አርሰናል እና ማንቸስተር ሲቲ ሽንፈት ሲቀምሱ፤ ሊቨርፑል ወደ ሊጉ መሪነት ተመልሷል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በያዝነው የውድድር ዘመን ዋንጫ ሊያነሱ ይችላሉ ተብለው ተስፋ የተጣለባቸው አርሰናል እና ማንቸስተር ሲቲ በቅዳሜ የፕሪሚዬር ሊግ ጨዋታዎች ሽንፈት ቀምሰዋል።
ባለፉት ሁለት የውድድር ዘመናት ከማንቸስተር ሲቲ ጋር አንገት ለአንገት ተናንቀው የፕሪሚዬር ሊጉ ዋንጫ ያመለጣቸው አርሰናሎች በኒውካል 1-0 ተሸንፈዋል።
የአሰልጣኝ ሚኬል አርቴታ ተጫዋቾች ሽንፈቱን ተከትሎ ከሊጉ መሪ ሊቨርፑል በ7 ነጥብ ርቀው ተቀምጠዋል።
ከሰባት ነጥብ ልዩኑት ተነስተው ከዚህ ቀደም የፕሪሚዬር ሊግ ዋንጫ ማንሳት የቻሉት ብላክበርን፣ ማንቸስተር ዩናይትድ እና ማንቸስተር ሲቲ ናቸው።
ባለፉት ሶስት የሊጉ ጨዋታዎች ድል የራቃቸው መድፈኞቹ ከኖቲንግሀም ፎረስት በታች አራተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።
አርሰናል ካለፉት ስድስት ጨዋታዎች በአራቱ ቀድሞ ጎል ተቆጥሮባቸዋል። በተከታታይ ከሜዳቸው ውጭ ባደረጓቸው ጨዋታዎች ቀድሞ ጎል የተቆጠረባቸው ሚኬል አርቴታ አሰልጣኝ ሆነው ከመምጣታቸው አስቀድሞ ነው።
በ2024 በ25 ጨዋታዎች አንድ ጨዋታ ብቻ የተሸነፉት መድፈኞቹ ካለፉት ሶስት ጨዋታዎች ሁለቱን ተረትተዋል።
አርሰናል በዘንድሮው የውድድር ዘመን ከሜዳው ውጭ ሲጫወት ለጎል የሚሆኑ ኳሶችን ማመቻቸት ያቃተው ይመስላል።
አሰልጣኝ ሚኬል አርቴታ ስለሸንፈቱ ከማውራት ይልቅ በሥራ እናሳያለን የሚል አስተያየት ሰጥተዋል።
አሰልጣኙ በሚመጣው ረቡዕ በአውሮፓ ቻምፒዮንስ ሊግ በኢንተር ሚላን ሜዳ በሚደረገው ጨዋታ ለተቺዎቻቸው መልስ እንደሚሰጡ ተናግረዋል።
“ዋንጫ የማንሳት ተስፋ ጉዳይ አይደለም። በየሳምንቱ የተሻለ አቅም የማሳየት ጉዳይ ነው። ዛሬ ምርጥ አቋም አላሳየንም።”
አምበሉ ማርቲን ኦዴጋርድ በጉዳት ምክንያት ከሜዳ መራቁ አርሰናልን እንደጎዳው ተንታኞች ይናገራሉ።
በተመሳሳይ ከአርሰናል ጋር ለዋንጫው ትልቅ ግምት የተሰጠው ማንቸስተር ሲቲ ከሜዳው ውጭ በቦርንመዝ 2-1 ተሸንፏል።
ባለፉት 32 ጨዋታዎች ሽንፈት አስተናግዶ የማያውቀው ሲቲ በፕሪሚዬር ሊጉ ሰንጠረዥ ከሊቨርፑል በሁለት ነጥብ ዝቅ ብሎ ወደ ሁለተኛ ደረጃ ወርዷል።
“ቦርንመዝ ፍጥነታቸው ልዩ ነው። እሱን ልንቆጣጠረው አልቻልንም” ሲሉ ፔፕ ጉዋርዲዮላ ተናግረዋል።
የማንቸስተር ሲቲ አሰልጣኝ ሆነው በአውሮፓውያኑ 2016 የተሾሙት ጉዋርዲዮላ 488 ጨዋታዎችን አድርገው 360 ሲያሸንፉ 60 ጨዋታዎች አቻ ወጥተዋል፤ 68 ፍልሚያዎች ተሸንፈዋል።
ሲቲ ለመጨረሻ ጊዜ ሽንፈት ያስተናገደው በ2023 ከሜዳው ውጭ ከአስተን ቪላ ጋር ባደረገው ጨዋታ ነበር።
ኧርሊንግ ሀላንድ፣ ኤደርሰን፣ ፊል ፎደን፣ ኢካይ ጉንዶዋን እና በርናንዶ ሲልቫ ሲቲ እንዲያሸንፍ ያደረጉት ጥረት አልተሳካም። በጉዳት ምክንያት ነባር ተቀያሪዎቻቸውን ይዘው ያልገቡት ፔፕ ሁለት ተጫዋቾች ብቻ ነው የቀየሩት።
በሌሎች የፕሪሚዬር ሊግ ጨዋታዎች ሊቨርፑል በሜዳው አንፊልድ ብራይተንን አስተናግዶ 2-1 በመርታት የሊጉ መሪ መሆን ችሏል።
ኢፕስዊች ከሌስተር አቻ ሲወጡ ኖቲንግሀም ፎረስት ዌስት ሀምን በመርታት ሶስተኛ ደረጃን ተቆናጧል። ሳውዝአምፕተን ድል ሲቀናው ዎልቭስ እና ክሪስታል ፓላስ 2 አቻ ተለያይተዋል።
እሑድ በፕሪሚዬር ሊጉ የሳምንቱ ተጠባቂ ጨዋታ በኦልድ ትራፈርድ ይደረጋል። አሰልጣኝ ኤሪክ ቴን ሀግን ያሰናበተው ማንቸስተር ዩናይትድ ቼልሲን ያስተናግዳል።
ከዚህ ጨዋታ ቀደም ብሎ ቶተንሀም ከአስተን ቪላ ይጫወታሉ።












