የቀድሞው የሊቢያ መሪ ልጅ ሳይፍ አል-ኢስላም ጋዳፊ በጥይት ተመትተው ተገደሉ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የቀድሞው የሊቢያ መሪ ኮሎኔል ሙአመር ጋዳፊ ልጅ ሳይፍ አል-ኢስላም ጋዳፊ በጥይት ተመትተው መገደላቸው ተዘገበ።
በአንድ ወቅት የጋዳፊ ተተኪ ይሆናሉ ተብለው ይጠበቁ የነበሩት የ53 ዓመቱ ሳይፍ ማክሰኞ መገደላቸውን የፖለቲካ ፓርቲያቸው እንዳረጋገጠ የሊቢያ ዜና ወኪል ዘግቧል።
ጠበቃቸው "አራት ሰዎች ያሉት ኮማንዶ" መኖሪያቸው ቤታቸው በሚገኝበት ዚንታን ከተማ ግድያ እንደፈፀመባቸው ለኤኤፍፒ የዜና ወኪል ተናግረዋል።
ጥቃቱን የፈፀመው ቡድን ማን እንደሆነ እስካሁን ግልፅ አይደለም።
እህታቸው ደግሞ በተቃራኒው የሞቱት ሊቢያ ከአልጄሪያ ጋር በምትዋስንበት ድንበር አቅራቢያ እንደሆነ ለሊቢያ ቴሌቪዥን ጣቢያ ተናግረዋል።
ሳይፍ አል-ኢስላም ከአባታቸው ጋዳፊ ቀጥሎ ትልቅ ተጽእኖ ማሳደር የሚችሉ ግለሰብ ተደርገው ይቆጠሩ ነበሩ።
ኮሎኔል ሙአመር ጋዳፊ ከአውሮፓውያኑ 1969 ጀምሮ ሊቢያን ሲመሩ ከቆዩ በኋላ በ2011 በተነሳ ተቃውሞ ምክንያት ከሥልጣን ወርደው መገደላቸው ይታወሳል።
በ1972 የተወለዱት አል-ኢስላም በጋዳፊ የአመራር ዘመን ሊቢያ ከምዕራባዊያን ጋር የነበራትን ግንኙነት ለማለዘብ ብዙ እንደሠሩ ይነገርላቸዋል።
አባታቸው ከሥልጣን ከተወገዱ በኋላ በጋዳፊ ዘመን በነበራቸው ሚና ተከሰው በሚሊሻ ቡድን ቁጥጥር ሥር ውለው በዚንታን ከተማ ለ6 ዓመታት እስር ቤት ቆይተዋል።
ዓለም አቀፉ የጦር ወንጀለኞች ፍርድ ቤት በ2011 በሊቢያ በተነሳው ተቃውሞ ወቅት በሰብዓዊነት ላይ በተፈፀመ ወንጀል ምክንያት ችሎት ሊያቆማቸው ይፈልግ ነበር።
በ2015 በተባበሩት መንግሥታት በሚደገፈው ቡድን በምትመራው ትሪፖሊ ከተማ ተቃውሞን ለማፈን በሚል ወንጀል ፈፅመዋል ተብለው በሌሉበት በሞት እንዲቀጡ ተፈርዶባቸው ነበር።
ነገር ግን ከሁለት ዓመታት በኋላ በ2017 ቶብሩክ የሚገኘው ሚሊሻ በይቅርታ ከእስር ቤት እንዲለቀቁ አደረጋቸው።
ጋዳፊ ከሥልጣን ከወረዱ በኋላ ሊቢያ በተለያዩ ሚሊሻዎች የምትመራ ሲሆን በአሁኑ ወቅት ሁለት ተቀናቃኝ መንግሥታት ሀገሪቱን ከፋፍለው ይዘው ይመራሉ።
አል-ኢስላም በአባታቸው የአመራር ዘመን ኦፊሴላዊ ሥልጣን ባይኖራቸውም ፖሊስ ቀርፀዋል፤ ትልቅ ቦታ የሚሰጣቸውን ድርድሮች መርተዋል እንዲሁም አባታቸው የኒውክሌር ፕሮግራማቸውን እንዲያቋርጡ አድርገዋል።
በዚህ ምክንያት ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በሰሜን አፍሪካዊቷ ሀገር ላይ ጥሎ የነበረውን ማዕቀብ ያነሳ ሲሆን አንዳንዶች አል-ኢስላም የለውጥ አራማጅ ናቸው ሲሉ ያሞግሳቸው ነበር።
አል-ኢስላማ "ይህ በውርስ የሚሰጥ የእርሻ ቦታ አይደለም" በማለት ከአባታቸው ጋዳፊ ሥልጣን መውረስ እንደማይፈልጉ ደጋግመው ይናገሩ ነበር።
ነገር ግን በ2021 በሀገሪቱ በሚካሔደው ምርጫ ፕሬዝደንታዊ ዕጩ ሆነው መቅረብ እንደሚሹ ቢናገሩም ምርጫው ላልተወሰነ ጊዜ ተራዝሟል።















