ወንድሟን ከሞት ፍርድ ነጻ ለማውጣት ለ56 ዓመታት የታገለችው እህት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የጃፓኑ ፍርድ ቤት በመስከረም ወር በዓለም ላይ ረዥም ዓመት የቆየውን የሞት ፍርደኛ፣ ኢዋዎ ሃካማታን፣ ንፁሕ ነው ብሎ ሲፈርድ ደስታና ሐዘን ተቀላቅለው የተደበላለቀ ስሜት ፈጥረው ነበር።
የ91 ዓመቷ እህቱ ሂዴኮ ሃካማታ በጃፓን ሃማማሱ በሚገኘው መኖሪያ ቤቷ ሆና ለቢቢሲ "ከክሱ ነጻ ተብሎ እንዲፈታ መወሰኑን ስነግረው ዝም አለ። . . . ያልኩትን ተረድቶኝ ይሁን ወይም አይሁን ማወቅ አልቻልኩም" ብላለች።
ሂዴኮ ወንድሟ በአውሮፓውያኑ1968 የአንድ ቤተሰብ አባል የሆኑ አራት ሰዎችን በመግደል ተከስሶ ከተፈረደበት ጊዜ አንስቶ፣ ውሳኔው ዳግም እንዲታይ ስትታገል ነበር።
እ.ኤ.አ. በመስከረም 2024፣ በ88 ዓመቱ፣ በመጨረሻ ውሳኔ ተሰጠው፤ ይህም በጃፓን ረዥም ዓመት የወሰደ የሕግ ክርክር ፍጻሜ ሆኖ ተመዝግቧል።
በጃፓን የሞት ፍርድ የተፈረደባቸው እስረኞች፣ ውሳኔው ሊፈጸምባቸው ጥቂት ሰዓታት ሲቀረው ብቻ ነው ሊሰቀሉ እንደሆነ የሚነገራቸው፤ እናም እያንዳንዷ ቀን የመጨረሻቸው ስለመሆኗ እርግጠኛ ባልሆኑበት ዓመታትን ያሳልፋሉ።
በዚህም የተነሳ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች፣ እስረኞች ለከባድ የአእምሮ ሕመም የመጋለጥ እድላቸውን ያባብሳል፤ እንዲህ ዓይነቱ ድርጊት ጭካኔ የተሞላበት እና ኢሰብዓዊ ነው በማለት ሲያወግዙ ቆይተዋል።
እናም ሃካማታ ከግማሽ በላይ የሕይወት ዘመኑንን በብቸኝነት፣ ባልሰራው ወንጀል እንደሚገደል እየጠበቀ ያሳለፋቸው ዓመታት ጥቁር ጠባሳ ጥለውበት አልፈዋል።
በ2014 ጉዳዮ በድጋሚ እንዲታይ ተወስኖ ከተለቀቀ ጊዜ ጀምሮ በእህቱ ሂዴኮ የቅርብ እንክብካቤ ስር ቆይቷል።
የቢቢሲ ጋዜጠኞች የመኖርያ አፓርትመንት ሲደርሱ ሁለቱ አረጋውያን ወንድምና እህትን የሚደግፍ የበጎ ፈቃደኞች ቡድን ጋር ወጣ ብሎ ነበር።
እንግዳ ፊት ሲያይ ይጨነቃል፤ ሂዴኮ "በራሱ ዓለም" ውስጥ ለዓመታት በመቆየቱ ያዳበረው መሆኑን ታስረዳለች።
"ምናልባት ልንረዳው አንችልም" ትላለች። "ይህ የሆነው ከ40 ዓመታት በላይ በአንዲት ትንሽ እስር ቤት ውስጥ በመታሰሩ ነው።. . . እንደ እንስሳ እንዲኖር አደረጉት።" ትላለች በቁጭት።
