ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ከአንድ ዓመት በፊት የታሰሩት የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክር ቤት አባል አዲስ ሦስተኛ ክስ ተመሠረተባቸው
በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ሕገ መንግሥት ማሻሻያ ላይ አቤቱታ ካቀረቡ በኋላ የታሰሩት የክልሉ ምክር ቤት አባል አቶ ዮሐንስ ተሰማ፤ አዲስ ሦስተኛ ክስ እንደተመሠረተባቸው የቤተሰብ አባላቸው ተናገሩ።
ከዚህ ቀደም ከሽብር እና ከሊዝ አዋጅ ጋር የተያያዙ ክሶች በቀረቡባቸው የምክር ቤት አባሉ ላይ የተመሠረተው አዲስ ክስ፤ "የሙስና ወንጀል አዋጅን መተላለፍ" የሚል ነው።
ላለፈው አንድ ዓመት ገደማ እስር ላይ ያሉት የክልል ምክር ቤት አባሉ አቶ ዮሐንስ፤ በአሶሳ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ለቀረበባቸው አዲስ ክስ የቀጠሮ መጥሪያ የደረሳቸው ትናንት ረቡዕ የካቲት 18/2018 ዓ.ም. እንደሆነ አንድ የቤተሰብ አባል ለቢቢሲ ተናግረዋል።
አቶ ዮሐንስ ባለፈው ዓመት የካቲት ወር ላይ ከታሰሩ በኋላ ከአምስት ዓመት በፊት ተቋርጦ በነበረ "ከሊዝ አዋጅ ስሪት ውጪ የከተማ መሬት አስፋፍቶ በመያዝ" ክስ አምስት ዓመት ከ10 ወር ተፈርዶባቸዋል።
ይግባኝ የቀረበለት የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የቅጣት ውሳኔውን ወደ አራት ዓመት ዝቅ ያደረገው ሲሆን፣ አሁንም ጉዳዩ በፌደራል ሰበር ሰሚ ችሎት አቤቱታ ቀርቦበት ቀጠሮ ላይ ነው።
ባለፈው ጥር ላይ ደግሞ ከሽብር ጋር በተያያዘ የተመሠረቱባቸውን ሌሎች ሦስት ክሶች ሲመለከት የነበረው የአሶሳ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ነጻ እንደሆኑ ወስኖላቸዋል።
አቶ ዮሐንስ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክር ቤት አባል በመሆን ያገኙት ያለመከሰስ መብት እንዲነሳ የተደረገው ከእነዚህ ክሶች ጋር በተያያዘ ነበር።
ክሶቹ "ሕዝብን ከሕዝብ ማጋጨት፣ ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ከፍተኛ አመራሮችን መሳደብ እና ከውጭ አካላት ጋር ግንኙነት መፍጠር" የሚሉ እንደነበሩ ጉዳዩን የሚከታተሉት የቤተሰብ አባላቸው በወቅቱ ለቢቢሲ ተናግረው ነበር።
ፍርድ ቤቱ አቶ ዮሐንስን በነጻ ያሰናበታቸው ክሱን የመሠረተው ዐቃቤ ሕግ "ምስክሮችን ማቅረብ ስላልቻለ" እንደሆነም ገልጸዋል።
ረቡዕ ዕለት ለምክር ቤት አባሉ የደረሰው አዲስ ክስ ደግሞ አቶ ዮሐንስ የክልሉ የሥራ አመራር ተቋም ዋና ዳይሬክተር በነበሩበት ወቅት ተፈጽሟል የተባለ ነው።
የምክር ቤት አባሉ ከጥቅምት 2014 ዓ.ም. አንስቶ እስከታሰሩበት ጊዜ ድረስ ከሦስት ዓመት በላይ ለሚሆን ጊዜ ተቋሙን መርተዋል።
ቢቢሲ በተመለከተው የዐቃቤ ሕግ የክስ መዝገብ ላይ አንደኛ ተከሳሽ ሆነው የቀረቡት አቶ ዮሐንስ ሲሆኑ፣ የተቋሙ የፋይናንስ ዳይሬክተር የነበሩት ምትኬ ሮቢ ደግሞ በሁለተኛ ተከሳሽነት ተጠቅሰዋል።
