተኛ ክፍል ውጤት ከአገር አቀፉ ውጤት ለምን የተለየ ሊሆን ቻለ?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ጦርነት ውስጥ ለከረሙት የትግራይ ክልል የ12ተኛ ክፍል ተማሪዎች ካለፈው መስከረም 29 እስከ ጥቅምት 2/2016 ዓ.ም. የዩኒቨርስቲ መግቢያ ፈተና የተሰጠ ሲሆን፣ በክልሉ በሚገኙት አራቱም ዩኒቨርስቲዎች ውስጥ 9,514 ተማሪዎች ፈተናውን ወስደዋል።
ባለፈው ሳምንት ይፋ በተደረገው የፈተናው ውጤት ከተፈተኑት ተማሪዎች መካከል 66.69 በመቶ የሚሆኑት ወደ ዩኒቨርስቲ ለመግባት የሚያስችላቸውን ነጥብ እንዳመጡ የትግራይ ክልል ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር ኪሮስ ግዑሽ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
በክልሉ የተመዘገበው የ12ተኛ ክፍል ፈተና ውጤት ለሁለት ዓመታት በአገር አቀፍ ደረጃ ከተመዘገበው ጋር ሲነጻጸር በብዙዎች ዘንድ ያልተጠበቀ ሆኗል።
ባለፈው ዓመት መስከረም እና ጥቅምት ወራት ለመጀመሪያ ጊዜ በዩኒቨርስቲ ውስጥ የተሰጠውን የ12ተኛ ክፍል ፈተና ከወሰዱ ተማሪዎች ውስጥ ያለፉት 3.3 በመቶው ብቻ ነበሩ። በሐምሌ ወር ላይ ለሁለተኛ ጊዜ በዩኒቨርስቲዎች ውስጥ ፈተናው ሲሰጥም ማለፊያ ነጥብ ያገኙት 3.2 በመቶው ተፈታኞች ብቻ እንደሆኑ መገለጹ ይታወሳል።
የ12ተኛ ክፍል ፈተና ከፍተኛ ነጥብ በትግራይ
ካለፈው መስከረም ወር መጨረሻ አንስቶ በትግራይ ክልል በተሰጠው ፈተና ከፍ ያለ የማለፍ ምጣኔ ከመመዝገቡም ባሻገር በአገር አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ውጤት ተብሎ ከተያዘው ነጥብ ከፍ ያለ ውጤት ተመዝግቧል። መስከረም ላይ ይፋ በተደረገው መረጃ መሠረት ከፍተኛ ነጥብ የሆነውን 649 ያመጣችው በአዲስ አበባ ከተማ የክሩዝ ትምህርት ቤት ተማሪ የነበረችው ሀናን ናጂ ነበረች።
በዚህ ዓመት በትግራይ ክልል የተሰጠውን ፈተና የወሰደው የቀላሚኖ ልዩ ትምህርት ቤት የተፈጥሮ ሳይንስ ተማሪው ሙሴ ኪዳነ 657 በማምጣት ከፍተኛ ተብሎ ከተያዘው ነጥብ በላይ የሆነ ውጤት አስመዝግቧል።
ጦርነት የተካሄደባቸው ዓመታት ከባድ እንደነበሩ የሚናገረው ሙሴ፤ ማጥናት በቻለባቸው ጊዜያት ዝግጅት ሲያደርግ መቆየቱን ያስታውሳል። “በእርግጥ ይሄንን ውጤት አመጣለው ብዬ አላሰብኩም ነበር፤ ምክንያቱም ፈተና የተፈተንበት ወቅት በትግራይ መርዶ ሲነገር ነበር። ነገር ግን ፈተናው ላይ በደንብ መሥራት አለብኝ ብዬ [ወደ ፈተና] ስለገባሁ ያሰብኩትን አሳክቻለው” ሲል በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ይህንን ውጤት ማግኘቱን ጠቅሷል።
በመቀለ ከተማ የሚገኘው ቀላሚኖ ልዩ ትምህርት ቤት 106 ተማሪዎቹን ለፈተና ማስቀመጡን የትምህርት ቤቱ ርዕሰ መምህር አቶ ፀጋይ ገብረመድኅን ለቢቢሲ ገልጸዋል። ከእነዚህ ተማሪዎች ውስጥ ከስምንቱ ውጪ የሁሉም ውጤት የታወቀ ሲሆን፣ 98 ተማሪዎች የማለፊያ ነጥብ ሲያገኙ ከመካከላቸው 12 ተማሪዎች ደግሞ ከ600 በላይ የሆነ ውጤት ማስመዝገባቸውን ርዕሰ መምህሩ ገልጸዋል።
ከግማሽ በላዩ የማለፋቸው ምክንያት ምንድነው?
