ስለቴስላ ሳይበርትራክ የሚታወቁ ዋና ዋና እውነታዎች

የቴስላ ሳይበርትራክ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የኤሌክትሪክ መኪና አምራቹ ቴስላ ሳይበርትራክ ሲል ስያሜ የሰጠውን መኪናውን በአውሮፓውያኑ 2019 ነበር ያስተዋወቀው።

መኪናው በኤሌክትሪክ የሚሠራ ነው።

የስፔስ ኤክስ ባለቤት እና የዓለማችን ቁጥር አንድ ሃብታም የሆነው ኢላን መስክ የቴስላ ባለቤት ነው።

የመኪናው ዲዛይን ከጄምስ ቦንድ ፊልም ላይ የተወሰደ መሆኑን ቢሊየነሩ በወቅቱ አስታውቆ ነበር።

መኪናው ለዕይታ በቀረበበት ወቅት ሁሉም ነገር እንደታሰበው ሊሳካ አለመቻሉ በብዙዎች ዘንድ መነጋገሪያ እንዲሆን አድርጎታል።

መኪናው የማይሰበር እና ለመስታወት ሥራ ጥቅም ላይ ከሚውሉ የተለመዱት ቁሳቁሶች የበለጠ ጠንካራ እንዲሆን ታስቦ መሠራቱን መስክ በወቅቱ አስታውቆ ነበር።

መስክ አይሰበርም ብሎ ከመናገሩም በላይ መስታወቱን በመዶሻ በመስበር እንዲሞክሩ ሰዎችን ሲጋብዝ ነበር። መኪናው በሚተዋወቅበት መድረክ ላይ ጥንካሬውን ለመለካት የተደረገው ሙከራ ሳይሳካ ቀርቶ መስታወቱ ተሰበረ።

ኢላን መስክ ብዙ እንግዳ እና ድንቅ ፈጠራዎችን ለዓለም አስተዋውቋል። ከዓመታት በፊት የግል መኪናውን ወደ ምህዋር ልኳል።

ይህንን ያደረገው ደግሞ ፋልከን ሄቪ የተሰኘውን የዓለማችንን ጠንካራ ሮኬት በመጠቀም ነው። በዚህም በተሳካ ሁኔታ መኪናውን ወደ ጠፈር እንዲደርስ አድርጓል።

ለመሆኑ ስለሳይበርትራክ የሚታወቁ ዋና ዋና ጉዳዮች የትኞቹ ናቸው።

ዋጋ

የመስክ ሳይበርትራክ መኪና መጀመሪያ ላይ የነበረው ዋጋ 38 ሺህ ዶላር ገደማ ነበር።

መኪናው አሁን ዋጋው በከፍተኛ ደረጃ ጨምሯል።

ሳይበርትራክ በአሜሪካ ገበያ ላይ ከ79 ሺህ 990 ዶላር ጀምሮ በመሸጥ ላይ ይገኛል።

ሳይበርቢስት የተሰኘው የዚህ መኪና ዝርያው ደግሞ 99 ሺህ 990 ዋጋ እንዳለው ለማወቅ ተችሏል።

ቴስላ ዝቅተኛ ዋጋ ያለውን ሳይበርትራክ ለአነስተኛ ጊዜ ለገበያ አብቅቶ ነበር። ይህ መኪና 60 ሺህ 990 ዶላር ይሸጥ የነበረ ቢሆንም አሁን ከገበያ እንዲወጣ ተደርጓል።

ገዢዎች ለሳይበር ትራክ ያላቸው ፍላጎት በመቀነሱ ምንክንያት ግዢው እየወረደ መምጣቱ ታውቋል።

ለዚህም አንደኛው ምክንያት መኪናው ውድ መሆኑ ነው። ዋጋውን መቀነስ ካልቻለ ፉክክሩ እንደሚከብደው እየተገለጸ ይገኛል።

የፍላጎት መቀነስን ምክንያት በማድረግ ኩባንያው ከዚህ ቀደም ባመረታቸው የመኪና ዓይነቶች ላይ እንዳደረገው ሁሉ የዋጋ ቅናሽ እንዲያደርግ ሊገደድ ይችላል ሲል ፎርብስ ጽፏል።

የዓለማችን ቁጥር አንድ ሃብታም የሆነው ኢላን መስክ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ፉክክር

