አሜሪካ በሶማሊያ የአይኤስ ከፍተኛ አመራር ነው የተባለ ግለሰብን መግደሏን አስታወቀች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
አሜሪካ የልዩ ኃይል ወታደሮቿ ሶማሊያ ውስጥ የኢስላሚክ ስቴት ከፍተኛ አመራር የሆነ ቁልፍ ሰውን ጨምሮ 10 ረዳቶቹን መግደላቸውን ገለጸች።
አሜሪካ ገደልኩ ያለችው የአይኤስ ቁልፍ ሰው ቢላል አል ሱዳኒ የሚባል ሲሆን፣ በአፍሪካ እና ከዚያ ባሻገር እስላማዊ ታጣቂ ቡድኖችን በገንዘብ እና ቁሳቁስ በመደገፍ እና በማስፋፋት ትልቅ ሚና ነበረው ተብሏል።
አልሱዳኒ የተገደለው የአሜሪካ ወታደሮች በሰሜናዊ ሶማሊያ በምትገኝ ተራራ ላይ ባለ ዋሻ እርሱን ለመያዝ ዘመቻ ባደረጉበት ወቅት በተካሄደ የተኩስ ልውውጥ ወቅት ነው።
የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስትር ሎይድ ኦስቲን የተወሰደውን እርምጃ በተመለከተ በሰጡት መግለጫ “ስኬታማ የሆነ የፀረ ሽብር ዘመቻ” በማለትበሂደቱ ንፁሃን አለመጎዳታቸውን አመልክተዋል።
ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተሉ ተንታኞች አል ሱዳኒን ለመያዝ አልያም ለመግደል አሜሪካ ድሮን ከመጠቀም ይልቅ የልዩ ኃይል ወታደሮችን ማሰማራቷ ግለሰቡ ቁልፍ ሰው መሆኑን ያሳያል ብለዋል።
አሜሪካ የሶማሊያ መንግሥት ሠራዊት በአልሻባብ ላይ እያካሄደ ላለው ዘመቻ ድጋፍ እንደምታደርግ ይታወቃል።
በቅርቡም የአሜሪካ አየር ኃይል በሶማሊያ በፈጸመው ጥቃት 30 የሚደርሱ የአልሸባብ ቡድን አባላት መገደላቸውን የአሜሪካ ሠራዊት አስታወቆ ነበር።
የሶማሊያ መንግሥት በአልሸባብ ላይ የተጠናከረ ወታደራዊ ዘመቻ እየወሰደ ባለበት በዚህ ወቅት ታጣቂ ቡድኑ በበኩሉ ተደጋጋሚ ጥቃቶችን እያደረሰ ይገኛል።
አሜሪካ ሶማሊያ የምታካሄደውን ዘመቻ ለመደገፍ የድሮን ጥቃቶችን በማድረግ ድጋፍ ስትሰጥ ቆይታለች።
አዲሱ የሶማሊያ ፕሬዝዳንት ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ ከጎሳ ታጣቂዎች ጋር ሠራዊታቸውን በማቀናጀት በወሰዷቸው ወታደራዊ እርምጃዎች በአልሻባብ ቁጥጥር ስር የነበሩ በርካታ ስፍራዎችን ለመያዝ ችለዋል።
ለዓመታት ሰፊውን የሶማሊያን ግዛት በመቆጣጠር ማዕከላዊውን መንግሥት ሲፈትን የቆየው አልሻባብ ከአይኤስ ጋር ግንኙነት እንዳለው ይታመናል።
አልሻባብ በአፍሪካ ውስጥ አደገኛ ከሚባሉት የሽብር ቡድኖች መካከል ቀዳሚው ሲሆን፣ በበርካታ አገራትም በሽብር ቡድንነት ተፈርጇል።
አልሻባብ ከሶማሊያ ባሻገር በተለያዩ ጎረቤት አገራት ውስጥ ጥቃቶችን ሲፈጽም የቆየ ቡድን ሲሆን፣ ኢላማውም ምዕራባውያንን እና ተቋማቶቻቸውንም ያካትታል።
አሜሪካም ቡድኑን ለመወጋት ለሶማሊያ እና ለአካባቢው አገራት ድጋፍ እያደረገች ሲሆን፣ የምትፈልጋቸውን የቡድኑን አመራሮች ለሚጠቁሙ ሰዎችም በሚሊዮን የሚቆጠር ዶላር ሽልማት ለመስጠት በተደጋጋሚ ቃል መግባቷ ይታወቃል።












