ቤቱ ውስጥ በታጣቂዎች የተገደለው የጋዳፊ 'ተወዳጅ ልጅ' ሳይፍ አል-ኢስላም ማን ነው?

ሳይፍ አል-ኢስላም ጋዳፊ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, ሳይፍ አል-ኢስላም ጋዳፊ ለንደን ስኩል ኦፍ ኢኮኖሚክስ ነው የተማረው።
የንባብ ጊዜ: 6 ደቂቃ

የቀድሞው የሊቢያ መሪ ልጅ ሳይፍ አል-ኢስላም ጋዳፊ፤ በምዕራባውያን ዘንድ ራሱን ያስተዋውቅ የነበረው 'ተቀባይነት ያለው የሊቢያ ገጽታ' እንደሆነ ነበር።

የአባቱ ሥልጣን ሲንኮታኮት ግን ማንነቱ እየተለወጠ መጣ። በታዋቂው የለንደን ስኩል ኦፍ ኢኮኖሚክስ ነው የተማረው። አባቱ ከሥልጣን ሲወገዱ በአንድ ጀንበር የአባቱ የጋዳፊ ዋነኛ ተከላካይ ሆነ።

አባቱ ኮሎኔል ሞአመር ጋዳፊ ገናና ሳሉ ይዝናና የነበረው እንደ ዊንደሰር ካስል ባሉ የልዑላውያን ቤተ መንግሥቶች ውስጥ ነው።

'አረብ ስፕሪንግ' ሲቀጣጠል ሊቢያውያንም ተቃውሞውን ተቀላቀሉ። በቱኒዚያ እና በግብፅ መንግሥታት ሲገለበጡ፤ ሳይፍ አል-ኢስላም ጋዳፊ የአባቱን መንበር ለማስጠበቅ ላይ ታች ይል ጀመር።

ለአባቱ ታማኝ የሆኑ አገልጋዮች ተቃዋሚዎች ላይ ጭካኔ የተሞላው እርምጃ እንዲወስዱ አበረታትቷል።

"እስከ መጨረሻው ደቂቃ እና እስከ መጨረሻው ጥይት" እንዲዋጉ አሳስቧል።

የመንግሥታቱ ድርጅት በሰጠው ይሁንታ የሰሜን አትላንቲን የጦር ቃልኪዳን (ኔቶ) ኃይሎች የጋዳፊ መንግሥት ላይ ጥቃት ሲፈጽሙ፤ ሳይፍ አል-ኢስላም አባቱን መከላከሉን ቀጠለ።

ጋዳፊ እንደ አውሮፓውያኑ ከ1969 አንስቶ ሊቢያን አንቀጥቅጠው መርተዋል።

የጋዳፊ ቤተሰብ የአገሪቱን አማጺያን 'አይጦች' ሲላቸው፤ የኔቶን ኃይል 'የቅኝ ግዛት መሣሪያ' ብሎ አጣጥሏል።

አባቱ ከሥልጣን ሲወገዱ በአንድ ጀንበር የአባቱ የጋዳፊ ዋነኛ ተከላካይ ሆነ።

የፎቶው ባለመብት, AFP

የምስሉ መግለጫ, አባቱ ከሥልጣን ሲወገዱ በአንድ ጀንበር የአባቱ የጋዳፊ ዋነኛ ተከላካይ ሆነ።

'የለውጥ ኃይል'

የጋዳፊ መንግሥት ውድቀት ሲቃረብ ልጃቸው ጢሙን አሳድጎ፣ በአማጺያን ላይ በሚወሰደው እርምጃ አክራሪ እስላማዊ ቡድኖች እንደሚሳተፉ ዛተ።

ጋዳፊ፣ ልጃቸው እና የያኔው የሊቢያ የደኅንነት ኃላፊ አብዱላህ አል-ሴኑሲ በሰብአዊነት ላይ በተፈጸሙ ወንጀሎች በዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት ተከስሰዋል።

ሳይፍ አል-ኢስላም ጋዳፊ ምዕራባውያንን በወቅቱ እያስፈራራ ነበር። "ትልቅ ስህተት እየሠራችሁ ነው። የምትደግፉት የተሳሳቱ ሰዎችን ነው" ብሏቸዋል። ያኔ 'የሊቢያ ተቀባይነት ያለው ገጽታ' የሚለው ስሙ እና የምዕራባውያን ወዳጅነቱ ተሸረሸረ።

