ቆሻሻ አስወጋጆች ቴሌቪዥን እና ኮምፒውተሮችን የሚያቃጥሉት ለምንድነው?

አገልግሎታቸውን የጨረሱ ኤሌክትሮኒክ ዕቃዎች ተጥለው

ከአግቦግብሎሺ ቆሻሻ መጣያ የሚወጣው ጭስ ከብዝ ኪሎ ሜትሮች ርቀት ይታያል።

በጋና መዲና አክራ ምዕራባዊ ክፍል የሚገኘው ይህ ቦታ በጭስ ታፍኗል። የሚሳበው አየር መርዛማ ነው። ጠጋ ባሉ ቁጥር ትንፋሽ እያጠረዎት ይሄዳል፤ ዕይታዎ ይጋረዳል።

ይህን ጭስ ከበው የቆሙ በርካታ ወንዶች ይታያሉ። የቆሻሻ መኪናዎችን ነው የሚጠብቁት። የወጣቶቹ ሥራ ቆሻሻውን ከእሳት ማያያዝ ነው።

ሌሎቹ ደግሞ የቆሻሻውን ተራራ ወጥተው ቴሌቪዥን፣ ኮምፒውተር እና የልብስ ማጠቢያ መሽን ይዘው ይመጣሉ። ከዚያም ያቃጥሏቸዋል።

ቆሻሻ ከማቃጠል ባለፈ በኤሌክትሪክ ከሚሠሩት የወደቁ ዕቃዎች መዳብ እና ወርቅ ይለቅማሉ።

በእንግሊዝኛው ኢ-ዌስት የሚባሉት በኤሌክትሪክ የሚሠሩ ዕቃዎች አገልግሎታቸውን ጨርሰው ሲጣሉ ነው። እኒህ ዕቃዎች የማምረት አቅም ካላቸው አገራት መጥተው የሚራገፉት እንደ ጋና ባሉ ሀገራት ነው።

ወጣቱ አብዱላ ያኩቡ “ጤንነት አይሰማኝም” ይላል። ዓይኖቹ ደም የለበሱ መስለዋል። ውሀ ቋጥረዋል። ሥራው ገመድ እና ፕላስቲክ ማቃጠል ነው።

“አየሩ እንደምታዩት በጣም የተበከለ ነው። እኔ ደሞ እዚህ በየቀኑ መሥራት አለብኝ። ጤናችን መጎዳቱ የማይቀር ነው” ይላል።

ወጣቶች በጋና ቆሻሻ ሲያቃጥሉ

አቢባ አልሀሳን የአራት ልጆች እናት ናት። የተጣሉ ኤሌክትሮኒክ ዕቃዎች በሚጣሉበት አካባቢ የፕላስቲክ ጠርሙሶችን መሰብሰብ ነው ሥራዋ። ለመርዛማው ጭስ በጣም ቅርብ ናት።

“አንዳንድ ጊዜ መተንፈስ እንኳ ይከብዳል። ደረቴ አካባቢ የሚከብድ ስሜት ይሰማኛል። ጤናዋ ሲናጋ ይታወቀኛል ትላለች።

ኢ-ዌስት በዓለማችን እጅግ እየተስፋፋ ያለ የቆሻሻ አወጋገድ ሥርዓት ነው። በአውሮፓውያኑ 2022 ብቻ 62 ሚሊዮን ቶን ቆሻሻ ተሰብስቧል። ይህ ከ2010 ጋር ሲነፃፀር 82 በመቶ ከፍ ያለ ነው ይላል የተባበሩት መንግሥታት መረጃ።

ሰዎች በኤሌክትሪክ የሚሠሩ ዕቃዎችን መጠቀም ማበርከታቸው ነው ለኢ-ዌስት ትልቅ አስተዋፅዖ ያደረገው። ከተንቀሳቃሽ ስልኮች ጀምሮ፣ ኮምፒውተሮች ሌሎችም ሌሎችም ተፈላጊነታቸው እጅግ እየጨመረ መጥቷል።

በያዝነው የአውሮፓውያኑ ዓመት የወጣ የተባበሩት መንግሥታት ንግድ እና ዕድገት መረጃ እንደሚያሳየው ከ2010 ጀምሮ መተርተው በዓለም ዙሪያ የሚዘዋወሩ የስማርት ተንቀሳቃሽ ስልኮች ቁጥር በእጥፍ አድጎ በ2023 1.2 ቢሊዮን ደርሷል።

