የአሜሪካ ተዋጊ ጄት በቀይ ባህር ላይ 'በስህተት' ተመትቶ ወደቀ

 የዩናይትድ ስቴትስ ተዋጊ ጄት

የአሜሪካው የጦር መርከብ በቀይ ባህር ላይ በስህተት የራሱን ተዋጊ ጄት መትቶ መጣሉን የአሜሪካ ጦር አስታወቀ።

ሁለቱም የአሜሪካ የጦር ኃይል አባላት ጉዳት ሳይደርስባቸው መውጣት መቻላቸውን የጦሩ የማዕከላዊ ዕዝ ገልጿል።

አሜሪካ በየመን ዋና ከተማ ሰንዓ በሚገኘው እና በኢራን በሚደገፉ የሁቲ ታጣቂዎች የሚተዳደረውን የሚሳኤል ማከማቻ እና ማዘዣ ጣቢያ ላይ ተከታታይ የአየር ድብደባ ካደረገች በኋላ አጋጣሚው መከሰቱ ተገልጿል።

የአሜሪካ ማዕከላዊ ዕዝ አክሎም በቀይ ባህር ላይ የሚገኙ በርካታ የሁቲ ሰው አልባ አውሮፕላኖችን እና ፀረ መርከብ ክሩዝ ሚሳዔሎችን መምታቱን አስታውቋል።

ማዕከላዊ ዕዙ በሰጠው መግለጫ በቀይ ባህር ላይ በነበረ ተኩስ ወቅት አደጋው መከሰቱን አረጋግጧል።

"የአሜሪካው ሃሪ ኤስ ትሩማን የጦር መርከብ አካል የሆነው የዩናይትድ ስቴትስ ጌቲስበርግ በስህተት ከመርከቡ ሲነሳ ነበረውን ኤፍ/ኤ-18 መትቶታል" ሲል በመግለጫው አስታውቋል።

የወደቀው አይሮፕላን በየመን ዘመቻ ውስጥ ስለመሳተፍ አለመሳተፉ የታወቀ ነገር የለም።

በሰንዓ በሚገኙ ዒላማዎች ላይ የተፈጸመው ጥቃት "ሁቲዎች በአሜሪካ የባህር ኃይል መርከቦች እና በደቡብ ቀይ ባህር፣ ባብ አል-ማንደብ እና በኤደን ባህረ ሰላጤ ላይ ያሉ የንግድ መርከቦች ላይ የሚያደርሱትን ጥቃት ለማደናቀፍ እና ለማቀጨጭ ነው" ሲል የማዕከላዊ ኮማንዱ አስታውቋል።

የአሜሪካ ወታደራዊ ሃይል "ኤፍ/ኤ-18ን ጨምሮ የአሜሪካ አየር ኃይል እና የባህር ሃይሎችን" በመጠቀም "በርካታ የሁቲ ተሽከርካሪዎች ወይም ሰው አልባ አውሮፕላኖች እና በቀይ ባህር ላይ የሚገኙ ጸረ-መርከብ ክሩዝ ሚሳዔል" መምታቱን ተናግሯል።

ሰሜን ምዕራብ የመንን የሚቆጣጠረው እና በኢራን የሚደገፈው አማፂው የሁቲ ቡድን ከፍልስጤማውያን ጎን መቆሙን በማስታወቅ የጋዛ ጦርነት መጀመርን ተከትሎ በእስራኤል እና በዓለም አቀፍ መርከቦች ላይ ጥቃት መሰንዘር ጀመረ።

ከህዳር 2023 ወዲህ እንኳን የሁቲ ሚሳዔል ጥቃቶች ሁለት መርከቦችን በቀይ ባህር ሲያሰጥሙ ሌሎች ላይ ጉዳት አድርሰዋል። ከእስራኤል፣ ዩናይትድ ኪንግደም ወይም እንግሊዝ ጋር የተገናኙ መርከቦች ላይ ብቻ እያነጣጠርን ነው ይላሉ።

ባለፈው ታህሳስ ወር አሜሪካ፣ ፣ ዩናይትድ ኪንግደም እና ሌሎች 12 አገራት የቀይ ባህርን የመርከቦች እንቅስቃሴ ከጥቃት ለመከላከል 'ኦፕሬሽን ፕሮስፐሪቲ ጋርዲያን' የሚባል ዘመቻ አስተዋውቀዋል።

በሁቲ ጥቃት በቴል አቪቭ የደረሰው ጉዳት

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ከየመን የተወነጨፈ ሚሳዔል ለመምታት ያደረገው ሙከራ እንዳልተሳካ እና ሚሳኤሉ በቴልአቪቭ የሚገኝ መናፈሻን መትቷል ሲል የእስራኤል ጦር ቅዳሜ ዕለት ገልጿል።

የእስራኤል የድንገተኛ ህክምና አገልግሎት ባልደረባው ማጌን ዴቪድ አዶም በአቅራቢያው ያሉ ህንጻዎች መስታወቶች በመሰባበራቸው ምክንያት "መካከለኛ ጉዳት" የደረሰባቸው 16 ሰዎችን ማከማቸውን ተናግሯል።

ለመሸሽ ሲሞክሩ የነበሩ 14 ሰዎች ቀላል የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋልም ብሏል።

የሁቲ ቃል አቀባይ በበኩላቸው ቡድኑ ሃይፐርሶኒክ ባሊስቲክ ሚሳዔል በመጠቀም ወታደራዊ ዒላማውን መትቷል።

በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ እስራኤል በሁቲ ወታደራዊ ዒላማዎች ላይ አደረስኩት ባለችው ተከታታይ ጥቃቶች በየመን ዋና ከተማ ሰነዓ የሚገኙ ወደቦች እና የኃይል መሰረተ ልማቶችን መትታለች።

በሁቲ የሚመራው አል ማሲራህ ቲቪ በበኩሉ በሳሊፍ ወደብ እና በራስ ኢሳ የነዳጅ ጣብያ ዘጠኝ ሰዎች ተገድለዋል።

ሁቲዎች የጋዛው ጦርነት እስኪያበቃ ድረስ ጥቃታቸውን ለመቀጠል ቃል ገብተዋል። ዩናይትድ ስቴትስ በቅርቡ የወሰደችው ጥቃት ራሷን እና አጋሮቿን ለመጠበቅ የገባችው ቃል አካል ነው ብሏል።