ከብልጽግና ፓርቲ ጋር የተዋሃደው የቀድሞው "ቦሮ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ" አመራር የነበሩት አቶ ዮሐንስ፤ "ለሚመሩት የፖለቲካ ፓርቲ ሥራ ያላግባብ ክፍያ" እንዲፈጸም ማድረጋቸውን የክስ መዝገቡ አስፍሯል።
ለፓርቲው ሥራ ወደ ሌላ ስፍራ በሚጓዙበት ወቅት "ለውሎ አበል እና አውሮፕላን ትራንስፖርት" ወጪዎች በሚል ከመሥሪያ ቤቱ ገንዘብ ተከፍሏቸዋል ሲል ዐቃቤ ሕግ ከስሷል። መዝገቡ በእነዚህ ድርጊቶች በድምሩ ከ124 ሺህ ብር በላይ እንደተከፈላቸው ይገልጻል።
በተጨማሪም የተቋሙ ሠራተኛ የሆኑ ሠራተኞች ጥናት እና ምርምር ሲያቀርቡ የሚከፈላቸው ሁለት ሺህ ብር ቢሆንም፤ አቶ ዮሐንስ ለራሳቸው 218,800 ብር ክፍያ እንዲፈጸምላቸው እንዳደረጉ ዐቃቤ ሕግ በመዝገቡ ጠቅሷል።
ይህ ክፍያ ተፈጸመው "የተጠና ጥናት እና የምርመር ውጤት በሌለበት በተዘጋጀ የመነሻ ሀሳብ" ብቻ እንደሆነም ተጠቅሷል።
በግለሰብ 3,000 ብር ሊከፈላቸው ይገባ ለነበረ የውጭ አጥኚዎች ደግሞ 230,000 ብር እንዲከፈላቸው አቶ ዮሐንስ "የወጪ ትዕዛዝ መፈረማቸውን ወይም ማዘዛቸውን" መዝገቡ ያስረዳል።
በጥናት እና ምርምር ክፍያዎቹ "በድምር የ448,800 ብር ጉዳት መንግሥት ላይ" ማድረሳቸው ተገልጿል።
ሁለተኛው ተከሳሽ አቶ ምትኬ፤ የተወነጀሉበት አንደኛው ጉዳይ በአቶ ዮሐንስ ላይ የተዘረዘሩት ክፍያዎች እንዲከፈል ማድረግ ነው።
በተጨማሪም ሁለተኛው ተከሳሽ "የተጠና ጥናት እና የምርመር ውጤት በሌለበት በተዘጋጀ የመነሻ ሀሳብ ብቻ" ለራሳቸው 265 ሺህ ብር እንዲከፈላቸው ማድረጋቸውን መዝገቡ ያሳያል።
ለሌሎች አጥኚዎች የተሰጠውን እና ሌሎች ክፍያዎችን ጨምሮን በጥቅሉ በመንግሥት ላይ ከ580 ሺህ ብር በላይ ጉዳይ በማድረስ ተከስሰዋል።
ተከሳሾቹ በእነዚህ ድርጊቶቻቸው፤ በ2007 ዓ.ም. በወጣው የሙስና ወንጀሎች አዋጅን እንደጣሱ ዐቃቤ ሕግ በመዝገቡ ገልጿል። የተከሰሱበት የዚህ አዋጅ አንዱ ድንጋጌ ከ20 እስከ 10 ዓመት በሚደርስ እስራት ያስቀጣል።
የዐቃቤ ሕግ መዝገብ እንደሚያስረዳው ተከሳሾቹ የተላለፉት "የመንግሥት ወይም ሕዝባዊ ድርጅት ሥራን በማያመች አኳኋን መምራት" በሚለው የአዋጁ አንቀጽ ውስጥ የሚገኙ ሁለት ድንጋጌዎችን ነው።
አንደኛው የሕግ ድንጋጌ የመንግሥት ሥልጣን ላይ ያለ ግለሰብ የሚመራውን መሥሪያ ቤት "ጥቅም የሚጎዳ ተግባር በማናቸውም ዘዴ" መፈጸምን የሚመለከት ነው። ይህንን ድንጋጌ መጣስ ከአንድ እስከ 10 ዓመት በሚደርስ እስራት ያስቀጣል።
ሁለተኛው ድንጋጌ ደግሞ ይህን የሕግ ጥሰት የተፈጸመበት ሁኔታ ከባድ የሚያደርጉ ምክንያቶች ሲኖሩ በተደራቢነት የሚጠቀስ ነው።
የወንጀል ድርጊቱን ከባድ ከሚያደርጉት ምክንያቶች መካከል ግለሰቡ "ኃላፊነቱን ወይም ግዴታው እንዲጣስ የተፈለገበት ዓላማ" ወይም "የተገኘው ጥቅም ከፍተኛነት" ይገኙበታል።
የጥፋተኛው "የኃላፊነት ወይም የሥልጣን ደረጃ" እና "በደረሰበው ጉዳት ከፍተኛነትም" የጉዳዩን ክብደት የሚወስኑ ጉዳዮች ናቸው።
እነ አቶ ዮሐንስ የወንጀሉን ክብደት ከሚጨምሩት ከእነዚህ ሁኔታዎች ውስጥ ሁለቱን ወይም ከዚያ በላይ መፈጸማቸው ከተረጋገጠ የሚፈረድባቸው የእስር ቅጣት ከ10 ዓመት እስከ 20 ዓመት የሚደርስ እንዲሆን ይደረጋል።