በናይጄሪያ የነጻ ምግብ ዕደላ ላይ በተከሰተ መረጋገጥ 22 ሰዎች ሞቱ

ሲታደል የነበረ ሩዝ

የፎቶው ባለመብት, AFP

በናይጄሪያ ደቡባዊ ምስራቅ ኦክጃ ከተማ በነጻ የምግብ ዕደላ ላይ በተከሰተ መረጋገጥ የሟቾች ቁጥር 22 ደረሰ።

ነጻ ምግብ በሚታደልበት ወቅት ሰዎች ተረጋግጠው ሲሞቱ ይህ በዚህ ሳምንት ለሶስተኛ ጊዜ ነው።

የጎሮጎሮሳውያኑን የዘመን አቆጣጠር በሚከተሉት ዘንድ የሚከበረውን የገና በዓል አስመልክቶ ቅዳሜ ዕለት እየተደረገ በነበረ እርዳታ ላይ ነው ይህ ግርግር የተፈጠረው።

በርካቶች ሩዝ እና ዘይት ለመውሰድ በሚጣደፉበት ወቅት በተነሳው መረጋገጥ ሰዎች ተጨፍልቀው መሞታቸው ተገልጿል።

በተመሳሳይ ዕለት በዋናዋ ከተማ አቡጃ በሚገኘው የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ተመሳሳይ አደጋ ተከስቶ አስር ሰዎች ሞተዋል። ከዚያ ቀደም ብሎ ባለፈው ሳምንት ረቡዕ ዕለት ኢባዳን በተሰኘችው ከተማ በነበረ የካርኒቫል ዝግጅት የ35 ህጻናት ህይወት ተቀጥፏል።

ፖሊስ እንደዚህ አይነት የህይወት መጥፋትን ለመከላከል ዕርዳታ ሰጪዎች የበጎ አድራጎት ዝግጅቶችን ከማድረጋቸው በፊት ለባለስልጣኑ እንዲያሳውቁ አስጠንቅቋል።

በአቡጃ የቅድስት ስላሴ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን በነበረው የዕርዳታ አሰጣጥ ላይ በርካቶች የቤተ ክርስቲያኑን በር ጥሰው እንደገቡ ቶይን አብዱል ካድሪ የተሰኙ የዓይን እማኝ ለኤኤፍፒ የዜና ወኪል ተናግረዋል።

በዚህም አዛውንቶች ጭምር የተጎዱ ሲሆን አራት ህጻናት መገደላቸውን ፖሊስ ተናግሯል።

ጉዳቱን ተከትሎ አምነስቲ ኢንተርናሸናል ባወጣው መግለጫ "የፕሬዚዳንት ቦላ ቲኒዩ መንግሥት በአገሪቱ የተንሰራፋውን ረሃብ፣ ከፍተኛ ስራ አጥነት እና ከፍተኛ የኑሮ ውድነት ለመቅረፍ በአስቸኳይ ቅድሚያ ሊሰጥ ይገባል" ሲል አሳስቧል።

በናይጄሪያ የምግብ እና የትራንስፖርት ወጪዎች ባለፉት 18 ወራት ብቻ ከሶስት እጥፍ በላይ ጨምሯል።

የአለም አቀፍ የዋጋ ግሽበት እና መንግሥት እየተከተላቸው ያሉ እንደ ነዳጅ ድጎማ ማቆም የኑሮ ውድነቱን የበለጠ የከፋ አድርገውታል።

"በደስታ እና በበዓል ሰሞን ዜጎቻችን በወገኖቻቸው ላይ በደረሰው አሰቃቂ መታጣት አብረናቸው እናዝናለን። መጽናናትን እንዲያገኙ ጸሎታችን ከእነሱ ጋር ነው" ሲሉ ነው ፕሬዚዳንት ቦላ ቲኑቡ የገለጹት።

የክልል መንግሥታት እና ፖሊስ ህዝብ በሚሰባሰብባቸው ስፍራዎች ጥብቅ የሆኑ የቁጥጥር እርምጃዎችን እንዲተገብሩ አሳስበዋል። ህይወታቸውን ላጡ ተጎጂዎችን ለማሰብ መንግሥታቸው አቅዶ የነበሩ ዝግጅቶች እንዲሰረዙ ትዕዛዝ ሰጥተዋል።

በተጨማሪም በባለፈው ሳምንት መጀመሪያ ላይ በኢባዳን ከተማ የተከሰተውን ግርግር ከሌሎቹ ጋር ተመሳሳይነት እንዳለው ጠቅሰዋል።

በአንድ ትምህርት ቤት በነበረ የካርኒቫል ዝግጅት ላይ ነጻ ምግብ እንደሚታደል መነገሩን ተከትሎ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መምጣታቸውን ተከትሎ 35 ህጻናት ተገድለዋል። እንዲሁም ስድስት ሰዎች ተጎድተዋል።