የስሙ ትርጓሜ 'የእስላም ሰይፍ' ማለት ነው።

'የለውጥ ኃይል' ተደርጎ ይወሰድ የነበረው ሳይፍ አል-ኢስላም ጋዳፊ ከአባቱ ጋር በተያያዘ ከምዕራባውያን ጋር ተቆራረጠ።

ቀደም ባለው ጊዜ ከምዕራባውያን ጋር ባለው ወዳጅነት ምክንያት ሊቢያ የኒውክሌር መሣሪያ እንዳትገነባ አሳምኖ ነበር።

ሊቢያ ላይ የተጣሉ ማዕቀቦች እንዲነሱ እና በነዳጅ ዘርፍ ኢንቨስትመንት እንዲስፋፋ አስችሎም ነበር።

በአባቱ የአመራር ዘመን ይፋዊ ሥልጣን ባይኖረውም ፖሊሲ በመቅረጽ እና ትልቅ ቦታ የሚሰጣቸው ድርድሮች በመምራት ይታወቃል።

አባቱ እንደ አውሮፓውያኑ በ2011 ከሥልጣን ሲወገዱ ሳይፍ አል-ኢስላም በሚሊሻዎች ቁጥጥር ሥር ውሎ ነበር።

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, አባቱ እንደ አውሮፓውያኑ በ2011 ከሥልጣን ሲወገዱ ሳይፍ አል-ኢስላም በሚሊሻዎች ቁጥጥር ሥር ውሎ ነበር።

ሳይፍ አል-ኢስላም 'እጅግ ከሚፈለጉ' ወንጀለኞች ዝርዝር ውስጥ

በሊቢያ ዴሞክራሲያዊ ለውጥ እንዲመጣ ንቅናቄ የተጀመረበት ወቅት ነበር።

በአውሮፓውያኑ 1988 በተፈጸመው የቦምብ ድብደባ ምክንያት በስኮትላንዷ ከተማ ሎከርቢ 270 ሰዎች መገደላቸውን ተከትሎ የሟቾች ቤተሰቦች ካሳ እንዲያገኙ የሚጠይቅ የተራድኦ ድርጅት መሥርቷል።

ከቢቢሲ ጋር በአውሮፓውያኑ 2008 ባደረገው ቃለ ምልልስ ለዚህ ጥቃት ሊቢያ ኃላፊነት ብትወስድም "ጥፋተኛ" እንዳልሆነች ተናግሯል።

ለንደን ስኩል ኦፍ ኢኮኖሚክስን ጨምሮ ለሌሎች ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የገንዘብ ድጋፍ ያደርግም ነበር። በዚህ ትምህርት ቤት የዶክትሬት ዲግሪውን ሠርቷል።

በለንደን በሚገኘው ቅንጡ የመኖሪያ ሰፈር 'ሀምፓስድ ጋርደን' በነበረው መኖሪያው አሜሪካውያን ቢልየነሮች፣ እንደ ፒተር ማንደልሰን ያሉ ፖለቲከኞች እና ነጋዴዎች ይገኙ ነበር።

በመኖሪያው ከተጋበዙ ታዋቂ ሰዎች መካከል የሞናኮ ልዑል አልበርት ይገኙበታል።

ከጋዳፊ ሞት በኋላ ሊቢያ በሁለት ተከፍላ በተቀናቃኝ አስተዳደር ሥር ወድቃለች።

የምዕራብ እና ምሥራቅ ሊቢያ መሪዎች መገዳደራቸው ሲቀጥሉ፤ የመንግሥታቱ ድርጅት ድጋፍ የሰጠው የትሪፖሊ ብሔራዊ አንድነት መንግሥት እንዲሁም ዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት ሳይፍ አል-ኢስላም ጋዳፊን ማፈላለግ ቀጠሉ።