የሞት ፍርደኛ ሕይወት
የቀድሞ ፕሮፌሽናል ቦክሰኛ የነበረው ኢዋዎ ሃካማታ በሚሶ ማቀነባበሪያ ፋብሪካ ውስጥ እየሰራ ሳለ የአለቃው፣ የሚስቱ እና የሁለት ታዳጊ ልጆቻቸው አስከሬን ተገኘ። አራቱም የተገደሉት በስለት ተወግተው ነበር።
ባለሥልጣናቱ ሚስተር ሃካማታን ቤተሰቡን በመግደል፣ ቤታቸውን በማቃጠል እና 200,000 የን (£199፤ $556) በጥሬ ገንዘብ በመዝረፍ ከሰሰው።
በ1966 ፖሊስ ወንድሟን ለመያዝ በመጣበት ቀን "ምን እንደተፈጠረ ምንም አናውቅም ነበር" ስትል ሂዴኮ ታስታውሳለች።
የቤተሰቡ ቤት፣ እንዲሁም የሁለቱ ታላቅ እህቶቻቸው ቤት ተፈትሾ ሃካማታ ተወሰደ።
መጀመሪያ ላይ ሁሉንም ክሶች አልፈጸምኩም ብሎ የተከራከረ ቢሆንም፣በኋላ ግን በቀን እስከ 12 ሰዓታት የዘለቀ ድብደባ እና ምርመራን ሲደረግበት ወንጀሉን መፈጸሙን አምኗል።
ከታሰረ ከሁለት ዓመት በኋላ ሚስተር ሃካማታ በግድያ እና ሆን ብሎ ንብረት በማቃጠል ወንጀል ተከሶ ሞት ተፈረደበት።
ሂዴኮ ወንድሟ ወደ ሞት ፍርደኞች ክፍል ሲዛወር ነበር ለውጥ ያስተዋለችበት።
በተለይ አንድ ጉብኝቷን አትረሳውም።
"ትናንት ከ እኔ ክፍል ቀጥሎ እኖር የነበረ ሰው ላይ የሞት ፍርድ ተፈጸመበት" አለኝ በማለት ታስታውሳለች።
"ራስሽን ጠብቂ አለኝ፤ እና ከዚያ በኋላ ሙሉ በሙሉ ተለውጦ በጣም ዝምተኛ ሆነ ።"
የጃፓን ሞት ፍርደኞች የማለዳ ወፎች ዝማሬ ደስታን ብቻ አይደለም የሚያቀብሏቸው የስጋት ቆፈን ይለቁባቸዋል።
መቼ ፍርዱ እንደሚፈጸምባቸው ሳያውቁ እያንዳንዷን ቀን ማሳለፍ ሃካማታን እና ሌሎችን ለአእምሮ ጤና መቃወስ ዳርጓቸዋል።
"ከጠዋቱ 2፡00 እስከ 2፡30 ያለው ጊዜ፣ የሞት ፍርድ ውሳኔያቸው የሚፈጸምባቸው እስረኞች የሚነገራቸው ሰዓት በመሆኑ፣ በጣም ወሳኙ ጊዜ ነበር" በማለት ነፃ ከመውጣቱ በፊት 34 ዓመታትን በሞት ፍርድ ያሳለፈው ሜንዳ ሳካ መጽሐፍ ጽፏል።
"በጣም አስፈሪ ጭንቀት መሰማት ትጀምራለህ፤ ምክንያቱም ባለህበት ክፍል በር ላይ መትተው ይቁሙ ወይ አይቁሙ አታውቅም።ይህ ምን ያህል አሰቃቂ ስሜት እንደነበረ ለመግለጽ አይቻልም።"
