ከ‘ዲሽታ ጊና’ ጋር የተጣመረው ኤከን በአፍሪካዊ ሙዚቃዎች ላይ እንደሚያተኩር ገለጸ

ኤከን

የፎቶው ባለመብት, KONVICT KULTURE

የአርኤንድቢው ኮከብ ኤከን በሙዚቃው ከ20 ዓመታት በላይ ቆይቷል።

ባለፈው ዓመት ከኢትዮጵያዊው ድምጻዊ ታሪኩ ካንጋሲ ጋር ተጣምሮ ‘ዲሺታ ጊና’ ወይም ‘አዳም ወንድሜ’ የተሰኘውን ነጠላ ዜማ ሪሚክስ አድርጓል።

ታሪኩ በወቅቱ ከቢቢሲ ጋር ባደረገው ቆይታ “ኤከን መጥቶ ሕዝቤን እና ባህሌን ቢያይልኝ ደስ ይለኛል” ብሎ ነበር።

ከሰሞኑ ከቢቢሲ ጋር ቆይታ ያደረገው ሴኔጋላዊ አሜሪካዊው ድምጻዊ ከዓመታት በኋላ ‘የኔ’ የሚለውን ሙዚቃ መሥራት መጀመሩን ይናገራል።

የተወለደው አሜሪካ ነው። ከልጅነት ጊዜው ግማሹን ያሳለፈው በኒው ጀርሲ ግዛት ውስጥ ግማሹን ደግሞ በሴኔጋል ነው።

የምዕራብ አፍሪካን ጨምሮ ሌሎችም የአፍሪካ ሙዚቃ መሣሪያዎችን መጫወት ተምሯል።

እአአ በ2000 ገደማ ወደ ሙዚቀኛነት ሙያ ሲገባ የፕሮዲውሰሮች ፍላጎት የነበረው የኤከንን አንድ የማንነት ገጽታ ማሳየት ብቻ እንደነበር ያስታውሳል።

“ሙዚቃ ስጀምር ራሴን ከአፍሪካዊነቴ አርቄ ነበር” ብሏል ከቢቢሲ ኒውስቢት ጋር ባደረገው ቆይታ።

“እኔን እንደ አፍሪካዊ ሙዚቀኛ አቅርቦ ማስተዋወቅም ይሁን ገቢ ማግኘት ለፕሮዲውሰሮቹ ቀላል አልነበረም። ስለዚህ በዚያው መንገድ ቀጠለ።”

በእርግጥ ሙዚቀኛው ከንግድ አንጻር ስኬታማ ሆኗል። ‘ሎንሊ’ እና ‘ሎክድ አፕ’ የተሰኙት ዘፈኖቹ ከፍተኛ አድናቆት አግኝተዋል።

የሙዚቃ ንግድ የሚጠይቀው ማንነት ሙዚቃዎቹ ላይ ተጽዕኖ ማሳደሩን ይናገራል።

“የእያንዳንዱን ነገር ውጤት ማስላት በጣም አታካች እና ራሱን የቻለ ሥራ ነው” ይላል ድምጻዊው።

ሙዚቀኛው በሂደት የራሱን ሪከርድ ሌብል መሥርቷል። ‘ኮንቪክት’ የተባለ ልብስ በማምረትም የንግዱን ዘርፍ ተቀላቅሏል።

ሴኔጋል ውስጥ ‘የዋካንዳን አምሳያ’ ለመገንባት እንዲሁም የራሱን ክሪፕቶከረንሲ ለመጀመር ያደረገው ጥረት ፍሬ አላፈራም።

አሁን ግን የማንንም ድጋፍ ሳይሻ የሚፈልገውን ነገር በነጻነት መሥራት የሚችለበት ደረጃ ላይ መድረሱን ይናገራል።

50 ዓመት የሞላው ድምጻዊው አሁን የሚሠራው ሙዚቃ የሚወደው ዓይነት እንደሆነ ይናገራል።

“ብዙ የአፍሪካ ድምጾችን ማካተት ችያለሁ” ይላል።

አሁን ላይ ገንዘብ ማግኘት አለብኝ ከሚል ጫና ተላቋል።

“ሙዚቃ አሁን ዋነኛ ገቢ ማግኛዬ አይደለም። ምናልባት ገቢ ከማገኝባቸው ነገሮች አሥረኛው ሊሆን ይችላል።”