'እጅግ በሚፈለጉ' ወንጀለኞች ዝርዝር ውስጥም ተካቷል።

ለአባቱ ታማኝ የሆኑ አገልጋዮች ተቃዋሚዎች ላይ ጭካኔ የተሞላው እርምጃ እንዲወስዱ አበረታትቷል።

የፎቶው ባለመብት, PA

የምስሉ መግለጫ, ለአባቱ ታማኝ የሆኑ አገልጋዮች ተቃዋሚዎች ላይ ጭካኔ የተሞላው እርምጃ እንዲወስዱ አበረታትቷል።

ፕሬዝዳንት የመሆን ፍላጎት

የተለያዩ ወገኖች ሳይፍ አል-ኢስላም ጋዳፊን ማፈላለጋቸውን ቢቀጥሉም ከአባቱ ደጋፊዎች ጋር በመሆን ሳይያዝ አምልጧል።

በአውሮፓውያኑ 2021 ለፕሬዝዳንትነት እንደሚወዳደር ገልጾ ነበር።

በእርግጥ በአንድ ወቅት ከአባቱ ሥልጣን ለመረከብ ጫፍ የደረሰ ሰው ነበር። ነገር ግን በሊቢያ ተቃዋሚዎች ላይ የደረሰውን በደል መደገፉ ስሙ እንዲጠለሽ አድርጎታል።

በወቅቱ በይነ መረብ ላይ የተለቀቁ ምሥሎች እና ተንቀሳቃሽ ምሥሎች፤ ሳይፍ አል-ኢስላም ከአንድ የማስታወቂያ ፖስተር ፊት ቆሞ በምርጫው ለመሳተፍ ሲመዘገብ አሳይተው ነበር።

በሊቢያ ባሕላዊ ልብስ ያሸበረቀው ሳይፍ አል-ኢስላም ከቁርዐን ላይ ጥቅሶችን እየመዘዘ ሲናገርም ተደምጧል።

ሳይፍ አል-ኢስላም ያለው አቋም እና አባቱ ጋዳፊ ሥልጣን ላይ እያሉ ያሳይ የነበረው አቋም ፍጹም የተለያዩ ሆነው ተስተውለው ነበር።

አባቱ እንደ አውሮፓውያኑ በ2011 ከሥልጣን ሲወገዱ ሳይፍ አል-ኢስላም በሚሊሻዎች ቁጥጥር ሥር ውሎ ነበር።

በዚህ ሁኔታ ስድስት ዓመታት ከቆየ በኋላ ሞት ተፈርዶበት ነበር። ነገር ግን ይህ ፍርድ ኋላ ላይ ሊቀለበስ ችሏል።

የጋዳፊ ልጅ ለፕሬዝዳንትነት ሊወዳደር ሲያስብም በዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት በጦር ወንጀሎች ይፈለግ ነበር።

ሳይፍ አል-ኢስላም በወቅቱ በሊቢያ ዚንታን ከሚገኘው ቅንጡ ቤቱ ሆኖ ከኒው ዮርክ ታይምስ ጋር ያደረገው ቃል ምልልስ ብዙ ተመልካች አግኝቶ ነበር።

የጋዳፊ 'ተወዳጅ' ልጅ ሳይፍ አል-ኢስላም

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የተወለደው በውሮፓውያኑ 1972 ትሪፖሊ ውስጥ ነው። አባቱ ወደ ሥልጣን የመጡት ንጉሥ ኢድሪስ ላይ መፈንቅለ መንግሥት ፈጽመው ነበር።

ሳይፍ ለጋዳፊ ሁለተኛ ልጅ ነው። ጋዳፊ የቀድሞ ነርሳቸው ከነበረችው ከሁለተኛ ባለቤታቸው ሳፊያ ፋርካሽ ሰባት ልጆች ወልደዋል።

በ1986 ምዕራባውያን አባቱ ላይ የወሰዱትን የጭካኔ እርምጃ ተመልክቷል። ትሪፖሊ በሚገኘው የጋዳፊ ቤት ላይ አሜሪካ በሚሳዔል ድብደባ ፈጽማለች።

