በ12ኛ ክፍል ፈተና በተደጋጋሚ ለተመዘገበው ዝቅተኛ ውጤት ምክንያቱ ምንድን ነው?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ባለፉት ሁለት የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተናዎች በሚሊዮን የሚቆጠሩ ተማሪዎች ተፈትነው ያለፉት ግን እጅግ በጣም ጥቂት ናቸው።
ባለፈው ዓመት የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ብሔራዊ ፈተና ከወሰዱ እና ባለፉት ሳምንታት ውጤታቸውን ካዩ 845 ሺህ 99 ተማሪዎች መካከል ከ50 በመቶ በላይ ውጤት ያስመዘገቡት 3.2 በመቶ ብቻ ናቸው።
ይህ ለምን ሆነ? የብዙዎች ጥያቄ ነው።
የትምህርት ሚኒስትሩ ፕ/ር ብርሃኑ ነጋ በብሔራዊው ቴሌቪዥን ጣቢያ ላይ ቀርበው የፈተናው ክብደት እና ቅለት ላይ ከዚህ በፊት ከነበረው ምንም የተቀየረ ነገር አለመኖሩን አብራርተዋል።
እንደ እርሳቸው ገለጻ ከሆነ የተለየው ፈተና አሰጣጡ ነው።
“ከዚህ በፊት ፈተናዎች በየትምህርት ቤቶች ውስጥ ነው የሚሰጡት፤ ፈተናው መታተም ከጀመረ ጊዜ ጀምሮ ፈተናዎች ይሰረቃሉ። ፈተና ሲሰረቅ የነበረው በተደራጀ መልክ ነው፤ በክልሎች ፈታኞች በየክልሉ ሲሄዱ ትልቅ ግብዣ ተደርጎ ጉቦ ተሰጥቷቸው፣ ተማሪዎቹ እንዲኮራረጁ ይደረጋል። ውጤቱ ትርጉም ያለው አልነበረም” ሲሉ ተናግረዋል።
ከ40 ዓመት በላይ ያስተማሩት እና የሥነ ትምህርት ፕሮፌሰር የሆኑን አማረ አስገዶም በትምህርት ሚኒስትሩ ሃሳብ ይስማማሉ።
“በእዚህ ሁለት ዓመታት የተቀየረ ነገር ካለ እያንዳንዱ ተፈታኝ የራሱን ፈተና ብቻ መሥራት የሚችልበት ነገር ነው የተደረገው ሌላ የተቀየረ ነገር የለም።
“ፈተናው አልተቀየረም፤ የፈተናው አሰጣጥ ግን ተቀይሯል” ይላሉ።
‘የኢትዮጵያ ዘመናዊ ትምህርት እና ሥልጠና ችግሮች ያስከተሉት ኪሳራ እና መፍትሔዎቻቸው’ የተሰኘ ጥናታዊ መጽሐፍ ያዘጋጁት አቶ ተስፋዬ ለጋም፣ ከአማረ አስገዶም (ፕሮፌሰር) ጋር የመስማሙባቸው ነጥቦች አሉ።
ከአሁን በፊት የነበረው የፈተና አሰጣጥ ሂደት በስርቆት የተሞላ በመሆኑ ፈተና አሰጣጡ ትክክል ነበር ለማለት ያስቸግራል ይላሉ ሁለቱም ምሑራን።
በ2014 እና በ2015 ዓ.ም በድምሩ 1,741,619 ተማሪዎች የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተናን በመላው አገሪቱ ውስደዋል።
ከእነዚህ ውስጥ ያለፉት በድምሩ 57,301 ተፈታኞች ብቻ ናቸው።
ተማሪዎች በዚህ ልክ መውደቃቸው ዜጎችን ያስደነገጠ ቢሆንም፣ ከእነዚህ ተማሪዎች በፊትም የፈተና አሰጣጡ በዚህ መንገድ ቢሆን ውጤቱ ከዚህ እንደማይለይ እና የትምህርት ሥርዓቱ ውድቀት ከታች ጀምሮ የመጣ እንደሆነ የሚገልጹ በርካቶች ናቸው።
