ማንቸስተር ሲቲ ከአርሰናል፡ ተጠባቂውን ጨዋታ ማን በድል ይወጣል?

የኤፍኤ ዋንጫ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

አራተኛው ዙር የኤፍኤ ዋን ጨዋታ ከአርብ ምሽት ጀምሮ ቅዳሜ፣ እሑድ እና ሰኞ ይከናወናል።

በእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ አናት ላይ ቁጭ ያለው አርሰናል ወደ ማንቸስተር ከተማ ተጉዞ ሲቲን ይገጥማል።

የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ አርብ ምሽት አምስት ሰዓት ይጀምራል።

ማንቸስተር ሲቲ ከአርሰናል በእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ እንደገና በሚቀጥለው የፈረንጆቹ ወር የሚገናኙ ይሆናል።

የሲቲው አሠልጣኝ ፕፔ ጉዋርዲዮላ በአገር ውስጥ የዋንጫ ውድድሮች ቀልድ አያውቅም። አብዛኛውን ጊዜ ጠንካራ ቡድን ይዞ ነው ወደሜዳ የሚዘልቀው።

ነገር ግን ከፕሪሚዬር ሊግ አናት የሚገኘው አርሰናል በዋናው ቡድን አሊያም በተቀያሪ ይምጣ የሚታወቅ ነገር የለም።

እርግጥ ነው አርሰናል ለፕሪሚዬር ሊጉ እንጂ ለኤፍ ኤ ዋንጫ ቅድሚያ አይሰጥም። ነገር ግን አሁን አርሰናል ካለበት አቋም አንፃር ከሲቲ ጋር የሚኖራቸውን ፍልሚያ ማየት አጓጊ ይሆናል።

ከጉዋርዲዮላ ምክትል አሠልጣኞች መካከል አንዱ የነበረው ማይክል አርቴታ ሲቲን ይረታ ይሆን?

የቢቢሲ ስፖርት ተንታኙ ክሪስ ሱቶን ፍልሚያውን ማንቸስተር ሲቲ 2-1 ይረታል ይላል።

የሲቲ እና አርሰናል አርማ

ቅዳሜ ዕለት ከሚደረጉ ጨዋታዎች መካከል የፕሪሚዬር ሊጉ ሊድስ ዩናይትድ አርኪንግተንን 2-0፤ ሌይስተር ሲቲ ዋልሳልን 2-1 ይረታሉ ይላል ሱቶን።

ብላክበርን በርሚንግሃም ሲቲን 1-0፣ ብሪስቶል ሲቲ ዌስትብሮምን 2-1፣ ፉልሃም ሰንደርላንድ 3-0፣ በርንሊ ኢፕስዊችን 4-0 የክሪስ ግምቶች ናቸው።

ተንታኙ ቀጥሎ ሼፊልድ ዌንስዴይ፤ ፍሊትውድን 1-0 ያሸንፋል፣ ሳውዝሃምፕተን ደግሞ ብላክፑልን 4-0 ይረመርማል ይላል።

ባለፈው ሰኞ በእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ ፉልሃምን በመርታት አምስተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠው ቶተንሃም ሆትስፐርስ ፕሪስተንን ያሸንፋል ይላል ሱቶን።

እንደሱ ግምት ጨዋታው 1-0 ይጠናቀቃል።

ቅዳሜ ምሽት 5፡00 ማንቸስተር ዪናይትድ ሬዲንግን ያስተናግዳል።

የማን ዩናይትድ እና ሬዲን አርማ

የሬዲንግ አሠልጣኝ ፖል ኢንስ በተጫዋችነት ዘመኑ ከማንቸስተር ዩናይትድ ጋር የኤፍ ኤ ዋንጫ ማንሳቱ ይታወሳል።

ነገር ግን “ወደ ዩናትድ መጥቶ ድል ቀንቶት ይመለሳል የሚል ግምት የለኝም” ይላል ክሪስ ሱቶን።

የማንቸስተር ዩናይትዱ አሠልጣኝ ኤሪክ ቴን ሃግ ለዋንጫ ጨዋታዎች ፊት የማይሰጡ ሆነው ተገኝተዋል። በያዝነው ሳምንት በካራባዎ ዋንጫ ኖቲንግሃም ፎረስትን መርታታቸው ይታወሳል።

ሱቶን እንደሚለው ቅዳሜ ምሽት የሚካሄደውን ፍልሚያ ዩናይት 3-0 ያሸንፋል።

እሑድ ብራይተን ከሊቨርፑል ይገናኛሉ።

“የሊቨርፑል ደጋፊዎች ይቅርታ አድርጉልኝና እኔ እንደ ቀድሞው ክብር ልሰጣችሁ አልችልም” ይላል ክሪስ ሱቶን።

ብራይተን ባለፈው ወር ሊቨርፑልን በፕሪሚዬር ሊጉ 3-0 መርታቱ ይታወሳል። አሁንም ቢሆን ጥሩ ጨዋታ ብናይም ድል ግን ከብራይተን ጋር ናት በማለት ጨዋታ 4-3 እንደሚጠናቀቅ ይገምታል።

በሌሎች ፍልሚያዎች ሰቶክ ሲቲ ከስቴቬኔጅ 1 አቻ፤ ሬክስሃም ከሼፊልድ ዩናይትድ በተመሳሳይ አንድ አቻ፤ ደርቢ ዌስትሃምን 1-0 ይረታሉ ሲል የኤፍ ኤ ዋንጫ አራተኛ ዙር ጨዋታዎች ግምቱን ያጠናቅቃል።