የማደጎ እህቱ የተገደለችው በዚህ ጥቃት ነበር።

በ1990ዎቹ መባቻ ከትሪፖሊ ዩኒቨርስቲ በኢንጅነሪንግ ሳይንስ የመጀመሪያ ዲግሪውን አገኘ።

በዚያው ዩኒቨርስቲ አርክቴክቸር ተምሯል። ኦስትሪያ ውስጥ በቬይና ዩኒቨርስቲ በቢዝነስ ሁለተኛ ዲግሪ አግኝቷል።

ያኔ ሱፍ ለብሶ በመዘነጥ ይታወቅ ነበር።

አባቱ ከለጆቻቸው አብልጠው የሚወዱት እና ሥልጣናቸውን እንዲረከብ የሚፈልጉት እሱን ነበር።

ወደ አረብ አገራት በሚካሄዱ ጉዞዎች አምነው የሚልኩት ሳይፍ አል-ኢስላምን ነበር።

በሰሜን አፍሪካ እና ደቡብ ምሥራቅ እስያ የተያዙ ምዕራባውያን ታጋቾችን ገንዘብ እየከፈለ የሚያስለቅቀውን የአባቱን ተቋም ይመራ ነበር።

በሊቢያ ተይዘው የነበሩ ስድስት የቡልጋርያ ነርሶች የሞት ፍርድ ተበይኖባቸው የነበረ ሲሆን፤ በጋዳፊ ልጅ አማካኝነት እንዲለቀቁ ከአውሮፓ ኅብረት ጋር ድርድር ተደርጓል።

ነርሶቹ ሕጻናት በኤችአይቪ እንዲያዙ አድርገዋል በሚል ነበር የተከሰሱት።

በዚህ ወቅት ጋዳፊ ልጃቸው ላይ ጥያቄ ማንሳት ጀምረዋል። እሱ ከሚሳተፍበት መገናኛ ብዙኃን ጋር ትስስር ያላቸው ጋዜጠኞች ሲታሠሩ ጋዜጣውም ተዘግቷል።

በአውሮፓውያኑ 2010 የጋዳፊ ፋውንዴሽን ከፖለቲካዊ ተሳትፎ እንደሚወጣ እና አስተዳደሩም እንደሚቀነስም ይፋ ተደረገ።

ሆኖም ግን ጋዳፊ ለልጃቸው ያላቸው አመለካከት እንዳልተለወጠ ብዙዎች ያምናሉ።

ቢሊዮን ዶላሮች የሚያወጣው የሊቢያ ነዳጅ ኢንቨስትመንት ተቋም ተቆጣጣሪ ሳይፍ አል-ኢስላም መሆኑ ለዚህ አስተያየት መነሻ ነው።

የጋዳፊ ልጅ ለፕሬዝዳንትነት ሲወዳደርም በዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት በጦር ወንጀሎች ይፈለግ ነበር።

የፎቶው ባለመብት, AFP

የምስሉ መግለጫ, ለፕሬዝዳንትነት ሊወዳደር ሲያስብም በዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት በጦር ወንጀሎች ይፈለግ ነበር።

ከምዕራባውያን ጋር መቆራረጥ

በምዕራባውያን ዘንድ ያለው ተቀባይነት እየቀነሰ የመጣው አባቱ ከሥልጣን መወገዳቸውን ተከትሎ ባራመደው አቋም ነው።

የጋዳፊ የፀጥታ ኃይል ተቃዋሚዎች ላይ የአየር ድብደባ ሳይቀር ፈጽሟል።

ሳይፍ አል-ኢስላም ጋዳፊ ለንደን ስኩል ኦፍ ኢኮኖሚክስ ሳለ ወዳጆቹ የነበሩ ሰዎች ከእሱ ራሳቸውን ማሸሽ ጀመሩ።

ለንደን ስኩል ኦፍ ኢኮኖሚክስ ፒኤችዲ የሰጠው ሲቪል ማኅበራት በዴሞክራሲ ግንባታ ያላቸው ሚና ላይ ያተኮረ የመመረቂያ ጽሑፍ ካቀረበ በኋላ ነበር።

