ዶናልድ ትራምፕ በአገራት ላይ የጣሉት አዲሱ ታሪፍ እና የዓለም መሪዎች ምላሽ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images/BBC
ዶናልድ ትራምፕ ወደ አሜሪካ በሚገቡ ሸቀጦች ላይ አዲስ ታሪፍ ለመጣል መወሰናቸው "ለዓለም ኢኮኖሚ ትልቅ ጉዳት ነው" ሲሉ የአውሮፓ ኅብረት ኮሚሽን ኃላፊ ኡርሱላ ፎን ደር ሌየን ተናገሩ።
ቻይና የዶናልድ ትራምፐን እርምጃ በመቃወም "ተገቢውን ምላሽ ለመስጠት ቆራጥ" መሆኗን ገልጻለች።
ይህ የቻይና የማስጠንቀቅያ ምላሽ የተሰማው የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ከመጋቢት 27 2017 ዓ.ም. ጀምሮ ወደ አሜሪካ በሚገቡ ሁሉም ምርቶች ላይ የ10 በመቶ ታሪፍ መጣላቸውን ይፋ ካደረጉ በኋላ ነው።
ከመጋቢት 29/2017 ዓ.ም. ጀምሮ ደግሞ ወደ 60 የሚጠጉ አገራት ከፍተኛ የሆነ ታሪፍ ተጥሎባቸዋል።
ዶናልድ ትራምፕ እርምጃዎቹ ፍትሃዊ ባልሆኑ የንግድ ፖሊሲዎች ላይ የተሰጠ ምላሽ መሆኑን ተናግረዋል።
አክለውም በውሳኔዎቹ "በጣም ቸር" ለመሆን መሞከራቸውን አብራርተዋል።
ረቡዕ ዕለት ትራምፕ ታሪፉ የአሜሪካን ማምረቻዎች ለማሳደግ እንደሚውል ገልጸው እርምጃው "አሜሪካን እንደገና ሀብታም ያደርጋታል" ብለዋል ።
ሐሙስ ማለዳ ላይ መግለጫ የሰጡት ቮን ደር ሌየን አዲሱ አገራት ላይ የተጣለው ግብር "በዓለም ዙሪያ በሚሊዮኖች ለሚቆጠሩ ሰዎች፣ አስፈሪ መዘዝ" ይዞ እንደሚመጣ ገልጸዋል።
የአውሮፓ ኮሚሽን ኃላፊ አውሮፓ የተቀናጀ አካሄድ እንደምትከተል ቃል ገብተው፣ ኅብረቱ እያደረገ ያለው ድርድር ካልተሳካ የአጸፋ እርምጃዎችን ለመውሰድ እየተዘጋጁ መሆኑን አስጠንቅቀዋል።
"ከመካከላችን አንዳችን ላይ እርምጃ ከተወሰደ ሁላችንም ላይ እንደተወሰደ እንቆጥረዋለን" ብለዋል።
የትራምፕ አጋር የሆኑት ኢጣሊያዊቷ ፖለቲከኛ ጆርጂያ ሜሎኒ ውሳኔው "ስህተት ነው" ካሉ በኋላ፣ ከአሜሪካ ጋር "የንግድ ጦርነትን ላለመጀመር" እንደሚሰሩ አስታውቀዋል።
የስፔኑ ፔድሮ ሳንቼዝ በበኩላቸው አገራቸው "ለሁሉም ክፍት የሆነ ዓለም ለመፍጠር ቁርጠኝነቷን ትቀጥላለች" ሲሉ የአየርላንዱ ፖለቲከኛ ታኦይዝሽ ሚሼል ማርቲን ደግሞ የትራምፕን ውሳኔ "ማንም የማያተርፍበት" ሲሉ ጠርተውታል።
የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ሐሙስ ዕለት በአዲሱ ታክስ ከተጎዱ የንግድ ዘርፍ ተወካዮች ጋር በቤተመንግሥታቸው እንደሚገናኙ ጽህፈት ቤታቸው አስታውቋል።
