በአገር አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገበችው ሃናን ናጂ ስለውጤቷ ምን አለች?

የፎቶው ባለመብት, FBC
ብዙ ተማሪዎች የወደቁበት የአገር አቀፍ የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተናን 649 ነጥብ በማምጣት ከፍተኛውን ውጤት ያስመዘገበችው በአዲስ አበባ የክሩዝ ትምህርት ቤት ተማሪ ሃናን ናጂ ናት።
ሃናን ጊዜዬን በአግባቡ መጠቀሜ ለዚህ አብቅቶኛል ስትል ከቢቢሲ ጋር ባደረገችው ቆይታ ተናግራለች።
ቢቢሲ- እንኳን ደስ አለሽ?
ሃናን- እንኳን አብሮ ደስ አለን።
ቢቢሲ- ውጤቱን ልክ ስትሰሚ የት ነበርሽ?
ሃናን- ትናንትና [ሰኞ ዕለት] መግለጫ እየተሰጠ ነበር።መግለጫውንም እያዳመጥኩ አልነበረም። እና በመሃል ከፍተኛ ውጤት የተመዘገበው ከክሩዝ ትምህርት ቤት ነው፣ ሴት ነች ሲባል ጓደኞቼ ደውለውልኝ ነው የሰማሁት።
ከዚያ ሁሉም 'አንቺ ነሽ፣ አንቺ ነሽ' ሲሉ . . . ሁሉም ያሰበው እንደዚያ ስለሆነ፣ ያኔ ነው ያወቅኩት ማለት ይቻላል።
እኔ ላልሆን እችላለሁ ብዬ ጥርጣሬ ነበረኝ፤ ነገር ግን ያኔ ነው ያወቅኩት ማለት ይቻላል።ላለማመን ሞክሬያለሁ ግን ያኔ ነው ያወቅኩት።
ቢቢሲ- አንቺ መሆንሽን ስታውቂ ምን ተሰማሽ?
ሃናን - (ሳቅ) በጣም ደስ ይላል። ከዚያ ሁሉ ተማሪ. . . ጥሩ እንደሚሆን ብገምትም ከሁሉም ተማሪ ከፍተኛ ውጤት ማምጣት ደግሞ የተለየ ስሜት ነው ያለው።
ቢቢሲ- ብዙ ተማሪ አላለፈም ዘንድሮ። ፈተናው ከብዶ ነው ወይስ ምንድን ነው የሆነው?
ሃናን- ፈተናው ከባድ ነው የሚባል አይደለም።ከተዘጋጁበት የሚሰራው ፈተና ዓይነት ነው።
ቢቢሲ- በጣም ብዙ ተማሪ ወደቀ። ምንድን ነው የሆነው ታድያ?
ሃናን- ምክንያቱም ተማሪ መዘጋጀት ላይ አልነበረም።ዝግጅት ሲባል በዚህ ዓመት ብቻ ሳይሆን ከሥር ጀምሮ ነው መሆን ያለበት።አብዛኛውን ጊዜ ልክ ሀይስኩል ሲጀምሩ ነው እንደዚያ የሚሆነው።አብዛኛው ተማሪ ትኩረቱ ወደ ሌላ ነገር ነው የሄደው። ይህ ፈተና የመኮረጅ ዕድል አልነበረውም። በዚያ ምክንያት መሥራትም አልቻሉም። ለዚያም ነው ብዙ ተማሪ የወደቀው ብዬ አስባለሁ።
ቢቢሲ- አንቺን ለዚህ ያበቃሽ ነገር ምንድን ነው?
ሃናን- የእኔ ብቻ ነው ብዬ መውሰድ አልችልም። የብዙ ነገሮች ድምር ነው። ነገር ግን ለራሴን ጥረት ዋጋ እሰጣለሁ። ምክንያቱም በጣም ጥሬበታለሁ ማለት ነው።ያለኝ ጥሩ ጎን ብዬ የማስበው ጊዜ አጠቃቀሜን ነው። የሚሻለው ነገር ላይ ነው ሰዓቴን ማጥፋት የምመርጠው። አብዛኛውን ጊዜ ደግሞ የሚሻለው ነገር ማንበብ ነው።
ቢቢሲ- ፌስቡክ፣ ኢንስታግራም አለሽ?
