የደቡብ አፍሪካው ፕሬዝደንት ከትራምፕ ጋር ያለውን ውጥረት ለማርገብ ለኢላን መስክ ስልክ ደወሉ

የፎቶው ባለመብት, SA Presidency
የደቡብ አፍሪካው ፕሬዝደንት ሲሪል ራማፎሳ በመሬት ሕግ ምክንያት ከአዲሱ የአሜሪካ አስተዳደር ጋር የገቡትን ውጥረት ለማርገብ ኢላን መስክን አነጋግረዋል።
የፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ የቅርብ አማካሪ የሆነው ቢሊየነሩ ኢላን መስክ ደቡብ አፍሪካ ነው የተወለደው።
ትራምፕ ደቡብ አፍሪካ አከራካሪ የመሬት ሕግ አውጥታለች በሚል አሜሪካ የምታደርገውን ድጋፍ እንደሚያቋርጡ ዝተዋል። ትራምፕ፤ ደቡብ አፍሪካ መሬት እየነጠቀች ነው እንዲሁም "የተወሰነ የኅብረተሰብ ክፍል እየበደለች ነው" ሲሉ ወቅሰዋል።
ኢላን መስክም ተደምሮ ኤክስ በተባለው ማኅበራዊ ሚድያው "በግልፅ ዘረኛ የሆነ የመሬት ሕግ" ሲል ራማፎሳን ወቅሷል።
የራማፎሳ ቢሮ ባወጣው መግለጫ ፕሬዝደንቱ ለኢላን መስክ ስልክ መደወላቸውን አስታውቆ "ደቡብ አፍሪካ በሕገ-መንግሥት የፀና የሕግ የበላይነት፣ ፍትሕ እና እኩልነት ያላት ሀገር ናት" ማለታቸውን ገልጿል።
ባለፈው ወር ፕሬዝደንት ሲሪል ራማፎሳ ሕግ እንዲሆን ያወጁት ረቂቅ በአንዳንድ ሁኔታዎች መሬት ያለምንም የካሳ ክፍያ ሊወሰድ ይችላል ይላል።
ደቡብ አፍሪካ ውስጥ የመሬት ባለቤትነት ጉዳይ ለረዥም ዓመታት እጅግ አከራካሪ ሆኖ የቆየ ጉዳይ ሲሆን ምንም እንኳ ዘረኛ የሆነው የአፓርታይድ ዘመን ካበቃ 30 ዓመታት ቢቆጠሩም አብዛኛው የግል መሬት የተያዘው በነጮች ነው።
የደቡብ አፍሪካው ፕሬዝደንት ለትራምፕ በሰጡት ምላሽ መንግሥታቸው "ምንም ዓይነት መሬት እንዳልነጠቀ" ተናግረው ነበር።
ባለፈው እሑድ ትራምፕ ትሩዝ ሶሻል በተባለው ማኅበራዊ ድር "ሁኔታው ተመርምሮ እስኪጣራ ድረስ ለደቡብ አፍሪካ የምንሰጣቸውን ድጋፎች ሙሉ በሙሉ እናቆማለን" የሚል መልዕክት አስተላልፈዋል።
ቀጥለው ደግሞ በአንድ ጋዜጣዊ መግለጫ "የደቡብ አፍሪካ መንግሥት እጅግ አስከፊ ድርጊት እየፈፀመ ነው" ሲሉ ወቅሰዋል።
የደቡብ አፍሪካ አዲሱ የመሬት ሕግ መንግሥት ምንም ካሳ ሳይከፍል መሬት የሚወስደው "ፍትሐዊ እና የሕዝብን ፍላጎት ባሟላ መልኩ ነው" ይላል።
ለምሳሌ መሬቱ ጥቅም ላይ እየዋለ ካልሆነ፣ አሊያም ባለቤቶቹ ጥቅም ላይ ሊያውሉት ካልፈቀዱ፣ ወይም ገንዘብ እያፈሩበት ካልሆነ እንዲሁም ለሕዝቡ አደጋ የሚሆነ ከሆነ ይላል።
የብሪታኒያ ቅኝ ግዛት አመራር በአውሮፓውያኑ 1913 ነው ጥቁር ደቡብ አፍሪካዊያን የመሬት ባለቤት መሆን አይችሉም የሚል ሕግ ያወጣው። ከዚህ ጊዜ ጀምሮ በደቡብ አፍሪካ የመሬት ባለቤትነት ጉዳይ አከራካሪ ሆኖ ቆይቷል።
ኔቲቭስ ላንድ አክት የተባለው ሕግ አብዛኛው ለም መሬት በነጭ ዜጎች ተይዞ ጥቁሮች ወደላደጉ ቦታዎች እንዲሄዱ ያስገደደ እና በሀገሪቱ ዜጎች መካከል ከፍተኛ መከፋፈል የፈጠረ ነው።
በ1994 ኔልሰን ማንዴላ የመጀመሪያ በዲሞክራሲያዊ መንገድ የተመረጡ ፕሬዝደንት ሆነው ሲመጡ ይህን ጉዳይ ይፈታሉ ተብሎ ተጠብቆ ነበር።
በ2017 መንግሥት ያወጣው መረጃ እንደሚጠቁመው 72 በመቶ የሚሆነው የእርሻ መሬት በነጮች ይዞታ ሥር ይገኛል። በ2022 የሕዝብ ቆጠራ መሠረት በደቡብ አፍሪካ ነጮች ከጠቅላላው ሕዝብ 7.3 በመቶ ያክል ናቸው።