ያገኘው የገንዘብ ነጻነት በሙዚቃው ባህሉን የማሳየትም ነጻነት እንደሰጠው ይናገራል።

አዲስ የሚያወጣው ‘አፍሮ ፍሪክስ’ አልበም ቀድሞ ከሚሠራቸው ሙዚቃዎች የተለየ መሆኑንም ያክላል።

“ሙዚቃውን ስሠራ ስለ ሙዚቃ ንግድ እና ስለ ፖለቲካ ሳልጨነቅ በነጻነት ነው” ይላል።

በአልበሙ ከተካተቱ ሙዚቃዎች አብዛኞቹ መነሻቸው አፍሮቢት ነው።

እንደ ዴቪዶ፣ ዊዝኪድ እና በርና ቦይ ያሉ ድምጻውያን አፍሮቢትን ዝነኛ አድርገውታል።

የምዕራብ አፍሪካን እና የተቀረውን አፍሪካ ሙዚቃ ያካተተ ሙዚቃን በተሻለ ሁኔታ ለመሥራት የሚያደርገውን ጥረት ኤከን ይናገራል።

ኤከን

የፎቶው ባለመብት, KONVICT KULTURE

በአውሮፓውያኑ 2008 ዊዝኪድ የኤከን ሪከርድ ሌብልን ተቀላቅሏል።

አፍሮቢትስ አሜሪካ ውስጥ የማይደመጥበት ወቅት እንደነበር ያስታውሳል።

“በ2000 አፍሮቢትስ አሜሪካ ውስጥ እንዲሸጥ ያደረኩትን ጥረት አስታውሳለሁ። ሬጌ ሙዚቃ ነበር የመሰላቸው። አፍሪካ ብዙ ሕዝብ እንዳላት እና አፍሮቢትስ ለወደፊትም የሚኖር ሙዚቃ እንደሆነ ሰዎች እንዲገነዘቡ ለማድረግ መሞከር አታካች ነበር። ተቀባይነት አላገኘሁም።”

ይህ በሆነ በ10 ዓመት ውስጥ አፍሮቢትስ ዝናው ናኘ። ድሬክ እና ቢዮንሴን ጨምሮ ሌሎችም ታዋቂ ድምጻውያን ከአፍሮቢትስ አርቲስቶች ጋር ተጣምረው ሠርተዋል።

በ2021 ዊዝኪድ ግራሚ ሲያሸንፍ ኤከን “ድሮውንም ብያችሁ ነበር” ብሏል።

አፍሮቢትስ ከፍተኛ ዕውቅና ያገኘው በወጣቱ ትውልድ አማካይነት እንደሆነ ኤከን ይናገራል።

ኤከን

የፎቶው ባለመብት, KONVICT KULTURE

ከተለያዩ የሙዚቃ ስልቶች ጋር እየተዋሀደ እንዲሠራ በማድረግ ረገድ የማኅበራዊ ሚዲያን ሚና ሳይጠቅስ አያልፍም።

እንደ ዴቪዶ ያሉ ድምጻውያን አፍሮቢትስ በምዕራቡ ዓለም ያለው ተቀባይነት እንዲጨምር ምክንያት ናቸው።

ድምጻውያን በማኅበራዊ ሚዲያ መድረክ አፍሮቢትስ እንዲተዋወቅም አግዘዋል።

“ዓለም ማንነታችንን እንዲያውቅ ሁሉም ድርሻውን እየተወጣ ነው። አንዴ ሙዚቃውን ከሰሙት በኋላ ሱስ ነው የሆነባቸው።”

ለወደፊት ተስፋውም ብሩህ ነው።

“አፍሮቢትስ ለዓመታት የኖረ ስልት ነው። ለዓመታትም ይኖራል” ይላል።

የእሱ ሚና ያለውን ተደማጭነት ተጠቅሞ ዘርፉ የበለጠ እንዲተዋወቅ ማድረግ ነው።

የሙዚቃ ስልቱ ስለ አፍሪካ ሰዎች የበለጠ እንዲያውቁ እንደሚያነሳሳም ተስፋ ያደርጋል።

“አፍሮቢትስ በዓለም ታውቋል። ስለ አፍሪካ ዓለም እንዲያውቅም ይረዳል።”