የደቡብ አፍሪካው ፕሬዝዳንት ራማፎሳ የዩክሬን ጦርነት ማብቃት አለበት ሲሉ ለፑቲን ተናገሩ

የዩክሬን ወታደር

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የዩክሬን ጦርነት መቆም አለበት ሲሉ የደቡብ አፍሪካው ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳ ለፕሬዝዳንት ፑቲን ተናገሩ።

ራማፎሳ ይህን ለሩሲያ አቻቸው የተናገሩት በሩሲያዋ ሴይንት ፒተርስበርግ ትናንት ቅዳሜ ከሌሎች ስድስት የአፍሪካ መሪዎች ጋር ሆነው ከፑቲን ጋር በተነጋገሩት ወቅት ነው።

አርብ ዕለት ከዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪ ጋር ሲገናኙ ሩሲያ የዩክሬን መሬትን ለቅቃ እስካልወጣች ድረስ ለንግግር ዝግጁ አይደለንም ሲሉ ዜሌንስኪ ለአፍሪካ መሪዎች ልዑክ ተናግረዋል።

ፑቲን ደግሞ ለአፍሪካ መሪዎቹ ዩክሬን ሁልግዜም ንግግር ለማድረግ ፍቃደኛ አይደለችም ብለዋል።

ሴይንት ፒተርስበርግ በነበረው ስብሰባ ላይ ራማፎሳ ሁለቱ አገራት የጦር ምርኮኞችን እንዲለዋወጡ እንዲሁም ከዩክሬን ከወላጆቻቸው ተነጥለው የተወሰዱ የዩክሬን ልጆችን ሩሲያ እንድትመልስ ራማፎሳ አሳስበዋል።

ሩሲያ ዩክሬን ላይ ወረራ በፈጸመች ወቅት በመቶዎች የሚቆጠሩ ሕጻናትን ከወላጆቻቸው በመነጠል በኃይል ወስዳለች በሚል ቭላድሚር ፑቲን በዓለም አቀፉ የጦር ወንጀለኞች ፍርድ ቤት በጦር ወንጀል ክስ ተመስርቶባቸዋል።

የአፍሪካ መሪዎች ልዑክ እነዚህ ልጆች ወደ ቀደመ መኖሪያቸው መመለስ አለባቸው እያለ ንግግር ላይ ሳለ ፑቲን ጣልቃ በመግባት ሩሲያ ለልጆቹ ጥበቃ እያደረገች ነው ብለዋል።

“ልጆቹ ተሸብረዋል። ከግጭት ቀጠና አውጥተናቸው ሕይወታቸው ታድገን ጤናቸው ጠበቅን” ብለዋል።

ራማፎሳ የሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት በአፍሪካ ላይ ስለሚያሳድረው አሉታዊ ተጽእኖ ለፑቲን በመግለጽ ጦርነቱ በዲፕሎማሲያዊ መንገድ መፈታት አለበት ብለዋል።

“ጦርነት ሁሌም ቀጥሎ ሊካሄድ አይችልም። ሁሉም ጦርነት መፍትሄ አግኝቶ ማብቃቱ የማይቀር ነው” ካሉ በኋለ “እዚህ የተገናኘነው ይህ ጦርነት እንዲያበቃ ጽኑህ ፍላጎት እንዳለን ለማሳወቅ ነው” ብለዋል።

ጦርነቱ ጥሬ እህል ከዩክሬን እንዲሁም ለእርሻ ግብዓት የሚሆነው ማዳበሪያ አፍሪካ አገራት እንዳይርስ ችግር ፈጥሯል።

ፑቲን የዩክሬን እህል ድሃ ወደሆኑ የአፍሪካ አገራት እንዳይደርስ ምክንያት የሆኑት ምዕራባውያን ናቸው ካሉ በኋላ የሞስኮ ምርት የሆኑ የግብርና ግብዓቶችም ወደ ሌሎች አገራት እንዳይላኩ የምዕራባውያን ማዕቀብ እክል ሆኗል ይላሉ።

ከደቡብ አፍሪካ፣ ግብጽ፣ ሴኔጋል፣ ኮንጎ-ብራዛቪል፣ ኮሞሮስ፣ ዛምቢያ እና ኡጋንዳ የተወጣጡ የአፍሪካ ልዑክ ቡድን ከፑቲን ሲገናኙ ፕሬዝዳንቱ አፍሪካ በጦርነቱ ዙሪያ የያዘችው አቋም ለአንድ ወገን ያላደላ ነው ብለዋል።

ደቡብ አፍሪካ እና ኡጋንዳ ለሩሲያ በመወገን ይተቻሉ። ዛምቢያ እና ኮሞሮስ ደግሞ ከምዕራባውያን አገራት ወገን ናቸው ሲባሉ፤ ሴኔጋል፣ ግብጽ እና ኮንጎ-ብራዛቪል ደግሞ በስፋት ገለልተኛ የሆነ አቋም ሲያንጸባርቁ ይታያሉ።

ብዙ የአፍሪካ አገራት ይህን ጦርነት በሩሲያ እና ዩክሬን መካከል የሚደረግ ሳይሆን በሩሲያ እና በምዕራባውያን አገራት መካከል እየተደረገ እንደሆነ አድርገው ይመለከታሉ።