የትግራይ ክልል ተማሪዎች “በለጋ እድሜያቸው ያጋጠማቸውን እጅግ ፈታኝ እና ከባድ ወቅት” አልፈው ለፈተና መቀመጣቸውን የሚያስታውሱት የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር ኪሮስ፤ “ውጤቱ ከጠበቅኩት [አንጻር] በተወሰነ መልኩ ከፍ ያለ ነው” ብለዋል።
ይሁንና ትምህርት አቋርጠው ጦርነት ውስጥ የከረሙት የክልሉ ተማሪዎች ይህንን ውጤት ለማምጣታቸው የተለያዩ ምክንያቶች አስተዋጾ አድርገዋል ብለው እንደሚያምኑ ኃላፊው ለቢቢሲ ገልጸዋል።
የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ በቀዳሚነት የሚጠቅሱት ምክንያት አሁን ፈተና የወሰዱት ተማሪዎች በ2010 ዓ.ም የ10ኛ ክፍል አገር አቀፍ ፈተና ወስደው ወደ መሰናዶ ትምህርት ያለፉ መሆናቸውን ነው።
የትምህርት ሚኒስቴር እየተገበረ ባለው አዲስ የትምህርት ፍኖተ ካርታ ምክንያት ከዚህ ቀደም በአገር አቀፍ ደረጃ ይሰጥ የነበረውን የ10ኛ ክፍል ፈተና ከ2012 ዓ.ም ጀምሮ ቀርቷል። በአንጻሩ የ12ተኛ ክፍል ፈተና የዘጠኝ እና 10ኛ ክፍል ትምህርቶችን እንዲያካትት ተደርጓል።
የአሁኑን የ12ተኛ ክፍል ፈተና የወሰዱ የትግራይ ክልል ተማሪዎች ከዚህ ቀደም 10ኛ ክፍል ላይ ተፈትነው ያለፉ መሆናቸው ነጥብ ያላመጡ ተፈታኞች ቁጥር እንዲቀንስ ምክንያት ነው ብለው እንደሚያምኑ ዶ/ር ኪሮስ አስረድተዋል።
“ጎበዝ ተማሪውም፣ ሰነፍ ተማሪውም አልፎ ወደ 12ተኛ ክፍል የሚደርስ ከሆነ፤ [የሚያልፈው ተማሪ] ምጣኔ [ይቀንሳል]። 10ኛ ክፍል ላይ መቀጠል የማይችሉ ተማሪዎችን አስቀርተህ ከሆነ ደግሞ፤ ጎበዝ ተማሪዎች ብቻ ነው ያለፉት ስለዚህ [የሚያልፉ ተፈታኞች] ምጣኔ ከፍ ይላል” ሲሉ ሀሳባቸውን አብራርተዋል።
ከዚህም ባሻገር የትግራይ ክልል ተማሪዎች 10ኛ ክፍል ላይ አገር አቀፍ ፈተና በመውሰዳቸው ምክንያት በተለየ ሁኔታ የዘጠኝ እና 10ኛ ክፍል ትምህርቶች በአሁኑ ፈተናቸው ላይ አለመካተቱት ሁለት የቀላሚኖ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ለቢቢሲ ገልጸዋል።
ለፈተናው ምን አይነት ዝግጅት ተደርጎ ነበር?
የትምህርት ቢሮ ኃላፊው ዶ/ር ኪሮስ በክልሉ ለተገኘው ውጤት የሚጠቅሱት ሌላኛው ምክንያት ተማሪዎቹ ፈተናውን ከመውሰዳቸው በፊት የተደረገውን ዝግጅት ነው።
የክልሉ የ12ተኛ ክፍል ተፈታኞች ከሐምሌ ወር ጀምሮ በትግራይ ክልል በሚገኙት አራቱም ዩኒቨርስቲዎች ገብተው የትምህርት እና የሥነ ልቦና ዝግጅት እንዲሁም ድጋፍ እንዲያገኙ መደረጉን አስታውሰዋል።
ዶ/ር ኪሮስ እንደሚናገሩት ተማሪዎቹ ከሁለት ወራት በላይ በዘለቀው የዩኒቨርስቲ ቆይታቸው እገዛ የተደረገላቸው “በተመረጡ” 240 መምህራን ነው። መምህራኑ ሲያስተምሩ የነበሩት ከተማሪዎች ጋር ዩኒቨርስቲ ገብተው፣ ዶርሚተሪ ይዘው እና ለተማሪዎች የሚቀርበውን ምግብ እየተመገቡ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ለአራት ዓመታት ትምህርት አቋርጠው የቆዩት የትግራይ ክልል ተማሪዎች በአሁኑ ወቅት የ22 ዓመት ገደማ ወጣት መሆናቸው ጥሩ ውጤት ለማስመዝገባቸው ምክንያት ይሆናል የሚል ግምት እንዳላቸውም ዶ/ር ኪሮስ ተናግረዋል። ተማሪዎቹ ዕድሜያቸው ከፍ ከማለቱ ጋር ተያይዞ “ብስለት እንደሚኖራቸው እንዲሁም ትኩረት አድርጎ በአጭር ጊዜ ውስጥ ፈተናን የመሥራት” አቅም እንዳዳበሩ አስረድተዋል።
የትምህርት ቢሮ ኃላፊው ዶ/ር ኪሮስ፤ “ተማሪዎቹ ባለፉት አራት ዓመታት ከትምህርት የተፈናቀሉት፣ ከጓደኞቻቸው ወደኋላ የቀሩት ያለጥፋታቸው ስለሆነ የሚፈጥረው ቁጭት አለ። ይህ ቁጭት ኃይል ነው፤ ብዙ እንዲሠሩ፣ ብዙ ትኩረት እንዲሰጡ የሚያደርግ ነው” ሲሉ ለተገኘው ውጤት ተጨማሪ ምክንያት ነው ያሉትን ጉዳይ ጠቅሰዋል።
ቢቢሲ በጉዳዩ ላይ ከትምህርት ሚኒስቴር እንዲሁም ከትምህርት ምዘና እና ፈተናዎች አገልግሎት ተጨማሪ መረጃ ለማግኘ ያደረገው ጥረት አልተሳካም።












