የ12ኛ ክፍል ፈተናን ከወሰዱት መካከል 96 በመቶዎቹ 50% አላመጡም

የፎቶው ባለመብት, SM
ባለፈው ዓመት የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ብሔራዊ ፈተና ከወሰዱ 845 ሺህ 99 ተማሪዎች መካከል 50 እና ከዚያ በላይ ውጤት ያስመዘገቡት 27 ሺህ 267 ተማሪዎች ብቻ መሆናቸውን ትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ።
ይህም ማለት ፈተናውን ከወሰዱት ውስጥ ከ50 በመቶ በላይ የሆነውን ውጤት ያስመዘገቡት 3.2 በመቶ የሆኑት ብቻ ናቸው።
በማታው የትምህርት ክፍለ ጊዜ ተምረው ፈተናውን ከወሰዱ 16 ሺህ 451 ተማሪዎች መካከልም ከ50 በመቶ በላይ ውጤት ያስመዘገቡት12ቱ ብቻ ሲሆኑ፣ ይህም በመቶኛ ሲሰላ 0.1 በመቶ ነው።
ይህ የተገለጸው በሐምሌ ወር በመላው አገሪቱ የተካሄደው የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ብሔራዊ ፈተና ውጤትን አስመልክቶ ትምህርት ሚኒስቴር ዛሬ ሰኞ መስከረም 28 ቀን/2016 ዓ.ም. በሰጠው መግለጫ ነው።
በከተማ እና በገጠር ባሉ ትምህርት ቤቶች በተመገበው ውጤት መካከል ልዩነት እንዳለም ሚኒስቴሩ ጨምሮ ገልጿል።
ዛሬ የተገለጸው ውጤት ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር በ0.1 በመቶ ቅናሽ ማሳየቱም ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ አመልክቷል።
በ2014 ዓ.ም. ፈተና ላይ የተቀመጡት 896 ሺህ 520 ተማሪዎች ሲሆኑ፣ ከእነዚህ መካከል ከ50 በመቶ በላይ ውጤት ያስመዘገቡት 30 ሺህ 034 ነበሩ።
በኩረጃ እና በፈተና ስርቆት ለበርካታ ዓመታት ችግር ሲገጥመው የነበረው የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ብሔራዊ ፈተናን ተአማኒነት ለመጠበቅ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአገሪቱ ባሉ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ በጥብቅ ቁጥጥር ስር ሆኖ እንዲሰጥ መደረጉ ይታወቃል።
ባለፈው ዓመት ሐምሌ ወር ላይ በተሰጠውን የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ብሔራዊ ፈተና ከወሰዱ የተፈጥሮ ሳይንስ ተማሪዎች መካከልም 5.3 በመቶዎቹ 50 በመቶ እና ከዚያ በላይ አምጥተዋል።
1.7 በመቶ የሚሆኑት የማኅበራዊ ሳይንስ ተማሪዎች በተመሳሳይ የማለፊያ ነጥብ አስመዝግበዋል።
ይፋ በተደረገው ውጤት መሠረት በተፈጥሮ ሳይንስ ዘርፍ 649 ነጥብ ከፍተኛ ውጤት ሆኖ የተመዘገበ ሲሆን፣ በማኅበራዊ ሳይንስ ዘርፍ ደግሞ ከፍተኛው ነጥብ 533 መሆኑ ተገልጿል።
ባለፈው ዓመት የፈተና አሰጣጥ ሒደት ላይ በአማራ ክልል ውስጥ ካጋጠመው ግጭት ጋር በተያያዘ እና በአንዳንድ አካባቢዎች ባጋጠሙ ክስተቶች የፈተና መስጠት ሂደቱ መስተጓጎል ገጥሞት እንደነበር ይታወሳል።
የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ፣ የ2015 አገር አቀፍ የ12 ክፍል መልቀቂያ ብሔራዊ ፈተና ከዚህ ቀደም ያጋጥሙ ከነበሩ የኩረጃ እና የስርቆት ችግሮች በፀዳ ሁኔታ ተሰጥቶ መጠናቀቁን በወቅቱ አስታውቀው የነበረ ሲሆን፣ የሰው ሕይወት የጠፋባቸው ክስተቶች መፈጠራቸውንም ገልጸው ነበር።
ለሁለተኛ ጊዜ በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ውስጥ በተሰጠው ያለፈው ዓመት ብሔራዊ ፈተናን ለመውሰድ 868,074 ተማሪዎች ተመዝግበው 845,099 ተማሪዎች መፈተናቸውን ትምህርት ሚኒስቴር መግለጹ ይታወሳል።












