የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ተጠናቀቀ፣ በጎንደር አንድ ፈታኝ በታጣቂዎች ጥቃት ተገደለ

ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ፣ የትምህርት ሚኒስትር

የፎቶው ባለመብት, ena

የምስሉ መግለጫ, ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ፣ የትምህርት ሚኒስትር

በሐምሌ ወር በመላው አገሪቱ ሲካሄድ የነበረው የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ብሔራዊ ፈተና የተጠናቀቀ ሲሆን በአማራ ክልል ባለው የፀጥታ ችግር ጋር በተያያዘ የአንድ ፈታኝ ሕይወት እንዳለፈ ተገለጸ።

የ2015 አገር አቀፍ የ12 ክፍል መልቀቂያ ብሔራዊ ፈተና ከከዚህ ቀደም ያጋጥሙ ከነበሩ የኩረጃ እና የስርቆት ችግሮች በፀዳ ሁኔታ ተሰጥቶ መጠናቀቁን ያሳውቁት የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ፣ የሰው ሕይወት የጠፋባቸው ክስተቶች መፈጠራቸውንም ገልጸዋል።

በአማራ ክልል ለወራት በቆየው እና ባለፉት ቀናት ከተባባሰው የፀጥታ ችግር ጋር በተያያዘ በጎንደር ዩኒቨርስቲ ማራኪ፣ ቴዎድሮስ እና ፋሲል ካምፓሶች አካባቢ ታጣቂዎች ከመከላከያ ሠራዊት ጋር ባደረጉት የተኩስ ልውውጥ ምክንያት በፈተናው ሂደት ተሳታፊ የሆኑ ሰዎች ተገድለዋል።

በዚህም አንድ ፈታኝ መምህር እና ሁለት የፌደራል ፖሊስ አባላት የሞቱ ሲሆን ሌላ የፌደራል ፖሊስ አባል በጥቃቱ ምክንያት የመቁሰል ጉዳት እንደደረሰበት የትምህርት ሚኒስትሩ ተናግረዋል።

በጎንደር አዘዞ እና ማራኪ በተሰኙ አካባቢዎች ሐሙስ እኩለ ቀን ድረስ የተኩስ ድምጽ እየተሰማ መሆኑን ቢቢሲ ያነጋገራቸው የከተማዋ ነዋሪ ገልጸዋል።

በጎንደር ከተማ አውሮፕላን ማረፊያ አካባቢም ግጭት በመፈጠሩ የትራንስፖርት አገልግሎት መቆሙን ነዋሪዎች ለቢቢሲ በወቅቱ ተናግረዋል።

በጎንደር ዩኒቨርስቲ ባጋጠመው ከባድ የደኅንነት ችግር ምክንያት በዩኒቨርስቲው ውስጥ የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና መውሰድ የነበረባቸው 16 ሺህ የሚበልጡ ተማሪዎች ተወሰኑ ፈተናዎችን ሳይወስዱ መቅረታቸው ተገልጿል።

በተጨማሪም በሌሎች ሁለት ዩኒቨርስቲዎች ተፈታኝ የነበሩ ተማሪዎች ቀደም ሲል በነበረ የጤና ችግር ምክንያት ሕይወታቸው ያለፈ ሲሆን፣ በጋምቤላ ዩኒቨርስቲ የጤና ሳይንስ እና የመምህራን ማሰልጠኛ ኮሌጅ ውስጥ ተፈታኝ ከነበሩ ተማሪዎች መካከል 38ቱ በምግብ መበከል ምክንያት በመታመማቸው ሳይፈተኑ መቅረታቸውን ፕሮፌሰር ብርሃኑ ገልጸዋል።

በኩረጃ እና በፈተና ስርቆት ለበርካታ ዓመታት ችግር ሲገጥመው የነበረው የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ብሔራዊ ፈተናን ተአማኒነት ለመጠበቅ ካለፈው ዓመት ጀምሮ በአገሪቱ ባሉ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ እንዲሰጥ መደረጉ ይታወቃል።

በትግራይ ክልል ለሁለት ዓመት የዘለቀውን ደም አፋሳሽ ጦርነት ተከትሎ ከ2012 ዓ.ም ጀምሮ የ12ኛ ክፍል ያጠናቀቁ ተማሪዎች እንዳልተፈተኑም ተገልጿል።

በአሁኑ ወቅትም እነዚህ ተማሪዎች ማጠናከሪያ እና የማካካሻ ትምህርት እየተሰጣቸው መሆኑ ተገልጾ ከመስከረም 29 እስከ ጥቅምት 2 ቀን 2016 ዓ.ም ድረስ ፈተናውን ለመስጠት ዝግጅት እየተደረገ መሆኑንም ዶክተር ብርሃኑ መናገራቸው በመግለጫው ሰፍሯል።

ለሁለተኛ ጊዜ በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ውስጥ በተሰጠው የዚህ ዓመት ብሔራዊ ፈተናን ለመውሰድ 868,074 ተማሪዎች ተመዝግበው 840,859 ተማሪዎች መፈተናቸውን ትምህርት ሚኒስትሩ ገልጸዋል።

የ2015 ዓ.ም. የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ብሔራዊ ፈተና በአማራ ክልል ውስጥ ባለው የፀጥታ መደፍረስ ጋር በተያያዘ ጎንደር ውስጥ ከተከሰተው ችግር ውጪ ከአንዳንድ የሥነ ምግባር ግድፈቶች ባሻገር ያለ ምንም ኩረጃ እና ስርቆት በሰላም መጠናቀቁን ሚኒስትሩ ገልጸዋል።