ሳይበርትራክ በአውሮፓውያኑ 2024 አሜሪካ ውስጥ ለሽያጭ ከቀረቡ የኤሌክትሪክ መኪኖች በአምስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። በተመሳሳይ ዓመት ውስጥ 39 ሺህ ሳይበርትራኮች አሜሪካ ውስጥ ተሽጠዋል።

የቻይናው የኤሌክትሪካ መኪና አምራች ቢዋይዲ በ2024 ከፍተኛ ሽያጭ በማድረግ ከኢላን መስክ ድርጅት ጋር እየተገዳደረ መሆኑ ተዘግቧል።

ድርጅቱ በፈረንጆቹ ታኅሣሥ ወር ብቻ 207 ሺህ 734 የኤሌክትሪክ መኪኖችን ሸጧል። ይህ ጠቅላላ ዓመታዊ ሽያጩን ወደ 1.76 ሚሊዮን ዶላር ከፍ አድርጎታል።

ድጎማዎች እና የዋጋ ቅናሾች ደንበኞች ቢዋይዲ መኪናዎችን እንዲገዙ ምክንያት ሆነዋል ተብሏል።

መቀመጫውን ሼንዜን ያደረገው የቻይናው ድርጅት ከቴስላ ጋር ያለውን ልዩነት እያጠበበው ይገኛል።

ቢዋይዲ ዓመታዊ ሽያጩ ካለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር 41 በመቶ ከፍ ብሏል። ይህ ጭማሪ የመጣው የሀይብሪድ (ነዳጅ እና ኤልክትሪክ የሚጠቀሙ) መኪኖች ሽያጭ ከፍ በማለቱ ነው።

የቻይናው ኩባንያ ሽያጩ እንዲጨምር ምክንያት ከሆኑት ጉዳዮች አንዱ በሀገር ቤት ባለው የመኪና ገበያ ፉክክር ምክነያት ዋጋው ዝቅ እንዲል ማድረጉ እንዲሁም መንግሥት ዜጎች የቆዩ መኪኖዎቻቸውን በኤሌክትሪክ መኪና እንዲተኩ ድጎማ ማድረጉ ነው ተብሏል።

ቢዋይዲ 90 በመቶ መኪናዎቹን የሚሸጠው ቻይና ውስጥ ነው።

ለዕታ በበቃበት ወቅት የተሰበረው የሳይበርትራክ መስታወት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ውጣ ውረድ

ሳይበርትራክ በርካታ ውጣ ወረዶች ውስጥ ለማለፍ ተገዷል።

እአአ በ2019 ለዕይታ ሲበቃ መስታወቱ አይሰበርም በሚል የተደረገውን ሙከራ ማለፍ አለመቻሉ የመጀመሪያው ፈተናው ሆኖ ታይቷል።

ከዚህ በኋላም ቢሆን 150 ሺህ ትዕዛዝ መቀበሉን የአምራቹ ድርጅት ባለቤት መስክ ገልጾ ነበር።

ከደኅነነት ጋር በተያያዘ በሺህዎች የሚቆጠሩ የቴስላ መኪኖች ከአንድ ዓመት በፊት ከገበያ እንዲሰበሰቡ ተደርገዋል።

በወቅቱ መኪናው የፍጥነት መጨመሪያው ሲረገጥ ተጣብቆ እየቀረ ተደጋጋሚ የግጭት አደጋ በማስከተሉ ነበር መኪኖቹ እንዲሰበሰቡ የተደረጉት።

ባለፈው የአውሮፓውያን ዓመት (2024) የመጀመሪያ ወራት ሽያጩ በመውረዱ የቴስላ የአክሲዮን ዋጋም እንዲያሽቆለቁል ምክንያት ሆኗል።

መኪናው በአንድ ቻርጅ እስከ 800 ኪሎ ሜትር እንደሚጓዝ ቢጠበቅም ይህንን ግብ ለማሳካት ሳይቻለው ቀርቷል።

ሳይበርትራክ በአንድ ጊዜ ቻርጅ እስከ 520 ኪሎ ሜትር እንደሚጓዝ ቴስላ ይፋ አድርጓል።

በዚህ ረገድ የጠበቀውን ያህል ባይሆንም በገበያ ላይ ካሉ የኤሌክትሪክ መኪኖች አንጻር ጥሩ የሚባል መሆኑን ባለሙያዎች ጠቁመዋል።