የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክር ቤት አባሉ አምስት ዓመት ከ10 ወር ጽኑ እስራት ተፈረደባቸው

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ሕገ መንግሥት ማሻሻያ ላይ አቤቱታ ካቀረቡ በኋላ በቁጥጥር ስር የዋሉት የክልሉ ምክር ቤት አባል አቶ ዮሐንስ ተሰማ፤ የአምስት ዓመት ከ10 ወር ጽኑ እስራት እና የ15 ሺህ ብር የገንዘብ ቅጣት ተጣለባቸው።

አቶ ዮሐንስ የቅጣት ውሳኔው የተላለፈባቸው ከአምስት ዓመት በፊት ተቋርጦ በነበረው እና ባለፈው መጋቢት ላይ በድጋሚ በተንቀሳቀሰው "ከሊዝ አዋጅ ስሪት ውጪ የከተማ መሬት አስፋፍቶ በመያዝ" ክስ ነው።

የአሶሳ ከተማ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ብይኑን የሰጠው ዛሬ ነሐሴ 13/2017 ዓ.ም. ረፋድ በዋለው ችሎት እንደሆነ ሁለት ምንጮች ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የተቃዋሚው የቦሮ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ቦዴፓ) አመራር የሆኑት አቶ ዮሐንስ፤ ያለመከሰስ መብታቸው ሳይነሳ በቁጥጥር ስር የዋሉት በየካቲት ወር መጨረሻ ላይ ነበር።

የቦዴፓ አመራሩ የታሰሩት፤ ከሌሎች ሁለት የምክር ቤት አባላት ጋር በመሆን የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክር ቤት ያጸደቃቸው ሁለት አዋጆች "ተፈጻሚ እንዳይሆኑ" አቤቱታ ካቀረቡ ከቀናት በኋላ ነበር።

ለሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ አቤቱታ ከቀረበባቸው አዋጆች አንዱ የክልሉ ምክር ቤት መቀመጫ ቁጥርን ያሳደገውን የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ነው። ሁለተኛው አዋጅ ደግሞ የምርጫ ክልሎችን እንደ አዲስ ያዋቀረ ነው።

አቶ ዮሐንስ በመጋቢት ወር ያለመከሰስ መብታቸው ተነስቶ ፍርድ ቤት ሲቀርቡ "የክልሉን ሕገ መንግሥት ለመናድ በመንቀሳቀስ"፣ "ከውጭ ኃይሎች ጋር ግንኙነት በመፍጠር" ወንጀሎች እንደተጠረጠሩ ተገልጿል። በፍርድ ቤት እየታየ ያለው ይህ ጉዳይ እስካሁን ድረስ ክስ አልተመሠረተበትም።

የምክር ቤት አባሉ ከዚህ በተጨማሪ "ከሊዝ አዋጅ ስሪት ውጪ የከተማ ቦታ አስፋፍቶ እና አጥሮ መያዝን" የሚመለከት ክስ ቀርቦባቸዋል። ይህ ክስ አቶ ዮሐንስ በ2012 ዓ.ም. በታሰሩበት ወቅት በፍርድ ሂደት ላይ የነበረ ሲሆን ከስምንት ወራት እስር በኋላ ግን ክሱ ተቋርጦ ተለቅቀው ነበር።

በድጋሚ የተንቀሳቀሰው የዐቃቤ ሕግ የክስ መዝገብ እንደሚያስረዳው፤ አቶ ዮሐንስ "አስፋፍተው ይዘዋል" የተባለው የከተማ ቦታ የሚገኘው፤ " በግዢ ካገኙት እና በስማቸው ካደረጉት" ቦታ አጠገብ ነው።

ተከሳሹ "ከሚመለከተው አካል ፍቃድ ሳያገኝ"፤ "328 ካሬ ሜትር የመንግሥት ባዶ ቦታ" "አካቶ እና አስፋፍቶ በማጠር በሕገ ወጥ መንገድ ግንባታ [አካሂዷል]" ሲል ዐቃቤ ሕግ በክስ መዝገቡ አስረድቷል።

ይህ የወንጀል ድርጊት ከ7 እስከ 15 ዓመት በሚደርስ ጽኑ እስራት እና እስከ 200 ሺህ ብር በሚደርስ ገንዘብ እንደሚያስቀጣ በ2004 ዓ.ም. በጸደቀው "የከተማ ቦታን በሊዝ ስለመያዝ የወጣ አዋጅ" ላይ ተደንግጓል።

አቶ ዮሐንስ በበኩላቸው ቦታውን "በግዢ ያገኙት" እንደሆነ በመጥቀስ ተከራክረዋል። እንደ "የግዢ ውል"፣ "የመሬት ግብር ማስረጃዎች" ያሉ የሰነድ ማስረጃዎችን እንዲሁም "ሽያጩ ሲፈጸም ምስክር ነበሩ" የተባሉ ሰዎችን ጨምሮ 11 ምስክሮችን አቅርበዋል።

በተከሳሹ የቀረቡትን የሰው እና የሰነድ ማስረጃዎች ውድቅ ያደረገው ፍርድ ቤቱ፤ የጥፋተኝነት ውሳኔውን በማስተለላፍ ሁለቱ ወገኖች የቅጣት አስተያየታቸውን እንዲያቀርቡ ጠይቆ ነበር።

ዐቃቤ ሕግ የቅጣት ማክበጃዎችን በማቅረብ "በ18 ዓመት እስራት እንዲቀጡ" የቅጣት አስተያየቱን ለፍርድ ቤት ማቅረቡን ምንጮች ለቢቢሲ ተናግረው ነበር።

ባለፈው ሳምንት ማክሰኞ ነሐሴ 6 በዋለው ችሎት የቅጣት ማቅለያቸውን ያቀረቡት አቶ ዮሐንስ በበኩላቸው፤ "የክልሉን የፍትሕ እና የሥራ አመራር ተቋም መሥሪያ ቤቶችን" መምራታቸው እንዲሁም "በሰላሌ እና በአሶሳ ዩኒቨርሲቲዎች በሕግ መምህርነት ማገልገላቸው" እንዲያዝላቸው መጠየቃቸውን ሁለት ምንጮች አስረድተዋል።

"የቤተሰብ አስተዳዳሪ መሆናቸው"፣ "የኩላሊት ሕመም ያለባቸው" መሆኑ እና በእስር ቆይታቸው "ነጻ የሕግ አገልግሎት እየሰጡ" መሆናቸውን በመጥቀስም በማቅለያነት እንዲያዝላቸው ጠይቀዋል ተብሏል።

የአሶሳ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የቅጣት ውሳኔውን ለማስተላለፍ ዛሬ ባዋለው ችሎት፤ አቶ ዮሐንስ ያቀረቧቸውን የቤተሰብ አስተዳዳሪነት እና የኩላሊት ሕመም ማቅለያዎች መቀበሉን እንደገለጸ በችሎት የተገኙ ሁለት ምንጮች ገልጸዋል።

ፍርድ ቤቱ፤ አቶ ዮሐንስ ጥፋተኛ በተባሉበት "የከተማ ቦታን አስፋፍቶ መያዝ" እና "መንግሥት ያገኝ የነበረውን ገቢ ማሳጣት" ወንጀል በአምስት ዓመት ከ10 ወር ጽኑ እስር እና 15 ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጡ መወሰኑን አስታውቋል። ይህንን ቅጣት ውሳኔ ያልተቀበሉት አቶ ዮሐንስ ይግባኝ ለማቅረብ በሂደት ላይ መሆናቸውን ምንጮች ገልጸዋል።