በተጨማሪም ለዩኒቨርስቲው 1.5 ሚሊዮን ፓውንድ ለመስጠጥም ቃል ገብቶ ነበር።

ሆኖም ግን ዩኒቨርስቲው ከሊቢያ ጋር ያለውን ግንኙነት በአጠቃላይ ማቋረጡን አስታወቀ።

የጥናት ጽሑፉ የተኮረጀ ነው ከተባለ በኋላ ምርመራ እንደሚደረግ እና ፒኤችዲውን እንደሚቀማ ተገልጾ ነበር።

በአውሮፓውያኑ 2011 ወደ ትሪፖሊ የሚወስዱት ሁለት ቁልፍ ከተሞች ዛዊያ እና ጋርያን በአማጺያን ቁጥጥር ሥር ዋሉ።

መዲናዋን ለመያዝ ውጊያም ተጀመረ። ከዚያም ከአባቱ ጋር ሆኖ ወደ አባቱ ትውልድ ከተማ ሲራቴ መሸሹ ተሰማ።

አባቱ ሲገደሉ ወደ ደቡባዊ የአገሪቱ ክፍል ሸሸ። ወደ ኒጀር መሻገሩም ተገለጸ።

የጋዳፊ ደጋፊዎች በብዛት የተደበቁት ኒጀር እንደሆነ ይነገር ነበር።

አባቱ በተገደሉ በሦስተኛው ቀን ኔቶ በዋዲ ዛምዛም ላይ የአየር ጥቃት ሲፈጽም ሦስት ጣቶቹን ቢያጣም ሳይገደል ቀረ።

ዚንታን ውስጥ በሚሊሺያዎች ተያዘ። ሆኖም ግን የተባበሩት መንግሥታት ለሚደግፈው እና ትሪፖሊን ለሚያስተዳድረው መንግሥት አሳልፈው እንደማይሰጡት አስታወቁ።

የትሪፖሊው መንግሥት በአውሮፓውያኑ 2015 በሌለበት በጦር ወንጀሎች ሞት ፈርዶበታል።

ለዓመታት ከታሰረ በኋላ በ2017 ተለቅቋል። ከዚያም በሊቢያ ዚንታን ውስጥ በምሥጢራዊ ቦታ መኖር ጀምሯል።

የሳይፍ አል-ኢስላም ግድያ

ጋዳፊ ከሥልጣን ከተወገዱ በኋላ ሊቢያ በተለያዩ ሚሊሻዎች የምትመራ ሲሆን፤ በአሁኑ ወቅት ሁለት ተቀናቃኝ መንግሥታት አገሪቱን ከፋፍለው ይመራሉ።

ሳይፍ አል-ኢስላም "ሥልጣን በውርስ የሚሰጥ የእርሻ ቦታ አይደለም" በማለት ከአባቱ ጋዳፊ ሥልጣን መውረስ እንደማይፈልግ ደጋግሞ ይናገር ነበር።

ለፕሬዝዳንትነት ሲወዳደር "ቀስ በቀስ ነው መምጣት ያለብኝ። በጥቂት በጥቂቱ አእምሯቸው ላይ መጫወት" ሲል ቃለ ምልልስ ሰጥቶ ነበር።

ከ2005 እስከ 2011 ባሉት ዓመታት ኦርሊ ዊነርማን ከተባለች እስራኤላዊት ተዋናይት እና ሞዴል ጋር በፍቅር ግንኙነት ውስጥ እንደቆየ ይነገራል።

በአውሮፓውያኑ 2016 ደግሞ አንድ የጣልያን ጋዜጣ ትዳር እንደመሠረተ እና የሦስት ዓመት ሴት ልጅ እንዳለው ቢዘግብም ሳይፍ አል-ኢስላም ውሸት ነው ሲል አስተባብሏል።

'ዘ ታይምስ' እንደዘገበው፤ ከአገሪቱ የነዳጅ ሃብት ሽያጭ ወደ 30 ቢሊዮን ዶላር ያህሉ በእጁ ይገኝ ነበር።

ነገር ግን የ53 ዓመቱ ሳይፍ አል-ኢስላም ጋዳፊ እንደተመኘው ሊቢያን ሳይመራ በጥይት ተመትቶ ተገድሏል።

ጠበቃው እንዳሉት ከሆነ "አራት አባላት ያሉት ኮማንዶ" ነው ግድያውን ቤቱ ውስጥ የፈጸመው። ቢሆንም ግን ግድያውን የፈጸመው ቡድን ማን እንደሆነ እስካሁን ግልጽ አይደለም።