በ2009 አምነስቲ ኢንተርናሽናል ይህንን የሞት ፍርድ ቅጣት ሁኔታ "የማይቀረውን የሞት ቅጣት ጥበቃ የፈጠረው ስጋት ጨካኝ፣ ኢሰብዓዊ እና አዋራጅ ነው" ብሎ ነበር።
ሪፖርቱ እስረኞች "ከፍተኛ የአእምሮ ጤና" ስጋት ላይ መሆናቸውን ደምድሟል።

ሂዲኮ ዓመታት እያለፉ ሲሄዱ የወንድሟ የአእምሮ ጤና እያሽቆለቆለ ሲሄድ አስተውላለች።
አንድ ጊዜ 'እኔ ማን እንደሆንኩ ታውቂያለሽ?" ሲል ጠየቀኝ። "እኔም፣ 'አዎ፣ አንተ ኢዋኦ ሃካማታ ነህ' አልኩት፣ 'አይሆንም፣ ሌላ ሰው ለማየት መጥተሽ መሆን አለበት' ብሎ ጥሎኝ ሄደ።"
ሂዴኮ ለወንድሟ አፍ መሆን ብቻ ሳይሆን ተሟጋቹም ነበረች።
በሃካማታ ላይ ከቀረቡት ቁልፍ ማስረጃዎች መካከል በስራ ቦታው በሚሶ የውሃ ገንዳ ውስጥ የተገኙ በቀይ ቀለም የበለዙ ልብሶች ነበሩ።
እነዚህ ማስረጃዎች ግድያው ከተፈጸመ ከአንድ ዓመት ከሁለት ወር በኋላ የተገኙ ሲሆን አቃቤ ሕግም የእሱ ናቸው ብሏል።
ነገር ግን ለአመታት የሃካማታ ጠበቆች ከልብሱ ላይ የተገኘው ዲኤንኤ ከእርሱ ጋር አይመሳሰልም፤ የቀረበውም ማስረጃ ሆን ተብሎ የተቀነባበረ ነው ሲሉ ተከራክረዋል።
እ.ኤ.አ. በ 2014 ዳኛው ከእስር ቤት እንዲፈታ እና ጉዳዩ ዳግም እንዲታይ ውሳኔ አሳልፈዋል።
በፍርድ ቤት ውሳኔ መሰረት ክሱን ዳግም ለማየት እስከ ባለፈው ጥቅምት ወር ድረስ የተራዘመ የሕግ ክርክር የፈጀ ሲሆን፣ ክሱ መታየት ሲጀምርም ወንድሜ ጥፋተኛ አይደለም ብላ ለመሞገት ፍርድ ቤት የተገኘችው ሂዴኮ ነበረች።
የሃካማታ ዕጣ ፈንታ ወንጀሉ ከተፈጸመ ከመቆየቱ የተነሳ በቀጭን ገመድ ላይ የተንጠለጠለ ነው
አቃቤ ሕግ በማስረጃነት የቀረቡት ልብሶች በተገኙበት ጊዜ ቀይ ምልክት [የደም ምልክት] ነበራቸው ብሏል።
ነገር ግን ጠበቆች ልብሱ ለረዥም ጊዜ ከተቀመጠ ደሙ ወደ መጥቆር ነበረበት ሲሉ ተከራክረዋል።
ይህም ዳኛው በሃካማታ ላይ ምርመራውን ያደረጉት ፖሊሶች ማስረጃዎች ሆን ብለው አቀነባብረዋል ብለው እንዲያምኑ ለማድረግ በቂ ነበር።
ይህም "የመርማሪው ባለስልጣን የደም እድፍ ጨምሯል እና ክስተቱ ከተከሰተ በኋላ እቃዎቹን በሚሶ ታንክ ውስጥ በደንብ ደብቋል" በማለት ሰብሳቢውን ዳኛ ኮሺ ኩኒ ለማሳመን በቂ ነበር።
ዳኛው በተጨማሪ የምርመራ መዝገብን ጨምሮ ሌሎች ማስረጃዎች በሃካማታ ላይ እንደተፈበረኩ እና ከወንጀሉ ንፁህ መሆኑን ተናግረዋል።
