አየር መንገዱ 'አውሮፕላኑ በከባድ አውሎ ንፋስ መሀል አርፏል' መባሉ ስህተት ነው አለ

የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን

የፎቶው ባለመብት, ETHIOPIAN

የኢትዮጵያ አየር መንገድ የበረራ ቁጥር ኢቲ608 በሆንግ ኮንግ አየር ማረፊያ 'በከባድ አውሎ ንፋስ ውስጥ አርፏል' የተባለው ስህተት ነው አለ።

አየር መንገዱ ይህን ያለው የአገር ውስጥ እና የውጭ መገናኛ ብዙሃን የአየር መንገዱ የመንገደኞች አውሮፕላን ከባንግኮክ ተነስቶ በሆንግ ኮንግ በከባድ አውሎ ንፋስ ውስጥ ያረፈው ብቸኛ አውሮፕላን በሚል ዘገባ ካወጡ በኋላ ነው።

አንድ የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን አየር መንገዱ "በከባድ አውሎ ንፋስ መካከል ማረፍ የቻለ በመሆኑ ዓለም ቀፍ መነጋገሪያ ሆኗል" ሲል ዘግቦ ነበር።

ብሉምበርግ የተሰኘው ጋዜጣ ደግሞ የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን ዝናብ በቀላቀለ አውሎ ንፋስ ውስጥ ዓርብ ምሽት በሆንግ ኮንግ አየር ማረፊያ ያረፈ ብቸኛው አውሮፕላን ነው ብሏል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ትናንት ነሐሴ 27/2015 ዓ.ም. ምሽት ባወጣው መግለጫ ከአዲስ አበባ ተነስቶ በባንግኮክ አድርጎ ሆንግ ኮንግ የሚበረው ኢቲ608 የመንገደኞች አውሮፕላን በአገሪቱ ሰዓት አቆጣጠር ከትናንት በስቲያ ዓርብ በታቀደለት ሰዓት ሆንግ ኮንግ አርፏል ብሏል።

አውሮፕላኑ በረራውን ከባንኮክ የጀመረው ሆንግ ኮንግ ሲደርስ የሚኖረው የአየር ጸባይ ለማረፍ የሚያስችል መሆኑን ከአየር ትንበያ ከተቀበለ በኋላ መሆኑን አስረድቷል።

ይህን ተከትሎም በመዳረሻው የአየር ጸባዩ ለማረፍ የሚፈቅድ መሆኑን ከተረጋገጠ እና ከሆንግ ኮንግ የአየር በረራ መቆጣጠሪያ ክፍል ፍቃድ ከተሰጠው በኋላ የመንደኞች አውሮፕላኑ ማረፉን አስታውቋል።

አየር መንገዱ በመግለጫው በሆንግ ኮንግ ስለነበረው አውሎ ንፋስ የቀላቀለ ከባድ ዝናብ ቀድሞ ያውቅ እንደነበረ ገልጾ የአየር ሁኔታ ጸባዩን በተመለከተ ተከታታይ የሆነ መረጃ ለበረራ ቡድኑ ሲያደርስ መቆየቱን ጨምሮ አስታውቋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

አየር መንገዱ አውሮፕላኑ በሆንግ ኮንግ ያለችግር ማረፉን እና ከበረራው በኋላ በሆንግ ኮንጎ ያለው የአየር ጸባይ ሁኔታ ለበረራ ምቹ ሳይሆን በመቅረቱ ከሆንግ ኮንግ የሚደረገው ቀጣይ በረራ በ24 ሰዓታት እንዲዘገይ መደረጉን ገልጿል።

ሳኦላ የተባለው በሰዓት እስከ 118 ኪሎ ሜትር የሚጓዝ አውሎንፋስ የቀላቀለው ዝናብ ሆንግ ኮንግ እና አካባቢዋን መትቶ ነበር።

በዚህ አውሎንፋስ የቀላቀለው ዝናብ ምክንያት በርካታ በረራዎች ተሰርዘዋል።

እንደ ብሉምበርግ ዘገባ ከሆነ አርብ ዕለት በጠቅላላው 460 በረራዎች የተሰረዙ ሲሆን በቀጠናው ከፍተኛውን በረራ በማድረግ የአንበሳውን ድርሻ የሚይዘው ካቲ ፓስፊክ ኤየርወይስ ወደ ሆንግ ኮንግ እና ከሆንግ ኮንግ የሚደረጉ በረራዎችን በሙሉ ከአርብ ከሰዓት 8 ጀምሮ እስከ ቅዳሜ ጠዋት 4 ሰዓት ድረስ ሰርዞ ነበር።

የበረራ መከታተየ ድረ-ገጽ ከሆነ ፍላይትራዳር24 ላይ በተገኘው መረጃ መሠረት ይህ ቦይንግ 787-9 ድሪምላየርነር የሆነው ግዙፍ ዘመናዊ አውሮፕላን የበረራ አቅጣጫው አዲስ አበባ - ባንግኮክ - ሆንግ ኮክ ነው።

አውሮፕላኑ ከአዲስ አበባ ተነስቶ ባንግኮክ ካረፈ በኋላ በአገሪቱ ሰዓት አቆጣጠር ዓርብ ነሐሴ 25/2015 ዓ.ም. ከባንግኮክ ወደ ሆንግ ኮክ 2 ሰዓት ከ20 ደቂቃ የፈጀው በረራው ነው መነጋገሪያ የሆነው።

ይህ አውሮፕላን ወደ ሆንግ ኮንግ እየበረረ ሳለ ፍላይትራዳር24 ላይ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በረራው በቀጥታ ሲከታተሉ ነበር። እንደ ብሉምበርግ ከሆነ በአገሪቱ ሰዓት አቆጣጠር ከሰዓት 11 ሰዓት ከ 06 ዲቀቃ ላይ ያረፈውን አውሮፕላን 6400 ሰዎች ሲከታተሉት ነበር።

አውሮፕላኑ ሴፕተምበር 3 ከባንኮክ ወደ አዲስ አበባ በረራ አድርጎ ቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ መድረሱንም ፍላይትራዳር24 ላይ መመልከት ይቻላል።