በኢትዮጵያ አወዛጋቢ የነበረው ሬማ ለንደን ላይ ባቀረበው የሙዚቃ ዝግጅት መነጋገሪያ ሆነ

ሬማ በለንደኑ የሙዚቃ ድግስ ላይ

የፎቶው ባለመብት, @heisrema

የምስሉ መግለጫ, ሬማ በለንደኑ የሙዚቃ ድግስ ላይ

በኢትዮጵያ አዲስ ዓመት ዋዜማ የሙዚቃ ሥራዎቹን ያቀርባል ከተባለ በኋላ ውዝግብ ፈጥሮ የነበረው ናይጄሪያዊው ዘፋኝ ሬማ በለንደን ያቀረበው የሙዚቃ ድግስ መነጋገሪያ ሆነ።

ሬማ 20 ሺህ ታዳሚዎችን የመያዝ አቅም ባለው የለንደኑ '02 አሬና' ባቀረበው የሙዚቃ ሥራው ወቅት “ሰይጣናዊ እና የኢሉሚናቲ መልክቶችን አንጸባርቋል” የሚሉ ቅሬታዎች ከተሳታፊዎች እና ከአድናቂዎቹ ቀርቦበታል።

በሙሉ ስሙ ዲቫይን ኢኮቦር በመባል የሚታወቀው ድምጻዊ ከዚህ ቀደምም በአለባበሱ እንዲሁም በሙዚቃ ቪዲዮ ሥራዎቹ ላይ የሚታዩ ትዕይንቶች ክርስቲያናዊ አይደሉም የሚሉ ቅሬታዎች ሲቀርቡበት ቆይቷል።

በኢትዮጵያም ሊያቀርበው የነበረው የሙዚቃ ድግሱ እንዲሰረዝ ምክንያት የሚጠቀምባቸው አልባሳት እና ማጌጫዎች ክርስትናን የሚቃረኑ ናቸው በሚል መሆኑ አይዘነጋም።

ሬማ ከቀናት በፊት ለንደን ውስጥ ባቀረበው የሙዚቃ ዝግጅቱ መጀመሪያ ላይ በፈረስ አምሳል በተሠራ ሐሰተኛ ፈረስ ላይ ተቀምጦ በሚብለጨለጭ ብርሃን ውስጥ ሆኖ ይታያል።

የሚያበሩ ዐይኖች እና ጋማ ያለው ሲሆን እንዲሁም የፊት እግሮቹን ወደ ላይ የሰቀለ በሚመስለው ፈረስ ላይ የተቀመጠው ሬማ፤ ጭንቅላቱን ጨምር የሚሸፍን ጥቁር ገዋን የለበሰ ሲሆን ፊቱ ላይ ደግሞ ደማቅ ቀለማት ያሉት ጭምብል አጥልቆ ታይቷል።

ሬማ በሳምንቱ መጀመሪያ ማክሰኞ ኅዳር 4 ያቀረበው ኮንሰርት የመግቢያ ቲኬቱ ቀድሞ ተሽጦ ያለቀ ሲሆን፣ በእውቁ የለንደን የሙዚቃ ሥራዎች የሚቀርቡበት 02 አሬና ሙሉ ታዳሚ በማግኘት ከጥቂት አፍሪካውያን አርቲስቶች መካከል አንዱ ሆኗል።

ሬማ በዕለቱ ሁለተኛውን ዙር የሙዚቃ ሥራውን ማቅረብ የጀመረው ደግሞ በሌሊት ወፍ አምሳያ የተሰራ ግዙፍ ሐሰተኛ የለሊት ወፍ ላይ ቆሞ ነው።

ከዐይኖቹ ደማቅ ቀይ ብርሃን የሚያወጣው እና ክፍንፎቹን በዝግታ የሚያማታው ግዙፍ የሌሊት ወፍ ላይ የቆመው ሬማ ከመሃል ጭንቅላቱ የሚነሳ ባለ ብረት ትልቅ መነጻር አድርጎ ታይቷል።