የሂዴኮ የመጀመሪያ ምላሽ ማልቀስ ነበር።
"ዳኛው ተከሳሹ ጥፋተኛ አይደለም ሲሉ በጣም ተደሰትኩ፤ እያለቀስኩ ነበር" ብላለች። "አልቃሻ ሰው አይደለሁም፤ ነገር ግን እንባዬ ለአንድ ሰዓት ያህል ያለማቋረጥ ይወርድ ነበር"

የታገተ ፍትሕ
ፍርድ ቤቱ በአቶ ሃካማታ ላይ የቀረቡት ማስረጃዎች የተቀነባበሩ ናቸው ሲል ያሳለፈው ውሳኔ አሳሳቢ ጥያቄዎችን አስነስቷል።
በጃፓን የወንጀል ፍትህ ላይ ያተኮረ ጥናት የሰሩት እና የሶሲዮሎጂ ፕሮፌሰር የሆኑት ዴቪድ ቲ ጆንሰን የሃካማታን ጉዳይ ላለፉት 30 ዓመታት ተከታትለዋል።
ሃካማታ የፍትሕ ጸሐይ እንደናፈቀችው በፍርድ ቤት አስርት ዓመታትን ያሳለፈበት ምክንያት "ለተከላካይ ጠበቆች ወሳኝ የሆነው ማስረጃ እስከ 2010 ድረስ ይፋ አልሆነላቸውም" ነበር ይላሉ።
ውድቀቱ "አስደንጋጭ እና ማስተባበያ የማይቀርብበት ነው" ሲሉ ፕሮፌሰር ጆንሰን ለቢቢሲ ተናግረዋል። "ዳኞች ክሱ ዳግም እንዲታይ ለመወሰን በተደጋጋሚ ሲገፉት የነበረው ስራ ስለሚበዛባቸው እንደሆነ ይታወቃል ሕጉም ግን ይፈቅድላቸዋል።"
ሂዴኮ የፍትህ መጓደሉ አስኳል በግዳጅ እንዲናዘዝ መደረጉ እና የደረሰበት ማስፈራርያ እና ዛቻ እንደሆነ ትናገራለች።
ነገር ግን ፕሮፌሰር ጆንሰን የሐሰት ውንጀላዎች በአንድ ስህተት ምክንያት ብቻ አይከሰቱም ይላሉ።
ይልቁንስ በየደረጃው ያሉ ውድቀቶች፣ ከፖሊስ ጀምሮ እስከ አቃቤ ሕግ፣ ከፍርድ ቤት እስከ ፓርላማ ድረስ የዘለቁ ናቸው።
"ዳኞች የመጨረሻው ቃል አላቸው" የሚሉት ፕሮፌሰሩ፣ "የተሳሳተ የጥፋተኝነት ክስ ተመስርቶ ውሳኔ ሲተላለፍ በመጨረሻ እነሱ በመወሰናቸው የሆነ ነው። ብዙ ጊዜ ዳኞች የተሳሳቱ ፍርዶችን የመወሰን እና የማስቀጠል ኃላፊነት ችላ ተብሏል፣ተዘሏል ካልሆነም ወደ ጎን ተገፍቷል።" ይላሉ።
በዚያ ዳራ ውስጥ ሃካማታ ከጥፋተኝነት ነፃ መውጣቱ ያልተለመደ እና ከስንት አንድ ጊዜ የሚገኝ እድል ነው።
ሃካማታ ከቀረበበት ክስ ነጻ ያሉት ዳኛ ፍትህን ለማግኘት ይህን ያህል ጊዜ በመፍጀቱ ይቅርታ ጠይቀውታል።
ከጥቂት ቆይታ በኋላ የሺዙካ ፖሊስ አዛዥ ታካዮሺ ቱዳ ቤታቸው ተገኝተው ወንድም እና እህትየውን እጅ ነስተዋል።