ቆሻሻ ማጓጓዝ

የተባበሩት መንግሥታት እንደሚለው ቆሻሻ ተብሎ ከሚጣለው የኤሌክቶሮኒክ ቆሻሻ 15 በመቶው ብቻ ነው ድጋሚ ጥቅም ላይ የሚውለው። ለዚህ ነው ኩባንያዎች ቆሻሻውን አርቀው የሚጥሉት።

እኒህ ፕላስቲኮችን መልሶ ጥቅም ላይ ማዋል ቀላል አይደለም። መርዛማ የሆኑ ኬሚካሎች፣ ብረት እና ሌሎች ነገሮችን በመያዛቸው በቀላሉ መለየት እና ድጋሚ ጥቅም ላይ ማዋል ከባድ ይሆናል።

ያደጉ የሚባሉት ሀገራት እንኳ ኢ-ዌስት የሚያስወግዱበት መንገድ የላቸውም።

የተባበሩት መንግሥታት መርማሪዎች እንደሚሉት ከጥቅም ውጭ የሆኑት ኤሌክትሮኒክ ዕቃዎች ያደጉ ከሚባሉ አገራት ወደ አዳጊ አገራት እየተጓጓዙ ነው። ከአንድ ሀገር ወደ ሌላ ሀገር ሲጓጓዙ በቁጥጥር ሥር ከሚውሉ ዕቃዎች አብዛኛዎቹ ኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎች መሆናቸው ዓለም አቀፉ የጉምሩክ ድርጅት መረጃ ያሳያል።

በጣሊያኗ ኔፕልስ ከተማ በሚገኘው ወደብ ያሉ ፖሊሶች ለቢቢሲ ካሳዩት በቁጥጥር ሥር የዋለ ዕቃ መካከል 30 በመቶው የሚሆነው ያረጀ ኤሌክትሮኒክስ ነው።

በኮንቴይነር የተጫነው ኢ-ዌስት ማደረሻው አፍሪካ ሲሆን መኪና የሚል ጽሑፍ ተጽፎበታል። ነገር ግን ፖሊስ የጭነት ማጓጓዣውን ሲከፍተው የተሰባበሩ የመኪና ዕቃዎች የኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎች ሆነው ተገኝተዋል። አንዳንዶቹ ዕቃዎች ዘይት መልክ ፈሳሽ ማፍለቅ ጀምረዋል።

ቆሻሻ የሚሰበስብ ግለሰብ

የተራቀቁ የማጓጓዣ መንገዶች

የዩናይትድ ኪንግደም ባለሥልጣናት ከቦታ ቦታ የሚጓጓዙ የኤሌክትሮኒክስ ቆሻሻዎች ቁጥር እየጨመሩ መሆኑን ይናገራሉ።

የዩኬ ተፈጥሮ ጥበቃ ባለሥልጣን ቃል አቀባይ ቤን ራይደር እንደሚሉት እኒህ ከጥቅም ውጭ የሆኑ ኤሌክትሮኒክ ዕቃዎች ድጋሚ ጥቅም ላይ ይውላሉ በሚል እንደ ጋና ወዳሉ ሀገራት ቢጓዙም “ተሰባብረው ውድ የሚባሉ ማዕድኖች ይወጡባቸዋል፤ አሊያም በሕገ-ወጥ መንገድ ይቃጠላሉ።”

ቃል አቀባዩ አክለው እንደሚገልጡት ሕገ-ወጥ አዘዋዋሪዎች ኤሌክትሮኒክ ቆሻሻዎችን የሚያጓጓዙት ከሌሎች ዕቃዎች ጋር በመቀየጥና ሕጋዊ በማስመሰል ነው።

ዓለም አቀፉ የጉምሩክ ድርጅት ከዚህ ቀደም ባወጣው መረጃ ያረጁ መኪናዎች ዝውውር እጅግ በርክቶ 700 በመቶ አድጓል ብሎ ነበር። እኒህ ያረጁ መኪናዎች ትልቅ የኢ-ዌስት ምንጭ ናቸው።

ምንም እንኳ ያረጁ ኤሌክትሮኒክ ዕቃዎች ካደጉ ሀገራት ተጓጉዘው ወዴት እንደሚሄዱ የሚያሳይ ግልፅ መረጃ ባይኖርም በተለይ የደቡብ እስያ ሀገራት ትልቅ መዳረሻ እንደሆኑ የተባበሩት መንግሥታት መረጃ ያሳያል።