ወጣቱ ዘፋኝ ከሙዚቃ ሥራዎቹ በኋላ በመድረክ ላይ ለብሶ እና ይዞ የታየባቸው እንስሳት እና ቁሶች ሰይጣናዊ መልዕክቶችን የሚያንጸባርቁ ናቸው የሚሉ ትችቶች በስፋት ቀርበውበታል።

ይህንንም ተከትሎ ሬማ በሰጠው ምላሽ መድረክ ላይ የታየባቸው ቁሶች ከመጣበት ማኅበረሰብ አመለካከት እና ታሪክ ጋር የተያያዙ መሆናቸውን ገልጿል።

በናይጄሪያዋ ኤዶ ግዛት የተወለደው ሬማ የጋለበው ሐሰተኛው ፈረስ የቤኒን ወይም የኤዶ ኤምፓየር አምሳያ መሆኑን የገለጸ ሲሆን፣ አጥልቆት የነበረው የፊት ጭምብልም በ16ኛው ከፍለ ዘመን የኤዶ ሕዝቦች ገዢ የነበረችው የንግሥት ኢዲአ ጭምብል አምሳያ መሆኑን ገልጿል።

ሬማ በኤክስ ገጹ (ትዊተር) ላይ ጨምሮ እንደገለጸው በሁለተኛው ዙር የሙዚቃ ሥራው ላይ የጋለበው የሌሊት ወፍ በኤዶ የምሽት ሰማይ ላይ ለሚበሩት የሌሊት ወፎ ክብር ለመስጥ ያደረኩት ነው ብሏል።

ሬማ በመድረክ ላይ ያንጸባረቃቸው ድርጊቶች ሰይጣናዊ ናቸው ብለው የተቹት እንዳሉት ሁሉ ሙዚቀኛው የኤዶን ታሪክ በማስታወሱ ድጋፋቸውን የሰጡት አልጠፉም።

በተለይ የናይጄሪዋ ኤዶ ግዛት አስተዳዳሪ የሆኑት ጉድዊን ኦባሴኪ አቀንቃኙ ሬማ “የኤዶን ቅርስ እና ታሪክ በማንጸባረቁ ኮርተንበታል” ብለዋል።

ሬማ በሚለው የመድረክ ስሙ የሚታወቀው ዲቫይን ኢኮቦር እአአ በአውሮፓውያኑ 2000 ነው ናይጄሪያ ውስጥ የተወለደው።

ሬማ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በመላው ዓለም ተወዳጅነት ያገኘው ዘፈኑ ‘ካልም ዳውን’ ዩቲዩብ ላይ ከፍተኛ የተመልካች ቁጥር ያገኘ የናይጄሪያ ሙዚቃ ተብሎ ተመዝግቧል።

ይህን ዘፈን ከ548 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ዩቲዩብ ላይ ተመልክተውታል። በጣም ተወዳጅ የሆነው ዘፈኑ ‘ካልም ዳውን’ የናይጄሪያ ፖፕ እና አር ኤንድ ቢ ውህድ ነው።

ከአሜሪካዊቷ ድምጻዊት ሰሌና ጎሜዝ ጋር ተጣምረው ዘፈኑን ካቀነቀኑ በኋላ ሙዚቃው የበለጠ አድማጭ አግኝቷል።

በቢልቦርድ የምርጥ 100 ዘፈኖች ዝርዝር ሦስተኛ ከመሆኑም በተጨማሪ በአሜሪካ የአፍሮቢትስ ዘፈኖች ሪከርድን ለ52 ሳምንታት በአንደኛነት መርቷል።

ሬማ የተወለደው በናይጄሪያዋ ኤዶ ግዛት ሲሆን የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ ሳለ ይዘፍን፣ ራፕም ያደርግ ነበር።

ሙዚቃ የጀመረው ቤተ ክርስቲያን ነው።

ሬማ በስሙ የተጠራውን ‘ሬማ’ የተሰኘውን የመጀመሪያ አልበም የለቀቀው እአአ 2019 ላይ ነበር።