ለዚህ ውድቀት ደግሞ ሁሉም ባለድርሻ ኃላፊነት እንዳለበት እና ተማሪዎቹን ከሚያስተምሯቸው መምህራን ብቃት አንስቶ፣ የትምህርት ቤቶች የጥራት ጉዳይ፣ የግብዓት አቅርቦት ሁሉ ሊፈተሽ የሚገባው እንደሆነ የሚያመላክት መሆኑ ይነሳል።
ፕሮፌሰር አማረም ተማሪዎች ለረዥም ጊዜ ጥራት ላይ ያተኮረ ትምህርት እያገኙ ስላልነበረ በአግባቡ እውቀት ይሸምቱ ነበር ለማለት አስቸጋሪ ነው ይላሉ።
“ብዙዎች ፈተናውን እንዲያልፉ ብዙ እውቀት እና ክህሎት አንዲኖራቸው ማድረግ ይቻል ነበር። ነገር ግን የትምህርት ሥርዓቱ ብዛት ላይ እንጂ በጥራት ላይ ያተኮረ አልነበረም።”
ሁለቱም የትምህርት ባለሙያዎች እና ተመራማሪዎች የኢትዮጵያ ትምህርት ችግሩ የመምህራን ብቃት፣ የሥርዓተ ትምህርት፣ የመጻሕፍት አለመኖርም ብቻ አለመሆኑን አጽንኦት ሰጥተው ይናገራሉ።
ፕሮፌሰር አማረ ይህንኑ ሃሳባቸውን ሲያጠናክሩ “ችግሩ የሥርዓት ነው” በማለት ነው።
“ትምህርቱ ራሱ ለተማሪው የሚሆን ሳይሆን ተማሪውን የሚያሰለች እና ተማሪው ትምህርቱን ጓጉቶ እንዲቀበለው የሚያደርግ አይደለም። ሥርዓቱ በትምህርት ላይ ጉልህ የሆነ ጥራት ሊያመጣ አልቻለም።”
ተማሪዎች ትምህርታቸውን በፍጥነት አጠናቅቀው ዲግሪ እንዲይዙ እንጂ ተገቢው ክህሎት እና እውቀት እንዲኖራቸው የሚያደርግ ትምህርት አልነበረንም ይላሉ ፕሮፌሰር አማረ።
አቶ ተስፋዬም ትምህርት ሚኒስቴር “ያልዘራውን ለማጨድ እየሞከረ ነው” ይላሉ።
“በኮረና ወቅት እንዴት ነው ያስተማርኩት፣ አገሪቱ በተለያዩ ግጭቶች ስትታመስ የትምህርት ሥርዓቱን በአግባቡ ለማስኬድ ምንድን ነው ያደረኩት?” የሚል ግምገማ ማካሄድ እንዳለበትም ይመክራሉ።
በትምህርት ዓለም ተማሪ ከፈተና ዓለም ርቆ አያውቅም የሚሉት አቶ ተስፋዬ፣ አሁን ግን ፖለቲካው የፈተናውን ጉዳይ ስለሚያራግበው ፍርሃት መነዛቱን ያነሳሉ።
አክለውም “ስለምን የተፈተኑ ተማሪዎች በሙሉ ወደ ዩኒቨርስቲ እንዲገቡ እንጠብቃለን?” ሲሉ ይጠይቃሉ።

የፎቶው ባለመብት, MINISTRY OF EDUCATION
አሁን ባለው የኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ከተፈታኞች መካከል እጁ ሰርቶ መብላት የሚችል ትውልድ ለማፍራት የቴክኒክ እና ሙያ ትምህርት ቤቶች አማራጮች መሆናቸው ይላሉ።
እንደ እርሳቸው ማብራሪያ በየዓመቱ ከሚፈተኑ ተማሪዎች 85 በመቶው ቴክኒክ እና ሙያ ገብቶ በተለያዩ ክኅሎቶች ሠልጥኖ ራሱን አንዲችል ማድረግ፣ ቀሪውን 15 በመቶ ደግሞ ወደ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በማስገባት ትውልድን መቅረጽ የተሻለ ነው።
“አገርን የምናሳድገው ባለን፣ በቀረጽነው ትውልድ ልክ ስለሆነ እነዚህን ልጆች ወደ ምንፈልገው የልማት መስክ ለማስገባት መሠራት አንዳለበት ነው የማምነው።”
ለፕሮፌሰር አማረ የተማሪዎች ውጤት መውረድ በ12ኛ ክፍል ብሔራዊ መልቀቂያ ፈተና ላይ ብቻ የሚታይ አይደለም።