ሃናን- ከፈተናው በኋላ ነው የከፈትኩት።
ቢቢሲ- ትምህርት ራሱ ያዝናናሻል እነዴ?
ሃናን - አዎ (ሳቅ) አብዛኛውን ጊዜ ሳነብ ምናምን ከእራሴ ጋር ዘና እያልኩ ነው፣ አዲስ ነገር ሳውቅ በጣም ደስ እያለኝ . . . ከራሴ ጋር እያወራሁ የምደሰትባቸው ጊዜያቶች አሉ።ትምህርት እስከማይመስል ድረስ። አይሰለቸኝም እዝናናበታለሁ።
ቢቢሲ- የትኛውን የትምህርት ዓይነት ነበር የበለጠ የምትወጂው?
ሃናን- ከሁሉም የበለጠ ፊዚክስ ይመስለኛል።
ቢቢሲ- ለምንድን ነው የምትወጂው?
ሃናን - የአስተማሪ ተጽዕኖ ይኖራል መሰለኝ። ጥሩ አስተማሪዎች ስለነበሩኝ እና ፊዚክስ ትምህርቱም ደስ ይላል። ባዮሎጂ ምናምን ሲሆን ብዙ ጊዜ የሚሸመደዱ ፋክቶች ናቸው። ፊዚክስ ሲሆን ግን የበለጠ መሥራትና ጥረት የሚጠይቅ ነው።
ቢቢሲ- ጌም [ጨዋታ] ሆኖ ነው የሚሰማሽ?
ሃናን- [ሳቅ] ያን ያህል ባይሆንም በቃ ደስ ይለኛል።
ቢቢሲ- ወደፊት ማጥናት የምትፈልጊው ምንድን ነው?
ሃናን- አሁን በጣም ፍላጎት ያለኝ ፋርማኮሎጂ ነው። ስለ መድኃኒት መሥራት እና በዚያ ዙሪያ ያለ የጥናት ዘርፍ ነው ትምህርቱ።
ቢቢሲ- ከኮቪድ በኋላ የመጣ ሃሳብ ይመስላል?
ሃናን- በዚያም ጊዜ ያሰብኩት ነው፤ ግን ኮቪድ ብቻ ያመጣው ሳይሆን እሱ አካባቢ ላይ ብዙ የሚሰራበት ይመስለኛል። እኔም መመራመር ምናምን ነው የምፈልገው።እንደዚህ ዓይነት ነገር ላይ ዝንባሌ ስላለኝ እዚያ ላይ ብሰራ ደስ ይለኛል።
ቢቢሲ- በሕይወትሽ ዝቅተኛ ውጤት ያመጣሽው ምን ትምህርት ነው?
ሃናን- (ሳቅ) እንጃ አላስታውስም። ሁሉንም ትምህርቶች 100 አምጥቼ ስለማውቅ እኔን'ጃ፣ ይሄ ነው ብዬ ማለት አልችልም።
ቢቢሲ - የነጋዴ ልጅ ነሽ። እና ለምንድን ነው የምትደክመው ጥሩ ኑሮ አትኖርም እንዴ ከእነርሱ ጋር የሚሉ አሉ። ምን ትያለሽ?
ሃናን- ብር እየኖረኝ መኖር ብችል እንኳ በሕይወቴ ደስተኛ አልሆንም። ብሩ ስላለኝ ብቻ ደስተኛ አልሆንም። ደስተኛ የሚያደርገኝ በጣም የምፈልገው ነገር [ፓሽኔት የሆንኩበት] ነገር እያለ ለምን ወደ አነሰ ነገር እሄዳለሁ እላለሁ።
ቢቢሲ- ያነሰ ነገር ነው የምትይው ብርን ነው?