ከአውሮፓ ኅብረት ውጭ በአሜሪካ ፕሬዝዳንት "የለየላቸው አጥፊዎች" ተብለው ከተፈረጁት አገራት መካከል አንዷ የሆነችው ቻይና አሁን ባለው 20 በመቶ ቀረጥ ላይ 34 በመቶ ተጨማሪ ታሪፍ ተጥሎባታል።
ይህም አጠቃላይ የታክስ ግዴታዎቿ ቢያንስ 54 በመቶ ያደርሰዋል።
የአገሪቱ የንግድ ሚኒስቴር አሜሪካ ታሪፉን "በፍጥነት እንድትሰርዝ" የጠየቀ ሲሆን ቻይና "የራሷን መብት እና ጥቅም ለማስጠበቅ በቁርጠኝነት የአጸፋ እርምጃዎችን ትወስዳለች" ብሏል።
ወደ አሜሪካ የምትልከው ምርት ላይ የ32 በመቶ ታሪፍ የተጣለባት ታይዋን በበኩሏ፣ እርምጃውን "በጣም ምክንያታዊነት የጎደለው" በማለት ጠርታዋለች።
የደቡብ ኮሪያ ተጠባባቂ ፕሬዝዳንት ሃን ዳክ-ሶ እንዲሁ የዓለም ንግድ ጦርነት "እውን ሆኗል" ካሉ በኋላ መንግሥታቸው "የንግድ ቀውሱን ለማሸነፍ" የተለያዩ አማራጮችን እንደሚመለከት ተናግረዋል።
ጃፓን የተጣለባት የ24 በመቶ ታሪፍን "እጅግ በጣም ያሳዝናል" ካለች በኋላ የዓለም ንግድ ድርጅት እና የአሜሪካ-ጃፓን ስምምነቶችን የሚጥስ ብላዋለች።
ከዚህ ዜና በፊት ከአሜሪካ የሚገቡ ምርቶች ላይ የጣለችውን ታሪፍ ሙሉ በሙሉ ያነሳችው እስራኤል 17 በመቶ ታሪፍ የተጣለባት ሲሆን በዚህም "እጅጉን መደናገጣቸውን" የአገሪቱ ባለስልጣናት ለመገናኛ ብዙኃን ተናግረዋል።
"ከአሜሪካ ወደ አገር ውስጥ በሚገቡ ምርቶች ላይ የተጣለውን ታሪፍ ሙሉ በሙሉ ለመሰረዝ ስንወስን ይህን እርምጃ እንደሚያስቀር እርግጠኞች ነበርን።"
የዋይት ኃውስ ባለስልጣናት በአሜሪካ ምርቶች ላይ ከፍተኛ የሆነ ታሪፍ በሚጥሉ እንደ ቻይና ላሉ አገራት የተሰጠ ምላሽ መሆኑን ገልጸዋል።
የአውስትራሊያ ጠቅላይ ሚኒስትር አንቶኒ አልባኔዝ አገራቸው 10 በመቶ ታሪፍ ከተጣለባቸው መካከል መሆኗን ጠቅሰው፣ አሜሪካውያን ከፍተኛ የሆነ "ያልተገባ ታሪፍ" ይከፍላሉ ብለዋል።
መንግሥታቸው የአጸፋ እርምጃዎችን እንደማይወስድ የገለፁት ጠቅላይ ሚኒስትሩ "ዝቅተኛ ዕድገት የሚያመራ ፉክክር ውስጥ አንቀላቀልም" ብለዋል።
በላቲን አሜሪካ የግዙፍ ኢኮኖሚ ባለቤት የሆነችው ብራዚል በትራምፕ የተጣለውን የ10 በመቶ ታሪፍ በመቃወም አዲስ ሕግ አጽድቃለች።
የአገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር " የአጸፋ እርምጃ ለመውሰድ የዓለም ንግድ ድርጅትን ጨምሮ የሁለትዮሽ ንግድ ውስጥ ያሉንን አማራጮች በሙሉ እንገመግማለን" ብለዋል።
ዶናልድ ትራምፕ አዲሱን ታሪፍ ይፋ ካደረጉ በኋላ የአሜሪካ የገንዘብ ሚኒስትር ስኮት ቤሴንት አገራት "የአጸፋ ምላሽ እንዳይሰጡ" አስጠንቅቀው፣ የፕሬዝዳንቱን ውሳኔ"በጸጋ እንዲቀበሉ" ተናግረዋል።












