በእስራኤል ኤርትራውያን ጥገኝነት ጠያቂዎች ከአገሪቱ ፖሊስ ጋር ተጋጭተው ጉዳት ደረሰ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ትናንት ነሐሴ 27/2015 ዓ.ም. በእስራኤል መዲና ቴል አቪቭ ከኤርትራ ባሕል ፌስቲቫል ዝግጅት ጋር በተያያዘ የኤርትራ መንግሥት ደጋፊዎች እና ተቃዋሚዎች በፈጠሩት ሁከት በሰው እና በንብረት ላይ ጉዳት ደረሰ።
በእስራኤል መዲና ቴል አቪቭ የተከሰተውን ሁከት ለመቆጣጠር የእስራኤል ፖሊስ ጥይት፣ አስለቃሽ ጭስ እና የፕላስቲክ ጥይቶችን በመቶዎች በሚቆጠሩ ኤርትራውያን ላይ ለመተኮስ ተገዷል።
ኤርትራውያኑ የፈጠሩት ሁከት የአገሪቱን ባለስልጣናት ያስቆጣ ሲሆን በግጭቱ የተሳተፉ ጥገኝነት ጠያቂዎች ወደ ትውልድ አገራቸው በአስቸኳይ ለመመለስ ዕቅድ እንደሚወጣ ጠቅላይ ሚንስትር ቤኒያሚን ኔታኒያሁ አስታወቀዋል።
ትናንት ነሐሴ 27/2015 ዓ.ም. በእስራኤል አገር የኤርትራ ባሕር ፌስቲቫል ዝግጅት ጋር በተያያዘ የኤርትራ መንግሥት ደጋፊዎች እና ተቃዋሚዎች በፈጠሩት ሁከት ከአገሪቱ ፖሊስ ጋር ተጋጭተው ጉዳት ደርሷል።
ሁከቱ የተፈጠረው በኤርትራ መንግሥት ደጋፊዎች የተዘጋጀ ነው የተባለውን ዝግጅት ለማወክ በመቶዎች የሚቆጠሩ የኤርትራ መንግሥት ተቃዋሚዎች ፌስቲቫሉ ወደሚዘጋጅበት ቦታ በኃይል ከገቡ በኋላ ነው።
የጠቅላይ ሚንስትር ኔታኒያሁ ጽ/ቤት ትናንት ነሐሴ 27/2015 ዓ.ም. ምሽት እንዳለው በሁከቱ የተሳተፉ ኤርትራውያንን ወደ ትውልድ አገራቸው ለመመለስ ሚንስትሮችን በአባልነት የሚያቅፍ ግብረ ኃይል ይቋቋማል።
የኤርትራ መንግሥት ተቃዋሚ ናቸው የተባሉ ከመንግሥት ደጋፊዎች ጋር ተጋጭተው የእስራኤል ፖሊስ አባላትን ጨምሮ በመቶዎች የሚቆጠሩ ጉዳት የደረሰባቸው ሲሆን በንብረት ላይም ውድመት ደርሷል።
የኤርትራ የባሕል ፌስቲቫል ዝግጅትን ምክንያት በማድረግ በኤርትራውያን መካከል በአውሮፓ እና አሜሪካ ከተሞች ግጭት ሲፈጠረ ይህ የመጀመሪያው አይደለም።
በዚህ ዓመት ብቻ በጀርመን ጊሰን ከተማ፣ በስዊድን፣ በኖርዌይ እና በካናዳ ቶሮንቶ ብዙዎችን ለጉዳት የዳረገ ግጭት ተከስቷል።
ትናንት ነሐሴ 27/2015 ዓ.ም. በቴል አቪቭ የተከሰተውን ሁከት በተመለከተ የእስራኤል መገናኛ ብዙኃን እንደዘገቡት የፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ አስተዳደር ደጋፊዎች ወዳዘጋጁት የባሕል ፌስቲቫል ስፍራ ተቃዋሚዎች በኃይል ገብተዋል።
ፖሊስ ተቃዋሚዎቹ ወደ ዝግጅት ስፍራው እንዳይገቡ ክልከላ ማድረግ የቻለ ቢሆንም ኋላ ላይ የፖሊስ አጥርን ሰብረው ወደ ዝግጀት ቦታው ገብተዋል።
ይህን ተከትሎ በከተማዋ ሁከት ተቀስቅሷል። ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የተሰራጭ ተንቀሳቃሽ ምስሎች እንደሚያሳዩት በቀለም የተለያየ ካናቴራ የለበሱ ኤርትራውያን በሁለት ጎራ ተከፍለው በዱላ ሲደባደቡ እና በደንጋይ ሲፈነካከቱ ታይተዋል።