ሃናን- አዎ ምክንያቱም ዱንያ [ሃብት] ነው።ይጠፋል እኮ ብር።
በሃናን ውጤት ከፍተኛ ደስታ ከተሰማቸው የቤተሰቧ አባላት መካከል እናቷ ሹክሪያ ሺፋን አንዷ ናቸው። “አንደኛ በወጣች ቁጥር ሰዓት እየሸለምኩ አበረታታት ነበር” በማlት አንዴት እያበረታቷት እንዳደገች እናገራሉ።
እናት- ሃናን ሲበዛ በጣም ጎበዝ ተማሪ ናት።ለትምህርቷ ነው ብዙ ሰዓቷን መስዋዕት አድርጋ የምትሰጠው። እና አላምዱሉላሂ አላህ ደግሞ ዛሬ ደርሶ በውጤቷ እንዲህ አኩርቶናል።ሶሻል ሚዲያው ላይ ምንም የምታሳልፈው ነገር የለም።
ቢቢሲ- ፌስቡክ የላትም አንዴ?
እናት- ፌስቡክ ምናምን ተጠቃሚ አይደለችም።
ቢቢሲ- ፊልም ታያለች።
እናት- ሃናን ብዙ ሰዓቷን የምታሳልፈው ጥናት ላይ ነው።እረፍት አድርጊ ብለን እንኳ ስንቆጣት ክፍሏ ገብታ፣ በጣም ጫጫታ የሌለበት ቦታ መርጣ ነው እንጂ ፌስቡክ ላይ ምናምን አይደለም።
ቢቢሲ- እራት ሰዓት ሲደርስ ነይ ውጪ እራት በጋራ እንብላ ስትሏት ትወጣለች?
እናት- ትመጣለች።
ቢቢሲ- ቆይ ይህችን ልጨርስ ብላ አታስቸግርም?
እናት- አታስቸግርም።ዝምተኛ ናት፣ ግን መናገር ያለባትን ነገር ትናገራለች።
ቢቢሲ - ሃናን በምንድን ነው የምትዝናናው?
እናት- እኔ ሃናን የምትዝናናበት ነው የምለው ነገር የለኝም።ብዙ ጊዜ ሰዓቷን ጥናት ላይ፣ ደብተር ላይ፣ ጥናት ላይ ምናምን ስታሳልፍ ስለምትውል ይኼ ነው ብዬ ልል አልችልም።መዝናኛ እንኳ ሄደን ስልኳን ከፍታ ነው የምታጠናው።ጊዜ ማባከን አትፈልግም።አንዳንዴ አእምሮዋ እረፍት ያድርግ ብለን ይዘናት ስንወጣ የተወሰነ ሰዓት ትቆይና ወዲያው ስልኳን ከፍታ ወደ ጥናቷ ነው የምትገባው።በዚያ ምክንያት እኔም ይህንን ውጤት ጠብቄዋለሁ።
ቢቢሲ -በአገር አቀፍ ደረጃ አንደኛ ትሆናለች ብለው?
እናት- አንደኛ ትወጣለች ሳይሆን ጥሩ ውጤት ታመጣለች በሚለው እኔ በጣም እርግጠኛ ነበርኩ።ሙሉ በሙሉ ማለት ነው።
ቢቢሲ- አሁን ምንድን ነው የምትሸለመው?
እናት- አንደኛ ስትወጣ እስከ ስምንተኛ ባለው ክፍል ሰዓት ነበር የምንሸልማት። “እማማ አንቺ ሁሌ ለምንድን ነው ሰዓት የምትሸልሚኝ?” ስትለኝ ምክንያት እንዳለኝ እና ሁሉም ነገር በሰዓቱ መደረግ እንዳለበት እና ያለፈን ነገር መመለስ እንደማይቻል ለማስረዳት እንደሆነ ነገርኳት። “እውነትሽን ነው እማማ አለችኝ”። ዛሬ ላይ አላምዱሊላሂ ያንን ምክር ተጠቅማበታለች ብዬ አስባለሁ።
ቢቢሲ -ስለዚህ ግራ እጇ፣ ቀኝ እጇ ሰዓት ብቻ ነው? (ሳቅ)
እናት - (ሳቅ) ክፍሏ ሁሉ ሰዓት ብቻ ነው።












