የሊቢያ ወታደራዊ መሪ በቱርክ በተከሰተ የአውሮፕላን አደጋ ሞቱ

ጄነራል መሐመድ አሊ አሕመድ አል-ሐዳድ

የፎቶው ባለመብት, Anadolu via Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ጄነራል መሐመድ አሊ አሕመድ አል-ሐዳድ

የሊቢያ ወታደራዊ መሪ ጄነራል መሐመድ አሊ አሕመድ አል-ሐዳድ በቱርክ በደረሰ የአውሮፕላን አደጋ ሳቢያ መሞታቸው ተገለጸ።

የሊቢያ ጠቅላይ ሚኒስትር እንዳሉት፤ ከጄነራል መሐመድ በተጨማሪ ሌሎች አራት ሰዎችም በአደጋው ሞተዋል።

ወታደራዊ መሪው ከቱርክ መዲና አንካራ በፋልከን 50 ጄት ተሳፍረው መጓዝ ከጀመሩ ከ42 ደቂቃ በኋላ ከአውሮፕላኑ የሚተላለፍ ሲግናል መቋረጡን የቱርክ የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር አሊ የርሊካያ ተናግረዋል።

ወደ ትሪፖሊ እየተጓዘ የነበረው አውሮፕላን ሲግናሉ ከመቋረጡ በፊት በድንገተኛ አደጋ ሳቢያ ለማረፍ መገደዱን መረጃ ሰጥቷል።

ብዙም ሳይቆይ በደቡብ ምዕራብ አንካራ የአውሮፕላኑ ስብርባሪ ተገኝቷል።

የአውሮፕላን አደጋው መንስዔ እየተጣራ እንደሚገኝ ተገልጿል።

የቱርክ የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር በኤክስ ገጻቸው እንዳሉት፤ በሀይማንና ግዛት፣ የከሲካቪክ ግዛት ፖሊስ የአውሮፕላኑን ስብርባዎች አግኝቷል።

"ተጨማሪ መረጃ ሲገኝ ለሕዝብ ይፋ የምናደርግ ይሆናል" ብለዋል።

ዓለም አቀፍ ዕውቅና ያለው ሊቢያው አስተዳደር ጠቅላይ ሚኒስትር የሆኑት አብዱል ሐሚድ ደቢብሕ "ሊቢያ በቀናነት እና በታታሪነት ያገለግሏት የነበሩ ሰዎችን አጥታለች" ብለዋል።

የሊቢያ ልዑካን ቡድን ቱርክ እንደሚገኝ ገልጸዋል። የቱርክ እና የሊቢያ ወታደራዊ እና የደኅንነት ጉዳዮች ትብብር እንደሚቀጥልም አክለዋል።

ቱርክ ከ2019 ወዲህ በሊቢያ ቁልፍ ሚና ከሚጫወቱ አገራት አንዷ ሆናለች። ከአገሪቱ ምሥራቃዊ ክፍል የተነሳ ወታደራዊ ኃይል ዓለም አቀፍ ዕውቅና ያለውን መንግሥት እንዳያወርድ ወታደራዊ ድጋፍም ሰጥታለች።

ቱርክ እና ሊቢያ ጠንካራ ፖለቲካዊ፣ ወታደራዊ እና ምጣኔ ሃብታዊ ትስስር አላቸው።