በሜዲትራኒያን ባህር ላይ ጀልባ ተገልብጦ ቢያንስ አራት ስደተኞች ሞቱ

የቀይ ጨረቃ ሠራተኞች ከአደጋው የተረፉ ስደተኞችን ሲያነሱ

የፎቶው ባለመብት, Libyan Red Crescent

የምስሉ መግለጫ, በሊቢያ ቀይ ጨረቃ መሞታቸው የተረጋገጠው ሁሉም ተሳፋሪዎች 26 የባንግላዲሽ ዜጎችን አሳፍራ በነበረች ጀልባ ላይ የነበሩ ናቸው

ቅዳሜ ዕለት ወደ 100 የሚጠጉ ስደተኞችን አሳፍረው የነበሩ ሁለት ጀልባዎች በሊቢያ የባህር ዳርቻ ሰጥመው ቢያንስ አራት ሰዎች መሞታቸውን የነፍስ አድን ሠራተኞች ገለፁ።

እስካሁን በሊቢያ ቀይ ጨረቃ መሞታቸው የተረጋገጠው ሁሉም ተሳፋሪዎች 26 የባንግላዲሽ ዜጎችን አሳፍራ በነበረች ጀልባ ላይ የነበሩ ናቸው።

የሰብዓዊ ቡድኑ ወደ 70 የሚጠጉ አብዛኞቹ ሱዳናውያን የሆኑ ስደተኞችን አሳፍራ በሰጠመችው ሁለተኛዋ ጀልባ ተሳፋሪዎች ላይ ተጨማሪ ሞት ስለመድረሱ ያሉት ነገር የለም።

የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ድርጅት (አይኦኤም) ጀልባዎቹ በሰሜን አፍሪካ እና በጣሊያን መካከል ያለውን "በአደገኛነቱ የሚታወቀው የፍልሰት መንገድ" እየተጠቀሙ ነበር ብሏል።

ጀልባዎቹ በሊቢያ ሰሜን ምዕራብ ከምትገኘው የወደብ ከተማ አል ኩምስ የተነሱ ናቸው ሲል ድርጅቱ ገልጿል።

የሊቢያ ቀይ ጨረቃ ሠራተኞቻቸው በሕይወት ለተረፉ ሰዎች እርዳታ ሲሰጡ፣ እንዲሁም ጥቁር የአስከሬን መያዣ ቦርሳዎች መሬት ላይ ተቀምጦ የሚያሳዩ ምስሎች ይፋ አድርገዋል።

በየዓመቱ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በተጨናነቁ እና አስተማማኝ ባልሆኑ ጀልባዎች ወደ ደቡብ አውሮፓ ለመሻገር ሲሞክሩ ሕይወታቸውን ያጣሉ።

የዓለም አቀፉ ስደተኞች ድርጅት አይኦኤም እንደ አውሮፓውያኑ በ2025 በሜዲትራኒያን ባህር ወደ አውሮፓ ለማቋረጥ የሞከሩ ከ1,500 በላይ ሰዎች ሞተዋል ወይም ጠፍተዋል ብሏል። ከእነዚህ ስደተኞች መካከል አንድ ሦስተኛው የሞቱት በሊቢያ የባህር ዳርቻ ነው።

የአውሮፓ ኅብረት የድንበር ደህንነት ኤጀንሲ ፍሮንቴክስ ደግሞ በዚህ ዓመት በመካከለኛው የሜዲትራኒያን መንገድ ወደ አውሮፓ ከገቡት 59,000 የሚጠጉ ስደተኞች መካከል አብዛኛዎቹ የተነሱት ከሰሜን አፍሪካዋ አገር ሊቢያ ነበር።

በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ ከሊቢያ የባህር ዳርቻ የተነሱ በርካታ ስደተኞችን ያሳፈረች አነስተኛ ጀልባ በሜዲትራኒያን ባህር ላይ ከተገለበጠች በኋላ ስደተኞቹ ጠፍተዋል ወይም ሞተዋል ተብሏል።

በሕይወት የተረፉት ስደተኞች ከሱዳን፣ ከሶማሊያ፣ ከካሜሩን እና ከናይጄሪያ የመጡ ሲሆን ለአንድ ሳምንት ያህል በባህር ላይ ጠፍተው ከቆዩ በኋላ ከሞት ተርፈዋል።