ፖሊስ ጥይት እየተኮሰ ከላይ ደግሞ በሄሊኮፍተር ቅኝት ሲያደርግ የነበረ ሲሆን የቴል አቪቭ ከተማ ነዋሪዎች ክስተቱ መኖሪያ አካባቢያችንን 'የጦር ቀጠና' አስመስሎት ነበር ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
በሁከቱ ምክንያት በሰው እና በንብረት ላይ ጉዳት ደርሷል።
የፖሊስ መኪናን ጭምሮ በርካታ ተሸከርካሪዎች የወደሙ ሲሆን ሁከቱ የተፈጠረበት ስፍራ የነበሩ የንግድ ተቋማት የመስታውት መስኮቶች ተሰባብረዋል።
የእስራኤል ፖሊስ ባወጣው መግለጫ የፖሊስ አባላቱ ጥይት ለመተኮስ የተገደዱት ክስተቱ ለሕይወታቸው አስጊ መስሎ ስለተሰማቸው መሆኑን እና በግጭቱ 27 አባላት ጉዳት እንደደረሰባቸው አስታውቋል።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ከሁከቱ በኋላ 30 የፖሊስ አባላትን ጨምሮ 114 ሰዎች ጉዳት ደርሶባቸው የሕክምና አገልግሎት እንደተሰጣቸው ከአገሪቱ ጤና ተቋም የወጣ መረጃ አመላክቷል።
ከእነዚህ መካከል 8 በጸና የተጎዱ ሲሆኑ 13 ደግሞ ለሕይወት አስጊ ባይሆንም ቀላል የማይባል ጉዳት ደርሶባቸዋል።
ከቀናት በፊት የእስራኤል ፖሊስ የተለያየ የፖለቲካ አቋም ያላቸው ኤርትራውያን በተለያየ የከተማዋ ስፍራዎች አቋማቸውን ለመግለጽ አደባባይ ለመውጣት ተስማምተዋል ብሎ ነበር።
በአሥመራ ያለው መንግሥት ደጋፊዎች በእስራኤል የኤርትራ ኤምባሲ አካባቢ ለመሰባሰብ አቅደው የነበረ ሲሆን ተቃዋሚዎች ደግሞ በቴል አቪቭ የቀድሞ አውቶብስ ማቆሚያ ስፍራ ለመስባሰብ ነበር ቀድሞ ከስምምነት ተደርሶ የነበረው።
ይሁን እንጂ ሁለቱም አካላት ቀድሞ የገቡትን ቃላቸውን አልጠበቁም ብሏል፥ የእስራኤል ፖሊስ ከሁከቱ በኋላ ባወጣው መግለጫው።
አንድ በስም ያልተጠቀሱ ከፍተኛ የፖሊስ መኮንን ሃሬት ለተባለ ጋዜጣ ሲናገሩ፤ “በሁከቱ ከፍተኛነት በጣም ነው የተደነቅነው። ያልጠበቅነው ነበር። በዌስት ባንክ ብቻ የምናየው ዓይነት ሁከት ነው” ብለዋል።
ከግጭቱ በኋላ በመቶዎች የሚቆጠሩ የፖሊስ አባላት ወደ ስፍራው ተሰማርተዋል።
በአሁኑ ወቅት ወደ 18ሺህ የሚገመቱ ጥገኝነት ጠያቂ የሆኑ ኤርትራውያን በእስራኤል ይኖራሉ። አብዛኛዎቹ የግብጽን ሲናይ ባሕር ገብ መሬት አቋርጠው እስራኤል የገቡ ናቸው።
ጥገኝነት ጠያቂዎቹ ኤርትራውያን በአገሪቱ ያለውን የፖለቲካ እና የእምነት ጭቆና እንዲሁም የጊዜ ገደብ የሌለውን አስገዳጅ የብሔራዊ አገልግሎት በመሸሽ ከአገር እንደተሰደዱ ይገልጻሉ።
የኤርትራ መንግሥት ደጋፊዎች የሆኑ ጥገኝነት ጠያቂዎች እንደ ስደተኛ ዓለም አቀፍ ጥበቃ አያስፈልጋቸውም ይሁን እንጂ የአገሪቱ መንግሥት ጥገኝነት ጠያቂዎቹን የፖለቲካ አቋም መለየት አዳጋች እንደሆነበት የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።