ወደ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችም ተወርዶ የተማሪዎች የንባብ፣ የጽህፈት ክኅሎት ሲፈተሽ አብዛኛው ከሚጠበቀው በታች እንደሚያገኝ ፕሮፌሰሩ ያነሳሉ።
“ይህ የብሔራዊ መልቀቂያ ፈተና በመሆኑ ብዙ ተወራለት እንጂ፣ በየደረጃው ያሉ ተማሪዎች ተገቢውን እውቀት አለመጨበጥ በተደጋጋሚ በተለያዩ ደረጃዎች ላይ የተስተዋለ እና የሚታወቅ” መሆኑን ይጠቅሳሉ።
በኢትዮጵያ ውስጥ መንግሥት ብቻ ሳይሆን የተለያዩ ለጋሽ ድርጅቶች የትምህርት መሠረተ ልማቶችን ለማሟላት ከፍተኛ መጠን ያለው ሃብት ማፍሰሳቸውን የሚናገሩት ፕሮፌሰሩ፣ ነገር ግን ተገቢውን የትምህርት ጥራት ለማምጣት እንዳልተቻለ ያምናሉ።
ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ እንደ ፕሮፌሰሩ ገለጻ፣ ሥርዓቱ ከመጀመሪያ ጀምሮ ለትምህርት ጥራት የቆመ አለመሆኑ ነው።
“ሥርዓቱ ሕብረተሰቡን ሊያገለግሉት የሚችሉ፣ በኢኮኖሚ ለውጥ ሊያመጡ የሚችሉ ክኅሎት ያላቸው ተማሪዎችን ለመፍጠር የቆመ አይደለም።
“መንግሥት የሚጠየቀው በአካባቢው ትምህርት ቤት ስላልገነባ፣ ትምህርት በሁሉም አካባቢ እንዲዳረስ ስላላደረገ እንጂ የትምህርት ጥራት ስላላመጣ ባለመሆኑ አሁን አገሪቱ ለተገኘችበት ደረጃ ደርሳለች” ይላሉ።
አቶ ተስፋዬ በበኩላቸው የኢትዮጵያ ዘመናዊ ትምህርት ከአጼ ምኒሊክ ጀምሮ በበርካታ ችግሮች ውስጥ እያለፈ በመምጣቱ ችግሮችን በቋሚነት ለማስተካከል “በቀድሞ አስተዳደር፣ በመሠረተ ልማት አለመሟላት፣ በተማሪዎች ድክመት” እና ሌሎች ወዘተርፈዎች ላይ ከማመካኘት ወጥቶ ቆም ብሎ ማሰብ እንደሚያስፈልግ ይመክራሉ።
ለአቶ ተስፋዬ ለጋ በየዓመቱ ከተፈተኑ ተማሪዎች ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚያሳልፋቸውን ነጥብ ያመጡት አነስተኛ ቁጥር ያላቸው መሆናቸውን በመጥቀስ ተስፋ የሚያስቆርጡ ንግግሮችን ደጋግሞ መናገር መቅረት አለበት ይላሉ።
“ይህንን ያህል ትውልድ ብክነት አለው ብሎ በአደባባይ ላይ መናገር ትክክል አይደለም። የትውልድ ብክነትን ማውራት በፍፁም ልክ አይደለም።”
መንግሥት እንደዚህ ዓይነት አባባሎቹን ማቆም ካልቻለ እና ተመሳሳይ ስጋቶችን በተማሪዎች ላይ የሚፈጥር ከሆነ፣ “በየገጠሩ የሚገኙ የገበሬ ልጆች ከትምህርት ዓለም የሚገለሉ ይመስለኛል” ሲሉ ስጋታቸውን ገልጸዋል።
ተማሪዎች በዚህ ጦርነት ውስጥ፣ በኮረና ወረርሽኝ ውስጥ ለፍተው እንደተማሩ መረዳት ያስፈልጋል የሚሉት አቶ ተስፋዬ፣ አሁን ዝቅተኛ ውጤት መመዝገቡን የሚያይ ተማሪ ለምን ትምህርት ቤት እሄዳለሁ በማለት፣ ነገ ያልተማረ ትውልድ እንዳይበዛ ስጋት አላቸው - አቶ ተስፋዬ።
ለዚህም መፍትሄው የተማሩትን ወደ ቴክኒክ እና ሙያ እንዲሁም ወደ ከፍተኛ ተቋም የሚገቡ በሚል መለየቱ አስፈላጊ እርምጃ መሆኑን ይመክራሉ።