ነገር ግን እኒህ የደቡብ እስያ ሀገራት የኤሌክትሮኒክ ተረፈ ምርት ጉዞ ላይ የተለያዩ ዕቀባዎችን መጣል መጀመራቸውን ተከትሎ አዲሷ መዳረሻ አፍሪካ ሆናለች።

ሕገ-ወጥ አዘዋዋሪዎች አዳዲስ መላዎችን በመጠቀም የአግለግሎት ጊዜያቸውን ያበቁ ኤሌክትሮኒክ መሣሪያዎች ከአህጉር አህጉር እያጓጓዙ ይገኛሉ።

ከሕገ-ወጥ የኤሌክትሮኒክ ተረፈ ምርት ዝውውር እየተጠቀሙ ያሉ በርካታ ዓለም አቀፍ ቡድኖች አሉ።

ቆሻሻ የሚከመርበት ቦታ

አሳሳቢ ኬሚካል

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ኢ-ዌስት ሲጣል አሊያም ሲቃጠል በውስጡ ያዘላቸው ፕላስቲክ እና ብረታ ብረቶች ለሰው ልጅ ጤና እጅግ ጎጂ ሊሆኑ ይችላሉ፤ አልፎም አካባቢ ይበክላሉ ይላል የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ።

ድርጅቱ እንደሚለው እያደጉ ባሉ ሀገራት የቆሻሻ ማስወገድ እና ማቃጠል ሥራ የሚሠሩት ሕፃናት እና ሴቶችን ጨምሮ ሥልጠና የሌላቸው ሰዎች ሲሆኑ ምንም ዓይነት የመከላከያ መሣሪያ አይጠቀሙም። በዚህ ምክንያት ሊድ ለተባለው ኬሚካል እና ለሌሎች መርዛማ ጭሶች እየተጋለጡ ነው።

ዓለም አቀፉ የሠራተኞች ድርጅት እና የዓለም ጤና ድርጅት ቆሻሻ በማስወገድ ላይ የተሰማሩ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሴቶችና ሕፃናት ለአደጋ ሳይጋለጡ አይቀሩም ይላሉ።

ድርጅቶቹ አክለው በፅንስ እና በጨቅላነት ዕድሜ ለመርዛማ ጭስ መጋለጥ የዕድገት መቀንጨር ሌሎች የነርቭ ችግሮች ሊያስከትል ይችላል።

ዓለም አቀፍ የቆሻሻ ማስወገድን በተለመከተ የተፈረመው የባዜል ስምምነት ከአውሮፓውያኑ 2025 ጀምሮ ቆሻሻ የሚያጓጉዙ ድርጅቶች ያለፈቃድ መንቀሳቀስ እንደማይችሉ ያትታል። ምናልባት ይህ ስምምነት ሕገ-ወጥ የቆሻሻ አዘዋዋሪዎች ቀዳዳ ተጠቅመው እንዳይንቀሳቀሱ ሊያደርጋቸው ይችላል የሚል ተስፋ አለ።

ነገር ግን አሜሪካን ጨምሮ አቢይ የሚባሉ ቆሻሻ የሚልኩ ሀገራት የባዜል ስምምነትን አልፈረሙም። ይህ ደግሞ ኢ-ዌስትን ለመቆጣጠር የሚደረገውን ጥረት አዳጋች ያደርገዋል።

የባዜል አክሽን ኔትዎርክ ኃላፊ ጂም ፓኬት አሜሪካ ወደ ሜክሲኮ በርካታ የኤሌክትሮኒክስ ተረፈ ምርት እያጋዘች ነው ይላሉ።

በጋና ‘ቆሼ’ ያለው ሁኔታ ከቀን ወደ ቀን እየከፋ መጥቷል።

አቢባ ቆሻሻ በመልቀም ከምታገኘው ገንዘብ ግማሹን የምታጠፋው በመርዛማው ቆሻሻ ምክንያት ከሚደርስባት ሕመም ለማገገም መድኃኒት በመግዛት እንደሆነ ትናገራለች።

“ቢሆንም አሁንም እዚሁ ነኝ። ምክንያቱም ከዚህ በማገኘው ገቢ ነው የራሴንና የቤተሰቦቼን ሕይወት የምመራው።”

የጋና ገቢዎች ባለሥልጣን እና የአካባቢ ጥበቃ ሚኒስቴር ከቢቢሲ ተደጋጋሚ ጥያቄዎች ቢቀርብላቸውም ምላሽ ሊሰጡ አልፈቀዱም።